
ከ 6 ሰአት በፊት
ከየትኛውም የዓለማችን ክፍል በበለጠ በአፍሪካ አህጉር ለአየር ቲኬት ከፍተኛ ገንዘብ ይጠየቃል። በአህጉሪቱ ያሉ ተጓዦች ለአየር ቲኬት እና ለግብር ብዙ ገንዘብ ይከፍላሉ።
ከዋጋ አንጻር ወደ አፍሪካዊ አገር ከመብረር ይልቅ ወደ ሌላ አህጉር መብረር የተሻለ ነው።
ለመሳያነት ከጀርመኗ መዲና በርሊን ወደ ቱርክ ትልቋ ከተማ ኢስታንቡል መብረር ቢፈልጉ ለአየር ቲኬት በዛ ቢባል የሚጠየቁት 150 ዶላር ነው።
ተመሳሳይ ለሆነ እርቀት ከዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሌጎስ ናይጄሪያ ለመብረር ቢነሱ፣ ለአየር ቲኬት እስከ 850 ዶላር ሊጠየቁ ይችላሉ። እሱም በጉዞው መካከል ሌላ ከተማ ላይ እስከ 20 ሰዓት ጠብቀው አውሮፕላን ቀይረው ነው።
ይህ ሁኔታ በአፍሪካ የንግድ ሥራ መሥራትን በእጅጉ ከባድ እና ውድ ያደርገዋል።
ይህ ግን ሊሻሻል የሚችልበት አጋጣሚ አለ። አፍሪካውያን አገራት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሻሻል ቢተባበሩ ተጠቅመው ሌሎችን መርዳታ ይችላሉ።
እስከ 300 አየር መንዶችን አቅፎ የሚይዘው ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር እንደሚለው ከሆነ 12 ቁልፍ የአፍሪካ አገራት በጋራ ሠርተው ገበያቸውን ለአየር ግንኙነት ክፍት ቢያደርጉ ለ155 ሺህ ሰዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸውም በላይ የአገር ውስጥ ምርት እድገታቸውን ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማሳደግ ይችላሉ።
- ‘የአፍሪካ አቪየሽን አባት’ የሚባሉት አቶ ግርማ ዋቄ ማን ናቸው? ለምንስ ከሰሞኑ አነጋጋሪ ሆኑ?21 ሰኔ 2023
- “ከመሬት አግኝቼ ለባለቤቱ የመለስኩት 430 ሺህ ዶላር ፍቅርም ጥላቻም አድርሶብኛል”10 ሰኔ 2023
- በአፍሪካ አየር ላይ ‘የአንበሳውን ድርሻ’ እየያዘ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 19 ሀምሌ 2022
“የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በቀጥታ ለአገር ምርት እድገት አስተዋጽኦ ያበረክታል። ሥራ ይፈጥራል፤ ምጣኔ ሃብትን ያነቃቃል” ይላሉ የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሚል አል-አዋድሂ።
በዩናይትድ ኪንግድም የሚገኘው ዱርሃም ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሕግ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ኤፎላኬ አዴዬዬ በዚህ ይስማማሉ።
ረዳት ፕሮፌሰሩ አፍሪካ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቷ ደካማ በመሆኑ እንደ አህጉር ብዙ እያጣች ነው ይላሉ።
“በሌሎች እንዳየነው የአየር ትራንስፖርት ኢኮኖሚን ያሳድጋል። በሌሎች አህጉራት እንደተመለከትነው አየር መንገዶች ግንኙነትን በመፍጠር ለቱሪዝም እድገት ትልቅ አበርክቶ አላቸው። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሥራ ዕድልን ይፈጥራል።”
ረዳት ፕሮፌሰሩ በአፍሪካ ያለው ደካማ የመንገድ እና የባቡር መሠረተ ልማት ለአየር ትራንስፖርት የዕቃ ጭነት አገልግሎት ማደግ በራሱ መልካም አጋጣሚ ነው ይላሉ።
ከዓለማችን አጠቃላይ ሕዝብ 18 በመቶ በአፍሪካ አህጉር የሚገኝ ቢሆንም፣ በዓለማችን ከሚከናወኑ የአየር ትራንስፖርት ውስጥ በአፍሪካ ያለው ከ2 በመቶ ያነሰ ነው።
ምንም እንኳ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገና በማደግ ላይ ያሉ አገራት ናቸው ብሎ ከሚዘረዝራቸው 46 አገራት መካከል 33ቱ በአፍሪካ የሚገኙ ቢሆንም፤ አሁንም ደህነት በሚሊዮን ሊሚቆጠሩ አፍሪካውያን ትልቁ ጠላት ቢሆንም፣ በአህጉሪቱ ቀላል የማይባል መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ተፈጥረዋል።
እነዚህ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አፍሪካውያን በአየር ወደ አውሮፓ እና ሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የመብረር ፍላጎት እና አቅም አላቸው።

አፍሪካውያን አገራት ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት የአቪዬሽን ሴክተሩን ለማስተሳሰር ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም እስካሁን ስኬታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
“በአፍሪካን ምጣኔ ሃብት ላይ ስር ነቀል የሆነ ለውጥ ማምጣት ከተፈለገ ደካማ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ችግርን ለመቅረፍ አፍሪካ ወጥነት ያለው ስትራቴጂ ያስፈልጋታል” ይላሉ የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ዓለም አቀፍ ሊቀመንበር ዘመዴነህ ንጋቱ።
ዘመዴነህ እንደሚሉት አብዛኞቹ የበረራ መስመሮች የሚዘረጉት በአገራት መካከል በሚደረስ የሁለትዮሽ ስምምነት መሆኑን ገልጸው፣ በርካታ አየር መንገዶች እንኳን ትርፋማ ሊሆኑ እንደምንም ወጪያቸውን የሚሸፍኑ ናቸው፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም በኪሳራ ነው የሚንቀሳቀሱት ይላሉ።
“ሁሉም የአፍሪካ መንግሥታት የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ያነገቡ አውሮፕላኖችን በሂትሮ (የለንደን አየር ማረፊያ) ወይም በጄኤፍኬ (የኒው ዮርክ አየር ማረፊያ) ማየትን ይሻሉ። ነገር ግን የአፍሪካ መንግሥታት አየር መንገዶች ብቻቸውን ሊቆሙ እንደማይችሉ መረዳት አለባቸው።”
ዘመዴነህ በአፍሪካ ያሉ አየር መንዶች በአውሮፓ ካሉ የአየር መንገዶች ጥምረት ልምድ መውሰድ ይኖርባቸዋል ይላሉ።
ዘመዴነህ በብሪቲሽ አየር መንገድ እና በኔዘርላንዱ ኬኤልኤም አየር መንዶች መካከል ያለው ጥምረት አፍሪካውያን አየር መንገዶች እንደ ምሳሌ መውሰድ አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ።
ብዙ ደንበኛ ባለበት የአውሮፓ ገበያ ውስጥ እንኳ ከውድቀት ለመዳን እና ርካሽ አማራጭ ለማቅረብ ጥምረት ወሳኝ ነው ይላሉ።
አሁን ላይ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥራ የአየር ጉዞ ወጪን ለመቀነስ የተደረሰ ስምምነት አለ። የአፍሪካ ሰማዮችን ለአፍሪካ አየር መንገዶች ነጻ ለማድረግ እና የአየር ትራንስፖርት ወጪን ለመቀነስ አንድ ወጥ የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነትን 35 አገራት ቢፈርሙም ይህን ተፈጻሚ ለማድረግ ገና ብዙ ይቀራል።
የዓለም አቀፍ የአየር ትራስፖርት ማኅበሩ አል-ዋድሂ፣ አፍሪካውያን መንግሥታት ተባብረው ለመሥረት ብዙ ተነሳሽነት አያሳዩም ይላሉ።
አንዳንድ መንግሥታት በዘርፉ ኪሳራ ውስጥ ሆነው እንኳ፣ ለራሳቸው ጉዳይ እራሳቸው ብቻ የተሻለ መፍትሄ እንዳላቸው አድርገው ያስባሉ ይላሉ።

በዚህ መካከል ግን ለተቀሩት አፍሪካውያን አርዓያ መሆን የሚችል፤ ከፍተኛ እድገት እያሳያ ያለ አየር መንገድ አለ – የኢትዮጵያ አየር መንገድ።
አየር መንገዱ ከ15 ዓመታት በፊት 4 ሺህ ሠራተኞችን ያስተዳድር ነበር። ያ አሃዝ አሁን ላይ ከ17 ሺህ በላይ ተሻግሯል።
አየር መንገዱ ባለቤትነቱ የመንግሥት ቢሆንም፣ ያለመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደ ንግድ ተቋም እራሱን እያስተዳደረ ይገኛል።
አየር መንገዱ የአውሮፕላኖች ብዛቱን፣ መዳረሻውን እና የተጓዞች ቁጥሩን ከማሳደጉ በተጨማሪ አዲስ አበባን የጉዞ መዳረሻ ማዕከል በማድረግ ለአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ያስገባል።
ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ የሆኑት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስትራቴጂክ ዕቅድን በመቅረጽ የተሳተፉት ዘመዴነህ ንጋቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያውያን ኩራት ነው ይላሉ።
“የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለአገሪቱ ያስገባል፤ የአፍሪካውያን የሆነ፣ በአፍሪካውያን የሚመራ፣ ዓለም አቀፍ ኩባንያ መፈጠራቸው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኩራት ነው።”
አፍሪካውያን ተጓዦች ይህ አይነት ስኬት በአህጉሪቱ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን አሻሽሎ ከአውሮፓ እና ከእስያ ጋር ተቀራራቢ ሁኔታን ፈጥሮ በፍጥነት እና በአነስተኛ ዋጋ ወዳሻቸው ቦታ መሄድ እንደሚችሉ ተስፋ ያደርጋሉ።