
ከነሕይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ የተጨመሩ ወጣቶች ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም ተባለ ሰሞኑን አምስት ወጣቶች እጃቸው ወደኋላ ታስሮ እና ዓይናቸው ተሸፍኖ ከነሕይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ ተጥለው የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት ሲዘዋወር ተስተውሏል፡፡
አዲስ ማለዳም ስለ ክስተቱ ባደረገቸው ማጣራት ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ሰዎችን ያነጋገረች ሲሆን፤ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሰዎች ወጣቶቹ ላይ ድርጊቱ የተፈጸመው በምዕራብ ወለጋ ዞን ቂልጡ ካራ ከተማ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም እጃቸው ወደ ኋላ ታስሮ እና ዓይናቸው ተሸፍኖ ከነሕይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ ተጥለው የሚታዩት ወጣቶች፤ ኢያሱ ካሳሁን፣ አበበ ዱፌራ፣ ደሳለኝ ቡልቻ፣ ተስፋዬ ተርፋሳ እንዲሁም ኦብሲ ዲነግዴ የሚባሉ የቂልጡ ካራ ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ወጣቶቹን የመንግሥት የጸጥታ አካላት ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት” ብሎ ከሚጠራውና በመንግሥት “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በአሸባሪነት ከተፈረጀው ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አላችሁ በማለት፤ በእስር ቤት ካቆዩአቸው በኋላ ከማረሚያ ቤት በማውጣት ቂልጡ ካራ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አካባቢ ወደሚገኘው የመከላከያ ካምፕ እንደወሰዷቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ወደ መከላከያ ሠራዊት ካምፕ ከተወሰዱ በኋላም ጉድጓድ ራሳቸው እንዲቆፍሩ ተደርጎ፣ እጃቸውን የኋሊት በማሰርና ዓይናቸውን በጨርቅ በመሸፈን ከነሕይወታቸው ጉድጓዱ ውስጥ በጸጥታ ኃይሎች መከተታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከፍተኛ ድብደባ እና የሰብአዊ መብጥ ጥሰት የደረሰባቸው በመሆኑም፤ ከአምስቱ ወጣቶች አንደኛው በደረሰበት ጉዳት ወደ ሕክምና ተቋም መወሰዱን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ወጣቱ ለአራት ቀናት ሕክምናውን ተከታትሎ ወደ ቤተሰቡ ከተመለሰ በኋላም፣ በድጋሜ ወደ መከላከያ ሠራዊት ካምፕ እንዲመለስ መደረጉን ነው የጠቆሙት።
ወጣቶቹ ጉድጓድ ውስጥ ከተጣሉበት ቀን ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዝናብ እና ፀሐይ ሲፈራረቅባቸው ነበር የተባለ ሲሆን፤ አሁን ላይ ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩ ተጠቅሳል።
የወጣቶቹ ቤተሰቦች ምግብ እና ሌሎች ቁሳቆሶችን ይዘው ቢሄዱም፤ መገናኘት የማይፈቀድላቸው በመሆኑ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው ተብሏል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ከአካባቢው የመንግሥት ሹመኞችና ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።
አዲስ ማለዳ