የኢራን እና የኬንያ ፕሬዝዳንቶች በናይሮቢ።

ከ 2 ሰአት በፊት

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በአፍሪካ ታሪካዊ የተባለ ጉብኝታቸውን ከኬንያ ጀመሩ።

ፕሬዝዳንቱ መጀመሪያ ያቀኑት ወደ ኬንያ መዲና ናይሮቢ ነው።

ናይሮቢ የሚገኘው ስቴት ሃውስ በተሰኘው የፕሬዝዳንቱ መናገሻ ለኢራኑ ፕሬዝዳንት አቀባበል እንዲሆን በማለት 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።

አልፎም የኢራኑ ፕሬዝዳንት የኬንያ አቻቸው በተገኙበት ወታደራዊ ትዕይንት ተከናውኗል።

ራይሲ አሁን ከኬንያው መሪ ዊሊያም ሩቶ ጋር ስለሁለትዮሽ ግንኙነት ከመከሩ በኋላ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

ሁለቱ አገራት በኢንፎርሜሽን፣ ኮሚዩኒኬሽንና ቴክኖሎጂ፤ በአሳ ሃብት ልማት፣ በእንስሳት ጤና እና እርባታ ዘርፎች አብረው ለመሥራት ስምምነት ደርሰዋል።

የኢራኑ ፕሬዝዳንት የኬንያ ቆይታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ዩጋንዳ እና ዚምባብዌ ለማቅናት አቅደዋል።

የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ወደ አፍሪካ መጥቶ ጉብኝት ሲያደርግ ይህ ከአሥር ዓመት በኋላ የመጀመሪያው ነው።

ፕሬዝዳንት ራይሲ ማክሰኞ ወደ ናይሮቢ አውሮፕላን ከመሳፈራቸው በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ግንኙነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጠዋል።

ራይሲ ሃገራቸው ከአህጉረ አፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት የተቀዛቀዘ እንደነበር አልካዱም።

በለተያዩ ዘርፎች ከአፍሪካ ሃገራት ጋር መሥራት ያዋጣናል እንጂ አይጎዳም የሚል ስሜት ያለው አስተያየትም ሰጥተዋል።

ኢራን ከአፍሪካ ሃገራት ጋር አብራ ለመሥራት ጉጉት አላትም ብለዋል።

ነገር ግን የፖለቲካ ተንታኞች ከምዕራባውያን ዓለም ጋር መልካም ያልሆነ ግንኙነት ያላት የኢራንን ጉብኝት በበጎ አይመለከቱትም።

እርግጥ ነው ኢራን ከምዕራባዊያን እየደረሰባት ካለው ማዕቀብና ጫና አንፃር ከተቀረው የዓለማችን ክፍል ጋር ያላትን ግንኙነት ትሻለች።

ተትታኞች የኢራን አስተዳደር ቀጣናዊ ሰላም ያናውጣል፤ ሽብርተኝነትን ይደግፋል፤ ብሎም ሰብዓዊ መብት ይጥሳል ሲሉ ይወቅሳሉ።

ዩናይትድ ስቴትስና አጋሮቿ ኢራን ባለስቲክ ሚሳዔልና ኒውክሌር ታብላላች ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጣሉ።

ፕሬዝዳንት ራይሲ በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት ምዕራባዊያን ሃገራት በዓይነ ቁራኛ እንደሚመለከቱት እሙን ነው።