ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

ከ 2 ሰአት በፊት

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች መካከል ንግግር ለማስጀመር በግብፅ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ወደ ካይሮ አቀኑ።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከግብፁ አቻቸው አብደል ፈታህ አል-ሲሲ በቀረበላቸው ግብዣ መሠረት የሱዳን ጎረቤት አገራት መሪዎች በሚያደርጉት ውይይት ላይ ተሳታፊ ለመሆን ዛሬ ረፋድ ወደ ካይሮ መጓዛቸውን ገልጸዋል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የሱዳን ጎረቤት የሆነችው ግብፅ ሁለቱን የጦር ጄኔራሎችን ሐሙስ ሐምሌ 06/2015 ዓ.ም. ለማደራደር ማቀዷን መግለጿ ይታወሳል።

በአገሪቱ ጦር መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሐን እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ መካከል የተፈጠረው የሥልጣን ሹክቻ በሱዳን ሉዓላዊ እና እንድነት ላይ አደጋ ከመጋረጡ በላይ በቀጠናው ላሉ አገራት የደኅንነት ስጋት ሆኖ ቀጥሏል።

በቀጠናው የጄኔራል አል ቡርሐን ጠንካራ ደጋፊ እንደሆነች የምትገመተው ግብፅ ሁለቱን የጦር ጄኔራሎች ስለማደራደር እስካሁን ምንም አይነት ይፋዊ እርምጃ ሳትወስድ ቆይታለች።

ከግብፅ በተጨማሪ በቀጠናው የጄኔራል ዳጋሎ የቅብር ወዳጅ የምትባለው የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ሁለቱን ወገኖች ለማደራደር ይፋዊ ጥያቄ እስካሁን አላቀረበችም።

ነገ ሐሙስ ካይሮ ላይ የሚጀመረው ድርድር ዓላማ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለመ ስለመሆኑ የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ወራት ያስቆጠረውን የሱዳንን ግጭት ለማስቆም ከትናንት በስቲያ ሰኞ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የተጠራ ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።

በዚህ ስብሰባ ላይ በሱዳኑ ግጭት ተፋላሚ የሆኑ ወገኖች ባይገኙም፣ በስብሰባው ተሳታፊ የነበሩት መሪዎች የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ወደ ሱዳን ተሰማርቶ ሰላማዊ ሰዎችን እና የእርዳታ አቅርቦትን ለመጠበቅ እንዲያግዝ ሐሳብ አቅርበዋል።

ሱዳን ግን የትኛውም የውጭ ኃይልን ወደ ግዛቴ ማሰማራት ጠብ መፈለግ ነው የሚሆነው በማለት ሐሳቡን እንደማትቀበል በጽኑ አስታውቃለች።

ኢጋድ ስብሰባውን የጠራው የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዦችን በአካባቢው አገራት መሪዎች ፊት ለፊት ለማነጋገር አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የተፋላሚ ኃይሎቹ ተወካዮች አለመገኘታቸው እንዳሳዘነው ገልጾ በአካባቢው አገራት መሪዎች እና በሌሎችም የውይይቱ ተሳታፊዎች የሱዳን ጉዳይ ጥልቅ ውይይት ተደርጎበታል ብሏል።

የሱዳን ጦር ሠራዊት መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሐን፣ የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር የሆኑትን የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ይደግፋሉ በሚል ገለልተኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ በማስገባት በኢጋዱ ስብሰባ እንደማይገኙ ቀድሞ ተዘግቦ ነበር።

የኢጋድ ስብሰባ ተሳታፊዎች
የምስሉ መግለጫ,የኢጋድ ስብሰባ ተሳታፊዎች በሱዳን የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል እንዲሰማራ ሐሳብ ቢያቅርቡም ሱዳን ሐሳቡን አጥብቃ ተቃውማለች።

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ግብፅ በጠራችው ስብሰባ ላይ ስለመገኘታቸው የታቀወቀ ነገር የለም። ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባ በነበረው የኢጋድ ስብበሳ ላይ ሳይገኙ ከቀሩት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ውጪ የትኞቹ የቀጠናው አገራት መሪዎች እንደሚገኙ እሰካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በጂዳ ሁለቱን የጦር ጄኔራሎች ለማግባባት ጥረት ሲያደርጉ ካይሮ እና አቡ ዳቢ ተሳታፊ አልነበሩም።

ከዚህ ቀደም ግጭት ውስጥ የገቡትን የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ የሆኑትን ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን ለማግባባት የተደረጉ ተደጋጋሚ ጥረቶች ፍሬ አላፈሩም።

አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ ተፋላሚ ኃይሎቹ በተደጋጋሚ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ ማድጋቸው ቢገልጽም ይህ ግባራዊ ሳይሆን ውጊያው ቀጥሏል።

ሦስት ወር ሊደፍን የተቃረበው ግጭት በተለይ የሱዳን መዲና ካርቱም ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከትቶ ይገኛል። ሁለቱም ኃይሎች ዋና ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ለማስገባት እየተፋለሙ ነው።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የካርቱምን፣ የኦምዱርማንን እና የባህር ዳርቻ ከተሞችን አብዛኞቹን ክፍሎች ተቆጣጥሮ ይገኛል።

የእርስ በርስ ጦርነቱ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብን ከመኖሪያው ያፈናቀለ ሲሆን፣ 700 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አገር ጥለው ተሰደዋል።