ካርታ

ከ 7 ሰአት በፊት

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን፣ ግልገል በለስ ከተማ በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና የአካል ጉዳት መድረሱን የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የዐይን እማኞቹ እንዳሉት ባለፈው አርብ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም. ከቀኑ 11 ሰዓት ተኩል ገደማ በተፈፀመው ጥቃት ቢያንስ 18 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በርካቶች ቆስለዋል።

ጥቃቱን ያደረሱትም በቅርቡ ከትጥቅ ትግል በመውጣት በከተማው ቅርብ ርቀት ላይ የሰፈሩ ታጣቂዎች መሆናቸውን የዐይን መስክሮቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ባወጣው መግለጫ፣ እስካሁን ትጥቃቸውን ያልፈቱ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሚክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ታጣቂዎች በግልገል በለስ ከተማ ሰኔ 30 በፈፀሙት ጥቃት በርካታ ንፁሃን ዜጎች መገደላቸው እና በርካቶች መቁሰላቸውን አረጋግጧል።

ፓርቲው ድርጊቱ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው አስነዋሪ እና አሳፋሪ መሆኑን በመግለጽ አውግዟል። ግድያውን የፈጸሙ አካላት በአፋጣኝ ለሕግ እንዲቀርቡም ፓርቲው ጠይቋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የዐይን እማኞች፣ በጥቃቱ ቢያንስ የ18 ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና 16 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸውን ተናግረዋል።

“በአካባቢው ‘በመንግሥት የሚቀለቡ’ ሽፍቶች አሉ” የሚሉት የዐይን እማኙ፣ ታጣቂዎቹ ከባድ መሣሪያ ታጥቀው ከተማ ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱም ይናገራሉ።

መንግሥት በክልሉ የሕዝቡን ደኅንነት እና ሰላም ለመጠበቅ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ሲገልጽ የቆየ ቢሆንም፣ የዐይን እማኙ ግን በሚኖሩበት አካባቢ “የሚደረገውን እናያለን። እየሆነ ያለው ነገር ያሳዝናል። መንግሥት የአካባቢውን ሕዝብ እያስተዳደረ አይደለም” ሲሉ ወቅሰዋል።

አርብ ዕለት የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎም የአካባቢው ነዋሪዎች ከብቶቻቸውን እየነዱ ወደ ፓዌ መፈናቀላቸውን እና ከተማ ውስጥም የትራንስፖርትም ሆነ ሌላ እንቅስቃሴ መቆሙን እኚሁ የዐይን እማኝ ተናግረዋል።

ሌላው ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኝም ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት “በሰላም ስምምነት ተመላሽ ተብለው ለመንግሥት እጅ ሰጥተዋል የተባሉት ታጣቂዎችን” ነው።

ከቻግኒ ወደ ፓዌ መስመር የሚሄዱ ተሽከርካሪዎችን በማገድ ተሳፋሪ ላይ በመተኮስ እና ቦንብ በመወርወር ጥቃት መፈፀማቸውን የተናገሩት ግለሰቡ፣ በጥቃቱ ቢያንስ 18 ሰዎች መገደላቸውን እና ቢያንስ 12 ሰዎች መቁሰላቸውን ተናግረዋል።

“አርብ አመሻሽ አካባቢ ላይ የተጀመረው ጥቃት ጋብ ያለው በጨለማ እና በዝናብ ምክንያት ነው” ሲሉም በአፋጣኝ የደረሰላቸው የፀጥታ አካል እንደሌለ ጨምረው ተናግረዋል።

ጨምረውም እሁድ ሌሊት ለሰኞ አጥቢያ ተኩስ ነበር የሚሉት ነዋሪው፣ ተመሳሳይ ጥቃት ይደርስብናል በሚል ስጋት ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እየወጡ ነው ብለዋል።

“ታጣቂዎቹ የሰላም ጥሪን ተቀብለው ከጫካ ወጡ ቢባልም፣ መሣሪያቸውን አላስረከቡም” ይላሉ የዐይን እማኙ።

ጥቃቱን በተመለከተ ቢቢሲ ከአካባቢው አስተዳር እና የፖሊስ ኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካም።

ታጣቂ ቡድኑ የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከዚህ ቀደም በመተከል አካባቢ የተለያዩ ጥቃቶች እና እገታዎች በመፈፀም ይከሰሳል።

ቡድኑ “የጉሙዝ ሕዝብን ነጻ እናወጣለን” በሚል ታጥቆ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስም ይነገራል።

ከዚህ ቀደም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በመተከል ዞን የታጣቂ ቡድን አባላት በሰላማዊ መንገድ ተስማምተው ትጥቃቸውን መፍታታቸውን በተደጋጋሚ መግለጹ አይዘነጋም።

ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ የክልሉ መንግሥት በደረሰው ስምምነት መሠረት የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ ፈትተው የተሃድሶ ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ወደ ኅብረተሰቡ ይቀላቀላሉ ቢባልም የሚታየው ይህንን የሚያረጋግጥ እንዳልሆነ አመልክቷል።

አክሎም ታጣቂዎቹ ትጥቅ ሳይፈቱ ማኅበረሰቡ ውስጥ የሚያደረጉት እንቅስቃሴ በተለይም የመንግሥት የፀጥታ አካላትን ሚና ተክተው የሚያደረጉት እንቅስቀሴ በአስቸኳይ እንዲቆም እና ትጥቅ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ከዚህ ቀደም ማሳሰቡን ፓርቲው አስታውሷል።

በክልሉ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በተደጋጋሚ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች ተፈጽመው በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም አካባቢያቸውን ለቀው ለመፈናቀል ተገደዋል።

ጥቃቱን ለማስቆምም በተለያየ ጊዜ የክልሉ መንግሥት ከታጣቂዎች ጋር አደረኩት ያለውን ስምምነት ተከትሎ የተወሰኑ የታጣቂዎቹ አባላት የሰላም ትግል ለማድረግ መሣሪያ ማስረከባቸው መገለጹ ይታወሳል።

በዚህም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመው ጥቃትም ጋብ ብሎ ቆይቶ ነበር።

በክልሉ የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ መስማማታቸው ከተገለጸ በኋላ፣ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የተፈጸመው ጥቃት እና ግድያ ከፍተኛው ነው።