ዶ/ር እውነቱ ኃይሉ
የምስሉ መግለጫ,ዶ/ር እውነቱ ኃይሉ

ከ 7 ሰአት በፊት

ዶ/ር እውነቱ ኃይሉ ትውልድ እና እድገታቸው ገጠር ነው።

ተወልደው ባደጉበት የገጠር መንደር ቤተሰባቸውን በጉልበት እየረዱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።

ከዚያም በትውልድ አካባቢያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት ስላልነበረ፣ ወደ አምቦ በመሄድ እዚያ ከሚገኝ ዘመድ ጋር ተጠግተው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመከታተል ሞክረዋል።

ነገር ግን ዶ/ር እውነቱ ከዘመድ ዘንድ ተጠግተው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል የቻሉት የመጀመሪያውን ዓመት ብቻ ነበር።

“አንድ ዓመት ዘመዶቼ ቤት ሆኜ ተማርኩ” የሚሉት ዶ/ር እውነቱ፣ ነገር ግን የጉርምስና ዕድሜ ባህሪይ ከዘመድ ቤት ብዙ እንዲቀመጡ እንዳላደረጋቸው ያስታውሳሉ።

ሌሎች አቻዎቻቸው ያላቸውን ነጻነት የተመለከቱት ዶ/ር እውነቱ፣ ዘመድ ጋር ጥገኛ ከመሆን ይልቅ ከቤተሰባቸው ስንቅ እየተላከላቸው ከሚኖሩ ተማሪዎች ጋር ለመዳበል በማሰብ ነበር ካስጠጓቸው ዘመዶቻቸው የተለዩት።

ይህ የሆነው በደርግ ዘመን በ1970ዎቹ መጨረሻ ላይ ነበር። ይህ ውሳኔያቸው በሕይወት ጉዟቸው ላይ የገጠሟቸው ፈተናዎች ጅማሬ ነበር።

“ከዘመድ ቤት ከወጣሁ በኋላ አብሬያቸው የምኖረው ልጆች ስንቅ ከቤተሰብ ነው የሚያመጡት። የእኔ ቤተሰብ እሩቅ በመሆናቸው ስንቅ የሚያመጣልኝ የለም። በዚህም የነበረኝ አማራጭ ሁለት እንደሆነ ተረዳሁ” ይላሉ፤ እነሱም ትምህርታቸውን መቋረጥ ወይም ያገኙትን እየሰሩ እራስን ማስተማር የሚለ አማራጮች።

ትምህርት፣ የጉልበት ሥራ፣ ጥበቃ

ዶ/ር እውነቱ በዚያ ዘመን የነበሩበት ሁኔታ ኑሮን ከባድ ቢያደርግባቸውም ለትምህር ካላቸው ፍቅር የተነሳ በትምህር ገበታቸው መቆየታቸውን ይገልጻሉ።

በተጨማሪም ታታሪ ተማሪ ስለነበሩ በትምህርታቸው ከፍተኛ የሚባል ውጤት እያስመዘገቡ በክፍላቸው ተፎካካሪ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል ነበሩ።

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በድግሪ መመረቅ ደግሞ ገና ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ የያዙት ትልቅ ሕልም ነበር።

“ዩኒቨርሲቲ መግባት ወይም ሞት” የሚል ጠንካራ አቋም እንደነበራቸው ጭምር ይናገራሉ።

በእራሳቸው ኑሮን በመግፋት ትምህርታቸውን ለመቀጠል በመቁረጣቸው፣ ሕይወት ፈታኝ ብትሆንባቸውም ትምህርታቸውን ማቋረጥ ግን ፈጽሞ አማራጫቸው አልነበረም።

“የነበረኝ አማራጭ የጉልበት ሥራ እየሰራሁ እራሴን ማስተማር ነው። በዚያ ዘመን የጉልበት ሠራተኛ ለአንድ ቀን ውሎ የሚከፈለው ሁለት ብር ነበር። ሙሉ ቀን ከሰራሁ ሁለት ብር ይከፈለኛል። ግማሽ ቀን ትምህር ቤት ሄጄ ግማሽ ቀን ከሰራሁ ደግሞ አንድ ብር ይከፈለኝ ነበር።”

ዶ/ር እውነቱ የጉልበት ሥራን ከትምህርት ጎን ለጎን ማስኬድን ቀላል ሆኖ አላገኙትም። የጉልበት ሥራ ከባድ ሆነ። ስለዚህ ከቀን ሠራተኝነት ቀለል ያለ ሥራ መፈለግን ተያያዙ። ሌላ የነበረው አማራጭ የጥበቃ ሥራ ሆነ።

“የዚያን ጊዜ 10ኛ ክፍልን ገና መጨረሴ ነበር። ዘመኑ የደርግ ዘመን ነበር። አምቦ በዚያ ጊዜ ስድስት ቀበሌዎች ብቻ ነበሯት። እኔ የቀበሌ 5 ጽህፈት ቤት ዘበኛ ሆኜ ተቀጠርኩ። ደሞዜ በወር 50 ብር ነበር” ይላሉ።

ዶ/ር እውነቱ

የጨነገፈው ሕልም

ዶ/ር እውነቱ የ05 ቀበሌ ዘበኛ ሆነው መቀጠራቸው ለትምህርት የተመቸ ሆኖ አገኙት። የሥራ ሰዓታቸው ለሊት መሆኑ ቀን ለትምህርታቸው ሙሉ ትኩረት እንዲሰጡ ዕድልን ፈጠረላቸው።

በዚህ መካከል በትውልድ ቀያቸው ካለች ልጅ ፍቅር ይይዛቸዋል፤ በዚያም አላበቃም የሕይወት ዘመናቸውን ውሃ አጣጭ አግኝተው ወደ ሌላኛው የሕይወት ገጽ ወደ ትዳር ገቡ።

“የዘበኝነት ሥራውን ሳገኘ ደሞዝተኛ ነኝ ብዬ ከገጠር የወደድኳትን ልጅ አሳምኜ ወደ አምቦ ይዢያት ገባሁ። በአምቦ እኔ እየተማርኩ ዘበኝነት እየሰራሁ፣ እሷ ደግሞ የቀን ሥራ እየሰራች ሕይወት ቀጠለ” በማለት ከበርካታ ዘመናት በፊት የነበረው ያስታውሳሉ።

ዶ/ር እውነቱ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ደግሞ ያላቀዱት ሌላ ነገር ተከሰተ። የመጀመሪያ ልጃቸው ተወለደች። “አሁን ነገሮች ሁሉ እየበረቱ መጡ። በጥበቃ ሥራ ላይ ትምህርት እያለብኝ ልጅ ተጨመረበት” በማለት ውጥረቱን ያስታውሱታል።

ዶ/ር እውነቱ በወጣትነት ዕደሜያቸው የገጠማቸው ፈተና በትምህርታቸው ላይ ጫና ማሳደሩ አልቀረም። ቀደም ሲል እንደነበረው በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ቀረ።

በዚህም ምክንያት በወቅቱ የነበረው ከፍተኛ ፉክክር የነበረበትን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ የብሔራዊ ፈተናን (ማትሪክ) አልፎ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ሕልማቸው ጨነገፈ።

የማትሪክ ፈተናን ወደቁ። ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲያልሙት የነበረው፣ ከባድ ኃላፊነትን በመሸከም ሲጥሩለት የነበረው 12ኛ ክፍልን አልፎ ዩኒቨርስቲ የመግባት ዋነኛ ዕቅዳቸው ተሰናከለ።

በዚህም ሳቢያ መጪው ጊዜ ጨለማ የሆነባቸው ያህል ተሰማቸው፣ ተስፋ መቁረጥ ወረራቸው “ዋነኛው ሕልሜ ሲጨናገፍ መኖርን ሁሉ አስጠልቶኝ ነበር” የተፈጠረባቸውን ከባድ ስሜት ሲያስታውሱ።

ሕልምን ዕውን ለማድረግ ሌላ ጥረት

ዶ/ር እውነቱ በሕይወት አጋጣሚ ዋነኛው የሕይወት ውጥናቸው ቢጨናገፍም፣ እንደገና እንዲያንሰራራ ማድረግ እንዳለባቸው በማመን በሌላ በኩል ጥረት ማድረግ ጀመሩ።

“ነጥብ ሳይመጣልኝ ሲቀር ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ ጊዜ ወስጄ አሰብኩ። ከዚያ በኋላ ወደ መምህራን ማሠልጠኛ ተቋም ለመግባት ተወዳድሬ አለፍኩ። ለአንድ ዓመት ያህል ሥልጠና ወስጄ መምህር ሆንኩ።”

ነገር ግን የዶ/ር እውነቱ የትምህርት ጉዞ ገና አላበቃም ነበር። ከመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም ተመርቀው በመውጣት ሥራ ከጀመሩ በኋላም እራሳቸውን በትምህርት ለማሻሻል ጥረታቸውን ገፉበት።

በመምህርነት በምስክር ወረቀት ተመርቀው ሥራ ከጀመሩ በኋላም፣ በትምህርታቸውን ቀጥለው በዲፕሎም ተመረቁ።

ጥረታቸውንም ገፍተውበት ከስምንት ዓመታት በኋላ በልጅነታቸው ለማሳካት ሲመኙት የነበረውን ዩኒቨርሲቲ የመግባት ጽኑ ሕልም እውን በማድረግ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ።

“ከ12ኛ ክፍል በቀጥታ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት ስችል በራሴው መዘናጋት ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ስምንት ዓመት መጠበቅ ግድ ሆኖብኝ ነበር። ቢሆንም ግን ከምስክር ወረቀት በመጀመር ዲፕሎማ ይዤ ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት ችያለሁ” በማለት ተስፋ አለመቁረጣቸው ካሰቡት ደረጃ ላይ ለመድረስ እንደረዳቸው ይናገራሉ።

አሁንም የዶ/ር እውነቱ የትምህርት ጉዞ አልተጠናቀቀም ነበር። ዩኒቨርስቲ ገብተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ረዳት መምህር ሆነው ሥራ ጀመሩ።

ቀጥለው ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አገኙ በማስከትልም ለዶክትሬት ዲግሪ ትምህርት ወደ ውጭ አገር ተጉዞው፣ የትምህርት ጥማታቸውን እና ሕልማቸውን ከአገራቸው ባሻገር በውጭ አገርም ለማሳካት በቁ።

ዶ/ር እውነቱ

ከረዥም ውጣ ውረድ በኋላ የመጣ ስኬት

የትምህርት ሕይወታቸው በፈተናዎች የተሞላው ዶ/ር እውነቱ፣ ተስፋ መቁረጥን በማሸነፍ የልጅነት ምኞታቸውን ዕውን ለማድረግ በቅተዋል።

በዚህም ላለፉት 18 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ስመ ጥር ከሚባሉት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በሚመደበው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተመራማሪ እና መምህር ሆነው አገልግለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ የራሳቸውን ድርጅት በመመሥረት የግል ሥራንም ይሰራሉ።

“ትናንት ያ የቀበሌ ዘበኛ የነበረው ሰው ዛሬ መምህር፣ ተመራማሪ እና ለትውልድ መንግድ የሚጠቁም ሆኗል” ይላሉ ዶ/ር እውነቱ፣ ይህንንም የሕይወት ጉዟቸውን የሚያሳይ ‘ኡቡንቱ’ የተባለ መጽሐፍ አሳትመዋል።

ሰዎች ካለሙት ስኬት ለመድረስ “እቅዳቸውን 1፣ 2፣ 3 ብለው ለይተው ማስቀመጥ አለባቸው። ይህንንም መሠረት በማድረግ የመጀመሩትን ከፍጻሜ ማድረስ ይኖርባቸዋል። ያለንን ትተን ወደ ሌላ ከተሻገርን በኋላ የአእምሮ እረፍት ይነሳናል” ይላሉ ዶ/ር እውነቱ።

አክለውም ለስኬታችን መሳካት ትዕግስት ቁልፍ ነገር ነው የሚሉት ዶ/ር እውነቱ “እኔ ማትሪክ በመውደቄ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት 8 ዓመት ነው የፈጀብኝ። ያንን ጊዜ በትዕግስት ባላሳልፈው ኖሮ አሁን ካለሁበት ደረጃ አልደርስም ነበር።”

ዶ/ር እውነቱ የ11ኛ ክፍል ተማሪ እና የቀበሌ ዘበኛ ሳሉ የወለዷት የመጀመሪያ ልጃቸው ዛሬ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ እንደሆነች ይናገራሉ።