
10 ሀምሌ 2023, 08:14 EAT
ተሻሽሏል ከ 9 ሰአት በፊት
ለወራት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት እየተባባሰ ወዳለባት ሱዳን ወታደራዊ ኃይል እንዲሰማራ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሐሳብ አቀረቡ።
በአዲስ አበባ ዛሬ ሰኞ በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት ኢጋድ ስብሰባ ላይ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ወደ ሱዳን ተሰማርቶ ሰላማዊ ሰዎችን እና የእርዳታ አቅርቦትን ለመጠበቅ እንዲያግዝ ሐሳብ ቀርቧል።
በሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ጄኔራሎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ በተባባሰበት በአሁኑ ወቅት የውጭ ወታደሮችን ማሰማራት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚሆን እና በውጊያ ላይ ያሉት ወገኖችም ሐሳቡን ላይቀበሉት እንደሚችሉ ተነግሯል።
አዲስ አበባ ላይ የተካሄደው ስብሰባ ላይ የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዦችን በአካባቢው አገራት መሪዎች አማካይነት ፊት ለፊት ለማነጋገር የታቀደ ነበር።
ነገር ግን የተፋላሚ ኃይሎቹ ተወካዮች አለመገኘታቸው እንዳሳዘነው ኢጋድ የገለጸ ሲሆን፣ ቢሆንም ግን በአካባቢው አገራት መሪዎች እና በሌሎችም የውይይቱ ተሳታፊዎች ጥልቅ ውይይት መደረጉን ገልጿል።
የሱዳን ጦር ሠራዊት መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሐን፣ የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር የሆኑትን የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ይደግፋሉ በሚል ገለልተኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ ማስገባታቸው ይታወቃል።
የአዲስ አበባው የኢጋድ ስብሰባ
በሱዳን እየተካሄደ ላለው የእርስ በርስ ጦርነት መፍትሄ ለማፈላለግ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) አማካይነት የአራትዮሽ የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ሁለቱን የሱዳን ተፋላሚ የጦር ጀኔራሎችን ለማቀራረብ የአካባቢው አገራት መሪዎችን ጨምሮ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊ እንዲሁም ሱዳናውያን እንደተሳፉበት ተገልጿል።
በዚህ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐመድ አሊ እና የኢጋድ ሊቀ መንበር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ተሳታፊ ሆነዋል።
እንዲሁም የዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ድርጅቶች ተወካዮች በምክክሩ ላይ እየተሳተፉ ሲሆን በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ሞሊ ፊም ተሳታፊ እንደሚሆኑ የአሜሪካ መንግሥት አስታውቋል ነበር።
የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ሞሊ ፊ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ በስም ያልተጠቀሱ በቀጠናው ያሉ አገራት ተወካዮች እንዲሁም ግጭቱን ለማስቆም ጥረት እያደረጉ ካሉ ሲቪል ሱዳናውያን ንግግር ያደርጋሉ ብሏል ከአሜሪካ መንግሥት የወጣው መግለጫ።
ሰኞ እና ማክሰኞ በሱዳን ጉዳይ አዲስ አበባ ላይ እየተካሄደ ባለው ንግግር ላይ የግጭቱ መሪ የሆኑት የጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ወይም የጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ተወካዮች እንዳልተሳተፉ ተገልጿል።
ሱዳን ትሪቢዩን የተባለው የሱዳን ጋዜጣ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዥ ጄኔራል አል ቡርሐን አዲስ አበባ በሚደረገው ውይይት ላይ እርሳቸውም ሆኑ ተወካያቸው አይገኝም ሲል ቀደም ብሎ ዘግቧል።
- በአዲስ አበባ ድርድር በታሰበበት ጊዜ በካርቱም በተፈጸመ የአየር ጥቃት ቢያንስ 22 ሰዎች ተገደሉ9 ሀምሌ 2023
- በጀርመን የኤርትራ ፌስቲቫል ላይ በተከሰተ ግጭት 26 ፖሊሶች ሲጎዱ 100 ኤርትራውያን ታሰሩ9 ሀምሌ 2023
- የአገሪቱ ባለሥልጣናት መነጋገሪያ የሆነው ከነፍሳት የሚሠራው የጣልያን ፓስታ10 ሀምሌ 2023

ጋዜጣው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ ባወጣው ዘገባ አል ቡርሐን ወይም ተወካያቸው በአዲስ አበባው ንግግር ላይ የማይገኙት፣ የኢጋድ የወቅቱ ሰብሳቢ የሆኑት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ካላቸው ቅርበት የተነሳ በሱዳን ጉዳይ ገለልተኛ አይደሉም በሚል ምክንያት ነው።
ጋዜጣው ጨምሮ ኢጋድ አዲስ አበባ ላይ በጠራው ስብሰባ የኢትዮጵያ፣ የጂቡቲ፣ የኬንያ እና የደቡብ ሱዳን መሪዎች ይገኛሉ ብሏል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሞሊ ፊ ሰኞ ሐምሌ 3 እና ማክሰኞ ሐምሌ 4/2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቆይታ እንደሚኖራቸው ገልጾ፣ በሱዳን ግጭት የአሜሪካ ግልጽ አቋም ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሄ አማራጭ አይደለም የሚል ነው ብሏል።
የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱብ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጉዞ ይፋ ባደረገበት መግለጫው፣ የአካባቢው አገራት ለየትኛውም ወገን ወታደራዊ ድጋፍ በማድረግ በሱዳን ግጭት ጣልቃ እንዳይገቡ አሳስቧል።
የካይሮ ቀጠሮ
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብፅ ሁለቱን ተፋላሚ ኃይሎች የፊታችን ሐሙስ ካይሮ ላይ ጠርቼ አደራድራለሁ ብላለች።
በቀጠናው የጄኔራል አል ቡርሐን ጠንካራ ደጋፊ እንደሆነች የምትገመተው ግብፅም ሆነች የጄኔራል ዳጋሎ የቅብር ወዳጅ የምትባለው የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ሁለቱን ወገኖች ለማደራደር ይፋዊ ጥያቄ እስካሁን አላቀረቡም።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በጂዳ ሁለቱን የጦር ጄኔራሎች ለማግባባት ጥረት ሲያደርጉ ካይሮ እና አቡ ዳቢ ተሳታፊ አልነበሩም።
የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ካይሮ ላይ የታሰበው ውይይት ዓላማ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለመ ነው።

ከዚህ ቀደም ግጭት ውስጥ የገቡትን የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ የሆኑትን ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ለማግባባት የተደረጉ ተደጋጋሚ ጥረቶች ፍሬ አላፈሩም።
አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ ተፋላሚ ኃይሎቹ በተደጋጋሚ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ ማድጋቸው ቢገልጽም ይህ ግባራዊ ሳይሆን ውጊያው ቀጥሏል።
ሦስት ወር ሊደፍን የተቃረበው ግጭት በተለይ የሱዳን መዲና ካርቱም ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከትቶ ይገኛል። ሁለቱም ኃይሎች ዋና ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ለማስገባት እየተፋለሙ ነው።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የካርቱምን፣ የኦምዱርማንን እና የባህር ዳርቻ ከተሞችን አብዛኞቹን ክፍሎች ተቆጣጥሮ ይገኛል።
የእርስ በርስ ጦርነቱ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብን ከመኖሪያው ያፈናቀለ ሲሆን፣ 700 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አገር ጥለው ተሰደዋል።