
ከ 4 ሰአት በፊት
በመቶዎች በሚቆጠሩ አትሌቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈጸም እስር ላይ የሚገኘው የቀድሞ የአሜሪካ ብሔራዊ የጂምናስቲክ ቡድን ዶክተር ላሪ ናሳር በስለት ተወጋ።
ዶክተሩ በፍሎሪዳ በሚገኘው እስር ቤትም ቢያንስ 10 ጊዜ በስለት ተወግቷል ተብሏል።
ላሪ የጂምናስቲክ ስፖርተኞቹ ላይ ባደረሰው ጥቃት 175 ዓመታት ተፈርዶበት በእስር ይገኛል።
ጥቃቱም የተፈጸመበት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሌላ እስረኛ ነው።
ዶክተሩ በአሁኑ ወቅት በሆስፒታል ውስጥ እንደሚገኝ የተጠቆመ ሲሆን ሳንባው ከጥቅም ውጭ ሆኗል ተብሏል።
የ59 ዓመቱ ዶክተር በአትሌቶች ላይ በፈጸማቸው የወሲባዊ ጥቃቶች እንዲሁም ከሕጻናት ጋር የተያያዙ ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን ቪዲዮዎች ይዘው በመገኘታቸው ነው ለእስር የተዳረገው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ከሳሾችም ቀርበዋል።
ዶክተሩ ሁለት ጊዜ አንገቱ ላይ፣ ሁለት ጊዜ ጀርባው ላይ እና ስድስት ጊዜ ደረቱ ላይ እንደተወጋም የማረሚያ ቤቶች ማኅበር መሪ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ቢሮ እሁድ ከቀኑ 8፡30 ላይ ፍሎሪዳ በሚገኘው ኮልማን በተሰኘው እስር ቤት አንድ ታራሚ ጥቃት እንደደረሰበት አረጋግጧል።
- በአሜሪካ ታዋቂ አትሌቶች የወሲብ ጥቃቶችን ችላ በማለት ኤፍቢአይን ሊከሱ ነው9 ሰኔ 2022
- ዶክተሩ ለፈፀመው ጥፋት 175 ዓመት ተፈረደበት25 ጥር 2018
- ወሲባዊ ይዘት ካላቸው ፎቶዎች ጋር በተያያዘ በታገዱት ጋዜጠኛ ዙሪያ የቢቢሲ ኃላፊ ምላሽ እንደሚሰጡ ተጠቆመከ 6 ሰአት በፊት
በጉዳዩ ላይ የውስጥ ምርመራ የተጀመረ ሲሆን በጥቃቱ ሰራተኞችም ሆነ ሌሎች እስረኞች አልተጎዱም ብሏል።
ዶክተር ላሪ የአሜሪካ ብሔራዊ የጂምናስቲክ ፕሮግራም አካል እንዲሁም በሚቺጋን ዩኒቨርስቲ ይሰራ በነበረበት ወቅት በአትሌቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት መፈጸሙን አምኗል።
በጂምናስቲክና በዩኒቨርስቲው ፕሮግራም ውስጥ የነበሩ ከ330 በላይ ሴቶች እና ታዳጊዎች ዶክተሩ ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሰባቸው ክሳቸውን አሰምተዋል።
ከነዚህም መካከል የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚዎቹ ሲሞን ባይልስ፣ አሊ ሬይስማን እና ማኬይላ ማሮኒ ይገኙበታል።
አንዳንድ ታዳጊ አትሌቶችም እየደረሰባቸው ያለውን ጥቃት አሰልጣኞች እና ዶክተሮችን ጨምሮ ለአዋቂዎች ቢናገሩም ከቁብ እንዳልቆጠሯቸው ተናግረዋል።