
ከ 1 ሰአት በፊት
ለሁለት ዓመታት የቆየውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም የቋጨው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ጉልህ ክፍተቶች እንዳሉበት ‘አፍሪካንስ ፎር ዘ ሆርን’ የተሰኘ የሲቪል ማኅበረሰብ ጥምረት አስታወቀ።
ከስምንት ወራት በፊት በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ የተደረሰውን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነትን የገመገመው ይህ ተቋም ከፀጥታ፣ ከሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲሁም ከሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ አንጻር መሻሻል ቢኖርም ሰላሙን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ክፍተቶች እንዳሉበት ተመልክቷል።
25 ገጾችን በያዘው እና የበርካታ ሰዎች ቃለ መጠይቅ እንዲሁም የተለያዩ ሕዝባዊ መረጃዎች በተካተቱበት በዚህ የሰላም ስምምነቱ ግምገማ ሪፖርት የታዩ ጉልህ ክፍተተቾን እንዲሁም ምክረ ሃሳቦች ቀርበዋል።
ሪፖርቱ እነዚህ ጉልህ ክፍተቶች የታዩት አንዳንዶቹ ከስምምነቱ ውስንነት የመነጩ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በአፈጻጸሙ ላይ በታዩ ጉድለቶች መሆኑን አስፍሯል።
በትግራይ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያ እና የአካል ጉድለቶችን ያስከትል የነበረው ውጊያ ቢቆምም “በውጭ ኃይሎች” በተያዙ አካባቢዎች አሁንም የሰላማዊ ዜጎች ደኅንነት አደጋ ላይ ወድቋል ብሏል።
እነዚህም በኤርትራ ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች እና የአማራ ኃይሎች በሚቆጣጠሩት የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች መሆኑም ተጠቅሷል።
ከሰላም ስምምነቱም በኋላ በምዕራብ እና ደቡባዊ ትግራይ አካካቢዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ሪፖርቶች መውጣት መቀጠላቸውን የጠቆመው ይህ ሪፖርት፣ እነዚህ ስፍራዎች ገለልተኛ የሆኑ ተቆጣጣሪዎች የማይደርሱባቸው ስፍራዎች መሆኑንም ተመልክቷል።
በትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ የኤርትራ ወታደሮች በሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አላቸው ብሏል።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትና የናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሠረት የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያ መፍታት የሚካሄደው የውጭ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከትግራይ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ሆኖም በክልሉ ያሉት የኤርትራ እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ ክልል አለመውጣታቸው እና በክልሉ በሚፈጸሙ ጥሰቶችም ስማቸው ሲጠቀስ ይሰማል።
የትግራይ እና አማራ ክልል የሚወዛገቡባቸው ስፍራዎች ለዘላቂ ሰላም ቁልፍ ቢሆኑም ከፕሪቶሪያው ስምምነት ወሰን ውጪመደረጋቸውንም ገልጿል።
ሌላኛው ሪፖርቱ እንደ ክፍተት ያየው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ጉዳይ ነው። እነዚህ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው እንዳልተመለሱ እና ያለባቸውን አንገብጋቢ ችግር ላይ የግንዛቤ ችግር እንዳለ ጠቅሶ ሕጋዊ መብት እንደሌላቸው አስፍሯል።
በአሁኑ ወቅት ሕጋዊ ከለላን ጨምሮ ከፍተኛ ድጋፍ እና ጥበቃ በሚያስፈልጋቸው ሁኔታ ላይ ናቸው ተብሏል።
በትግራይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ተቋርጦ የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች ቢጀመሩም ከጤና እና ከትምህርት ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች አሁንም በተገቢው መልክ እየተሰጡ እንዳልሆነ እና የኢንቨስትመንት ግንባታ ሊደረግላቸው ይገባል ብሏል።
ሌላኛው ሪፖርቱ እንደ ክፍተት ያየው በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ጥቅምት መጨረሻ ላይ የተደረሰው ስምምነት የአፍሪካ ኅብረት ክትትል፣ አረጋጋጭ እና አስከባሪ የባለሙያዎች ቡድን ዋነኛ አካል የሥልጣን ሁኔታን ነው።
በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነትን የሚቆጣጠረው የአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪ የባለሙያዎች ቡድን እየተፈጸሙ ያሉ ጥሰቶችን በይፋ ሪፖርት የሚያደርግበት ሥልጣን እንደሌለው እና በቂ የሰው ኃይል አለመኖሩም ሪፖርት እንደ አንድ ክፍተት ተመልክቶታል።
- የኢትዮጵያን የሰላም ስምምነት የሚቆጣጠረው የአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪ ቡድን ቆይታ ተራዘመ8 ሰኔ 2023
- የናይሮቢው የትግበራ ዝርዝር ሰነድ ምን አካቷል?13 ህዳር 2022
- “ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በምዕራብ ትግራይ የዘር ማጽዳት እየተካሄደ ነው” ሂዩማን ራይትስ ዋች1 ሰኔ 2023
የአፍሪካ ኅብረት የስምምነት ክትትል፣ አረጋጋጭ እና አስከባሪ ኮሚቴም የሰላሙን አፈጻጸም አስመልክቶ እንዲከታተል ስምምነት ላይ የተደረሰው ለስድስት ወራት ቢሆንም፣ እስከ ቀጣይ ዓመት ታኅሣሥ ድረስ መራዘሙ ይታወሳል።
ኮሚቴው የስምምነቱ አንድ አካል የሆነውን ትጥቅ ማስፈታት፣ ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋም ሂደት በጥሩ መልክ መከናወኑን ከዚህ ቀደም አስታውቋል።
ሪፖርቱም የትግራይ ኃይሎች መሳሪያ በማስረከቡ ሂደት ጥሩ እመርታ ቢኖርም፣ ከመልሶ ማቋቋም ጋር የተያያዙ የአእምሮ ጤና እና የሥነ ልቦና አገልግሎት ጋር ውስንነት እንዳለውም ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በወሳኝ ሁኔታ በጦርነቱ ክፉኛ የተጎዱ ሴቶች እና ማኅበረሰቦች የሰላም ሂደቱ አካል ባለመሆናቸው የበለጠ እየተጎዱ እንደሆነም አስፍሯል።
ሰፊ የትግራይ ቦታዎች አሁንም የገለልተኛ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ጋዜጠኞች መድረስ ባለመቻላቸው የሰላማዊ ዜጎች ጥበቃና እና ሁኔታ መሉ በሙሉ መገምገም አለመቻሉም ተመልክቷል።
በተለይም የምዕራብ ትግራይ እና ደቡብ ትግራይ እንዲሁም በኤርትራ ቁጥጥር ስር ባሉ ሰሜናዊ የትግራይ አካባቢዎች መረጃ ማሰባሰብ አስቸጋሪ ነው ብሏል። የአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪ ቡድን በቸረነዚህ ስፍራዎች እንዳይደርሱም መከልከላቸው ተገልጿል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ በተከተሰው ጦርነት ከፌደራል መንግሥቱ ጎን በመቆም ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የአማራ እና የአፋር ክልል ኃይሎች እንዲሁም የኤርትራ ኃይሎች የሰላም ስምምነቱ አካል ባለመሆናቸው የስምምነቱን ውስንነትን ያሳየ እና ለዘላቂ ሰላም ጠንቅም ነው ብሏል ሪፖርቱ።
ጦርነቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ከመዛመቱ አንጻር በፕሪቶሪያው ስምምነቱ ከተካተቱት በተጨማሪ ሌሎች የጦርነቱ ተሳታፊ አካላትን በሰላም ስምምነቱ ሊካተቱ ይገባ ነበር ብሏል።
የሰላም ስምምነት ውስንነቱን አመላካች መሆኑ ከጠቆመው አንዱ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የቀጠሉ ግጭቶች እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉ የመብት ጥሰቶች መሆናቸውን ነው።
ግጭት የማቆም ዘላቂ ስምምነቱ ሁሉንም የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት እስካላካተተ ድረስ ሙሉ በሙሉ ሰላም ሊያረጋግጥ እንደማይችልም ጠቁሟል።
ተቋሙ ያልተቋረጠ እና ዘላቂ በጦርነቱ ለተጎዱ ሰዎች እንዲደርስ በማድረግ እና ዝርፊያዎችን በመከላከል የገቡትን ቁርጠኝነት እንዲያከብሩ ማሳሰብ እና ለተፈናቃይ ዜጎች የፖሊሲ ማዕቀፍ አውጥቶ ሕጋዊ እውቅና መስጠትን ጨምሮ ሌሎች ምክረ ሃሳቦችን ለግሷል።
የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ በሰላማዊ ዜጎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየፈጸሙ ያሉ ኃይሎች “መኖራቸውን እንዲሁም እየደረሰ ያለውን ጥቃት በማያሻማ ሁኔታ ሊያወግዝ ይገባል” ብሏል።
በተጨማሪም “የኤርትራ ኃይሎች የኢትዮጵያን ግዛቶች ለቀው እንዲወጡ ጥሪ ማድረግ እንደሚገባውም” አስቀምጧል።
የአፍሪካ ኅብረት የክትትል ቡድኑ እያጋጠሙት ስላሉት ተግዳሮቶች ግልጽነት ባለው መልኩ ይፋ እንዲያደርግና እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰቦችም የሚካተቱበት ማዕቀፍ እንዲፈጠር ጠይቋል።
በተጨማሪም ኅብረቱ በሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚ ያልሆኑ ጉዳዮችን በተመለከተ የክትትል ቡድኑ በይፋ እንዲናገር ሥልጣን እንዲኖረው እንዲያደርግም ጥሪ አቅርቧል።
ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን የቀጠፈውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ከስምንት ወራት በፊት መደረሱ ይታወቃል።
የሰላም ስምምነት መሠረት ለትግራይ ያልተገደበና ያልተቆራረጠ ሰብዓዊ እርዳታ፣ በትግራይ ለሁለት ዓመት የተቋረጠው መጀረታዊ አገልግሎት እንዲመለስ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን በመፍታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለመ ነው።
ሪፖርቱን ያወጣው አፍሪካንስ ፎር ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ የተባለው ተቋም የአፍሪካ ቀንድን እያመሷት ያሉ ቀውሶች ምላሽ እና አፈታት ለማሳደግ፣ የዜጎችን ድምጽ ለማጉላት፣ የተቋቋመ ተቋም መሆኑን በድረገ ገጹ ላይ አስፍሯል።
ተቋሙ ሰላምን ማዕከል በማድረግም በዋናነት የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን ከመንግሥታት፣ አገር አቀፍ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በትብብር ይሰራል።
ተቋሙ አትሮሲቲስ ዋች አፍሪካ፣ ፓን አፍሪካን ሎውየርስ ዩኒየን፣ አፍሪካን ሊደርሺፕ ሴንተርና ዘ ኢንተርናሽናል ሪፊዩጂ ራይትስ ኢንሺየቲቭ የተሰኙ አፍሪካዊ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት ነው።