የሉትዌኒያ ፕሬዚደንት ጊታናስ ናውሴዳ ( በቀኝ) የኔቶ ዋና ጸሐፊ ጀንስ ስቶልተንበርግ
የምስሉ መግለጫ,የሉትዌኒያ ፕሬዚደንት ጊታናስ ናውሴዳ ( በቀኝ) የኔቶ ዋና ጸሐፊ ጀንስ ስቶልተንበርግ እና የአባላት አገራቱን መሪዎች እያስተናገዱ ነው።

ከ 5 ሰአት በፊት

የሰሜን የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መሪዎች በዩክሬን ያለውን ጦርነት አቅጣጫ ቅርፅ ለማስያዝ እና የምዕራባውያን ኅብረት የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ለመምከር በሉቱዌኒያ እየተሰባሰቡ ነው።

ሰላሳ አንዱ የኔቶ አባላት የዩክሬንን ጦር ዘላቂነት ባለው መልኩ ለመርዳት ቁርጠኛ እንደሆኑ ለሩሲያ ለማሳየት ተስፋ አድርገዋል።

መሪዎቹ ለጉባኤው እየተሰባሰቡ ያሉት ቱርክ ስዊድን ኅብረቱን ለመቀላቀል ያቀረበችውን ጥያቄ ለመደገፍ ከተስማማች በኋላ ነው።

ሆኖም ዩክሬን ወደፊት ኅብረቱን ለመቀላቀል ያላት ፍላጎት ላይ አሁንም አለመግባባቶች አሉ።

አንዳንድ የኅብረቱ አባላት ኪዬቭ ወደፊት ሩሲያ የምታደርግባትን ወረራ ለመከላከል አዲስ የጸጥታ ዋስትና እንደሚሰጧት ይታሰባል። ከዚህም በተጨማሪ የጦር መሣሪያ እና ጥይት ለመስጠት እንደሚወያዩም ይጠበቃል።

የአባልነት ጥያቄውን በተመለከተ የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜለንሰኪ፣ መቼ እና እንዴት እንደሚሳካ በመግለጽ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ በተቻለ ፍጥነት አገራቸው ኅብረቱን መቀላቀል እንደምትችል ኔቶ እንዲፈቅድላት ይፈልጋሉ።

ሆኖም የተወሰኑ የኔቶ አባል አገራት፣ የሚገቡት ቃል ሩሲያ ጦርነቱን ለማባባስ እና ጦርነቱ ለማጓተት እድል ሊሰጣት ይችላል ሲሉ በሃሳቡ ብዙም አልገፉበትም።

የኔቶ ዋና ጸሐፊ ጀንስ ስቶልተንበርግ፣ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ አለመሰጠቱን ገልጸው ነገር ግን “ አንድነት እና ለዩክሬን ጠንካራ መልዕክት እንደሚኖረን እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል።

ዋና ጸሐፊው ሰኞ ዕለት ስዊድን ኔቶን ለመቀላቀል ያቀረበችውን ማመልከቻ ለመደገፍ ቱርክ መስማማቷን አስታውቀዋል። ይህ ዜናም በአሜሪካ እና ጀርመን እንዲሁም በስዊድን በራሷ ተቀባይነትን አግኝቷል።

ቱርክ ስቶክሆልም የኩርድ ታጣቂዎችን ትደግፋለች እንዲሁም በስቶኮልም ጎዳና ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ ፈቅዳለች ስትል ማመልከቻዋን ሳትቀበል ቆይታ ነበር።

ዋና ጸሐፊው እንዳሉት ሁለቱም ወገኖች ቱርክ ያለባትን ሕጋዊ የሆነ የጸጥታ ስጋት ለመፍታት አብረው ሰርተዋል ብለዋል።

ቀደም ብሎም የቱርኩ ፕሬዚደንት ሬሲብ ታይብ ኤርዶዋን አገራቸው ወደ አውሮፓ ኅብረት እንድትገባ የሚፈቀድላት ከሆነ ስዊድንን እንደሚደግፉ ሃሳብ አቅርበው ነበር።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ የኔቶ መሪዎች በምሥራቅ አካባቢ የሚገኙ ኃይሎቻቸውን በማጠናከር አባል አገራቱን ከወደፊት የሩሲያ ጥቃት ለመከላከል የሚረዳ አዲስ እቅዶች ላይ ከስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህም ባሻገር ከአገራቱ ኃብት 2 በመቶ የሚሆነው ለመከላከያ እንዲውል መስማማት ይጠበቅባቸዋል።

የሪሺ ሱናክ ቃል አቀባይ፣ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን ዓላማ ለማሳካት ለአጋሮች ጥሪ ያደርጋሉ ብለዋል።

የአገራቱ መሪዎች በተሰባሰቡባት ቪልኒየስ የጸጥታ ሁኔታ በአየር መከላከያ ሚሳይሎች ጨምሮ በኔቶ ኃይሎች ጥብቅ ተደርጓል።

የስብሰባው ዓላማም ኔቶ በዩክሬን ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የጦር ድጋፍ እንደሚያደርግ የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲንን ለማሳመን ነው።

ይህም የፑቲንን አስተሳሰብ መለወጥ ሊጀምር ይችላል ብለው ባለሥልጣናት ተስፋ አድርገዋል።

በመሆኑም አንዳንዶች ፑቲን ስትራቴጂያቸውን እንዲቀይሩ ለማሳመን በጦር ሜዳ ያገኙት ወታደራዊ ድሎች ያህል ይህ የመሪዎች ጉባኤ ጠቃሚ እንደሆነ ይመለከቱታል።

የኔቶ መለያ ሰንደቅ ዓላማ

የሰሜን አትላቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ወይም ኔቶ በአውሮፓውያኑ 1949 ላይ በ12 አገራት ነበር የተመሰረተው። በወቅቱ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ያካትት ነበር።

አባል አገራት ወታደራዊ ጥቃት ከደረሰባቸው እርስ በርሳቸው ለመደጋገፍ ነው ይህንን ስምምነት የተፈራረሙት።

አባል አገራት ከዚህ ስምምነት የደረሱት የሶቪየት ሕብረት አውሮፓ ውስጥ የመስፋፋት እቅድን ለመከላከል ያለመ ነበር።

እአአ 1955 ላይ ሶቪየት ደግሞ ለዚህ ስምምነት ምላሽ በሚመስል መልኩ የምሥራቅ አውሮፓ ኮምዩኒስት አገራት ጥምረት የሆነውን ‘የዋርሶ ስምምነት’ የተሰኘ ስብስብ አቋቋመች።

ነገር ግን እአአ 1991 ላይ የሲቪየት ሕብረት መፍረስን ተከትሎ በርካታ የዋርሶ ስምምነትን የፈረሙ አገራት ድርጅቱን እየለቀቁ ኔቶን መቀላቀል ጀመሩ።

በአሁኑ ወቅት ኔቶ 31 አባል አገራት አሉት። እነዚም የሚከተሉት ናቸው፡

ፊንላንድ፣አልባኒያ፣ ቤልጂየም፣ ቡልጋሪያ፣ ካናዳ፣ ክሮሺያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ኢስቶኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ሃንጋሪ፣ አይስላንድ፣ ጣሊያን፣ ላቲቪያ፣ ሊቱዌኒያ፣ ላክሰዘምበርግ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሰሜን መቄዶኒያ፣ ኖርዌይ፣ ፖላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ሩሜኒያ፣ ስሎቫኪያ፣ ስሎቬኒያ፣ ስፔን፣ ቱርክ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ናቸው።