ጁላይ 10, 2023


ፋይል - በሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ግጭት በቀጠለበት ወቅት በሱዳን፣ ካርቱም ጭስ ሲወጣ ይታያል። ሰኔ 8፣ 2023
ፋይል – በሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ግጭት በቀጠለበት ወቅት በሱዳን፣ ካርቱም ጭስ ሲወጣ ይታያል። ሰኔ 8፣ 2023

በሱዳን ያለው ግጭት ሙሉ ለሙሉ ወደ የእርስ በእርስ ጦርነት እያመራ መሆኑ እና ይህም ቀጠናውን ወደ ትርምስ ሊወስድ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አስጠንቅቀዋል።

ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ትናንት ማስጠንቀቂያውን የሰጡት ቅዳሜ ዕለት በተፈጸመ የአየር ጥቃት 22 ሲቪሎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ተከትሎ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ 3ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ጦርነት የሚቆምበትን መላ ለመሻት፣ የኢጋድ አባላት የሆኑት የኢትዮጵያ፣ ኬን ያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን መሪዎች፣ የልማት በይነ መንግስታቱ ጉዳዩን እንዲከታተሉ በሰጣቸው ሃላፊነት መሠረት በጉዳዩ ላይ ሊመክሩ አዲስ አበባ ላይ ዛሬ ስብሰባ መቀመጣቸው ታውቋል።

የቅዳሜው የአየር ጥቃት የካርቱም እህት ከተማ በሆነችው ኦምዱርማን እንደደረሰ ሲታወቅ፣ ትናንት እሁድም በካርቱም በሚገኘው የፕሬዝደንቱ ቤ/መንግስት አካባቢ እና በኦምዱርማን ተፈጽሞ እንደነበር የዓይን ምስክሮችን ጠቅሶ የኤኤፍፒ ዜና ወኪል ዘግቧል።

ጉቴሬዝ የአየር ጥቃቶቹን ማውገዛቸውን ምክትል ቃል አቀባያቸው የሆኑት ፋርሃን ሃቅ አስታውቀዋል።

ሁለቱ ተፋላሚ ጄኔራሎች፣ የጦር ሠራዊቱ አዛዥ የሆኑት አብደል ፋታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ አዛዥ ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ቢጋበዙም አለመገኘታቸው ታውቋል።