
ከ 6 ሰአት በፊት
ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ ተግባራዊ የሆነው ፌደራላዊ የአስተዳደር አወቃቀር 14 ክልሎች ነበሩት። ብዙም ሳይቆይ ደቡብ ክልሎች በአንድ ተጣቃለው፣ የአዲስ አበባ ክልልነት ወደ ከተማ አስተዳደርነት ሲለወጥ ቁጥሩ ወደ 9 ወርዶ ቆይቷል።
የክልልነት ጥያቄ ሲነሳበት ከቆየው የደቡብ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሦስት አዳዲስ ክልሎች በመውጣታቸው፣ የፌደራል መንግሥቱ አባል ክልሎች ቁጥር አሁን ወደ 12 ደርሷል።
የሲዳማን እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 28/2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለአዲሱ ለ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ይሁንታን ሰጥቶ የፌዴሬሽኑ አካል ሆኗል።
በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ተካተው የነበሩ የጌዴኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የዲራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ልዩ ወረዳዎች ናቸው አዲሱን ክልል የመሠረቱት።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ሁሉም የደቡብ ኢትዮጵያ ዞኖች እና ማኅበረሰቦች በሚያስብል ሁኔታ የተናጠል ክልል ለመመሥረት በምክር ቤቶቻቸው ውሳኔ አሳልፈው ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበው ነበር።
ነገር ግን ከሲዳማ ውጪ ያሉት ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በመውጣት የተዋቀሩት አዲሶቹ ክልሎች እነዚህን የክልልነት ጥያቄን ያቀረቡ አካባቢዎችን በአንድ ላይ ያካተቱ ናቸው።
አገሪቱ ካሏት ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑት የሚገኙበት የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አሁን ወደ አራት ክልልነት ተሸጋግሯል።
የሲዳማ ክልል ከደቡብ ክልል በመውጣት ቀዳሚ ሲሆን፣ በመቀጠልም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ አሁን ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እንዲመሠረት ተወስኗል። የቀሩት ደግሞ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ስር ይቀጥላሉ።
- ክልልነት ለጠየቀው ሁሉ ቢሰጥ ችግሩ ምንድነው?18 ሀምሌ 2019
- የደቡብ ክልል ፍጻሜ እየተቃረበ ይሆን?31 ሀምሌ 2022
- “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” በሚል 12ኛ ክልል ተመሠረተ5 ሀምሌ 2023
የደቡብ ክልል አለ?
በአገሪቱ ካሉት ትላልቅ ክልሎች ውስጥ አንዱ የነበረው የደቡብ ክልል ምንም እንኳን ከውስጡ ሦስት ክልሎች በፈጠሩም ሕልውናው ሳያከትም ባለበት ቀጥሏል።
በዚህም ክልሉ በሕገ መንግሥቱ ፈርሷል የሚል ነገር አለመኖሩን ፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ያጠኑት እና በክልሉ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ውስጥ ያገለገሉት አቶ ደያሞ ዳሌ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የደቡብ ክልል አካል የነበሩ እና በሕዝበ ውሳኔው ድምጽ ሳይሰጡ የቀሩት የክልሉ አካል ሆነው ይቀጥላሉ። በዚህም ክልሉ “ፈርሷል ማለት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በጠጨባጭ ግን ክልሉ የለም” ይላሉ የአቶ ደያሞ።
ደቡብ ክልል የፌደሬሽኑ አካል ሆኖ ቢቀጥልም ሲዋቀር የነበረው ድንበር፣ የቆዳ ስፋት፣ የሕዝብ ብዛት እና የብሔረሰቦች ቁጥር አሁን አለመኖሩ ‘በተጨባጭ ክልሉ የለም’ እንዲሉ አድርጓቸዋል።
በመሆኑም አሁን ክልል የሆኑት አካባቢዎች ተወካዮችን የያዘው ምክር ቤት ተሰብስቦ በሕጋዊ መንገድ ይፋ በማድረግ፣ የዋና ከተማው መቀመጫን ሲወስን የነባሩ ክልል ህልውና እንደሚያበቃ አቶ ደያሞ ይናገራሉ።
የአዳዲሶቹን ክልሎች ምሥረታ ተከትሎ በቀድሞው የደቡብ ክልል ውስጥ የሚቀሩት የም፣ ጉራጌ፣ ሃዲያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ እና ሃላባ ይሆናሉ።

77 ክልሎችን የመመሥረት መብት
አቶ ጎበዜ ጎአ የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር ሲሆኑ፣ የወላይታ ሕዝብ በራሱ ክልል ለመሆን የነበረው ፍላጎት ከ20 ዓመታት በላይ መገፋቱን ይናገራሉ።
የወላይታ ሕዝብ በሲዳሞ ክፍለ አገር፣ በደቡብ ክልል እና በቀድሞ ሰሜን ኦሞ አውራጃ ውስጥ በተለያዩ ሥርዓቶች “ተንካራታች ሕዝብ እንዲሆን ተፈርዶበታል” ይላሉ።
ነገር ግን አሁን በአዲሱ ክልል ውስጥ ለመካተት በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ይሁንታን መስጠቱ የተነገረው የወላይታ ሕዝቡ እራሱን የቻለ ክልል እንዲኖረው የሚያቀርበው ጥያቄ እንደሚቀጥል ይናገራሉ።
“ይህንን ሊከለክል የሚችል ሕግ የለም። የወላይታ ሕዝብ አብሬ ኖሬ አይቼዋለሁ አላዋጣኝም። አሁን ቤቴን ልገንባ ነው እያለ ያለው” ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ፣ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ሕገ መንግሥቱ ቋንቋ እና ብሔረሰብን መሠረት ያደረገ በመሆኑ በቀጣይም ክልሎች በየጊዜው የሚመሠረቱበት በር ክፍት ነው።
“የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ ቁጥር 2፣ ባሉት ክልሎች ውስጥ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች በማንኛውም ጊዜ ክልል መመሥረት ይችላሉ ይላል። ከዚያም አገር ለመሆን አንቀጽ 39 አለ።
“ስለዚህም አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ 76 ወይም 77 ብሔር፣ ብሔረሰቦች በፌደሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና አግኝተዋል። እነዚህ ሁሉ ክልል የመመሥረት ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው” ብለዋል።
አቶ ደያሞም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ። ተግባራዊ የተደረገው ግን በተለያየ መልኩ መሆኑን በመጥቀስ፣ ሲዳማ ውስጥ የክልልነት ጥያቄ ሕዝቡ ሲያቀርብ ምላሽ የተሰጠው በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንደሆነ ይናገራሉ።
በደቡብ ክልል ውስጥ ክልል የመሆን ጥያቄ በፖለቲካ ልሂቃን መሪነት በአካባቢዎቹ መዋቅሮች እንዲሁም በሕዝቡ ተደግፎ ሲቀርብ ቆይቷል። ውስብስቡን እና ተደራራቢውን የክልሉ ዞኖች ጥያቄን ለመመለስ የፌደራሉ መንግሥት ሲቸገር ቆይቷል።

“…የማስታገሻ ኪኒን”
አቶ ደያሞ እንደሚሉት በቅርብ ጊዜያት ከሕዝብ ባሻገር የክልልነት ጥያቄው ከተለያዩ ሁለት አቅጣጫዎች የሚመጡ ናቸው።
“አንደኛው ልክ እንደ ሲዳማ እኛም በብሔር ክልል መመሥረት አለብን የሚሉ የወላይታ እና የጉራጌ የብሔር ድርጅቶች አሉ። ሌላው ደግሞ በዚህ መልኩ ክልል ሁኑ በሚል ከብልጽግና ከላይ ወደታች የመጣ ነው። ስለዚህ ጥያቄውንም የብልጽግና ካድሬዎች ራሳቸው ያመጡት ሲሆን፣ መላሾቹም እነሱ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።
ከየትኞቹ አካባቢዎች ጋር በመጣመር ክልል እንዲሆኑ “ከላይ ወደ ታች ውሳኔ የወረደላቸው” ያሏቸው አካባቢዎች ምላሽ አለማግኘታቸውን ጠቁመዋል። በተለይም በወላይታ እና በጉራጌ አካባቢ “የከረረ ነገር አለ” ብለዋል።
አቶ ደያሞ ይህ ውሳኔ በክልሉ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየውን ጥያቄ በዘላቂነት የማይፈታው ነው በማለት “ከብልጽግና የተሰጠ የማስታገሻ ኪኒን ነው” ይሉታል።
ነገር ግን ከላይ ወደ ታች የወረደ ነው የሚሉት የክልልነት ጥያቄ እና ምላሹ፣ በአንዳንድ መልኩ አውንታዊ ውጤት ቢኖረውም ለክልልነት ፍላጎቱ ዘላቂ ምላሽ እንደማይሰጥ ያነሳሉ።
“ከአርሶ አደሩ አንጻር ከታየ ብዙም ልዩነት የለውም። የአርሶ አደር ጥያቄ በወረዳ ደረጃ ግልጋሎት ማግኘት ነው።”
በተግባር የመልካም አስተዳደር እና ኢኮኖሚ ጉዳዮችን ማሳካት ከተቻለ ቅቡልነት ሊኖረው እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠው “ከዚያ ውጪ ጥያቄዎች ይመልሳሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም።”
አቶ ጎበዜ ጎአ እና ሌሎች የወላይታ ፖለቲከኞች በቅርቡ በወላይታ ተካሄደውን ሕዝበ ውሳኔ ዕውቅና አይሰጡትም።
የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ወደ ጎን በማለት “የፓርቲ ውሳኔ ለማስፈጸም የተካሄደ የይስሙላ ሕዝበ ውሳኔ ነው” ይላሉ አቶ ጎበዜ።
ሕዝበ ውሳኔውን መብትን የሚደፈጥጥ ከማለት ባለፈ የሕዝቦችን ጥያቄ በመተው “ገዢዎች የሚያነሷቸውን ሃሳቦችን ወደፊት ያመጣ፤ የወላይትን ሕዝብ እና ጥቅም የሚፈታተን አደገኛ ፕሮጀክት እንደሆነ ተመልክተናል” ሲሉ ገልጸዋል።

ጥያቄ በሕዝብ ውሳኔው ላይ
በሕዝበ ውሳኔዎቹ ላይ የሕዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆን ተዓማኒ አያደርገውም ወይ ለሚለው አቶ ደያሞ ሲመልሱ በባለሥልጣናት ግፊት ሕዝቡ ወጥቶ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
በሕዝበ ውሳኔው ከተሳተፈው ሕዝብ ይልቅ አቶ ደያሞ መታየት ያለበት በሕዝበ ውሳኔው ላይ ስለቀረቡት አማራጮች ነው ይላሉ።
“ለምሳሌ ‘ለብቻህ ክልል ለመመሥረት ትፈልጋለህ ወይ?’ የሚል ጥያቄ አልቀረበም። ጥያቄው ‘እየፈረሰ ያለው ክልል ውስጥ ትቆያለህ ወይስ በአዲሱ ክላስተር ስር ትሆናለህ?’ ነው” ብለዋል።
ለዚህም ነው ከሲዳማ ውጪ ያሉት አዳዲስ ክልሎች የደቡብ ክልል አባላትን እና ድንበርን ከመቀነስ ውጪ ያመጣው ነገር የለም የሚሉት።
“ስለዚህ በነቂስ ወጣም፣ አልወጣ ሕዝቡ ምን ምርጫ ነበረው?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
አቶ ጎበዜም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ። ከወላይታ ሕዝብ መምረጥ የሚችለው 2.5 ሚሊዮን ያህሉ ቢሆንም በተለያየ ጫና 30 በመቶው ብቻ መመረጡን ጠቁመው፤ ይህ ቁጥር በዓለም አቀፍ መመዘኛ ጭምር ተቀባይነት እንደሌለው ጠቁመዋል።
በዚህ ምክንያት ሕዝበ ውሳኔው ውድቅ እንዲደረግ “ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አንስቶ ስምንት ተቋማትን በፍርድ ቤት ከሰናል። ሂደቱ በፍርድ ቤት ታይቶ ውጤት የሚመጣ ይሆናል” በማለት የወላይታ ክልል አስኪመሠረት ድረስ ጥያቄያቸው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አቶ ደያሞ የአዳዲሶቹ ክልሎች ጉዳይ ለብልጽግና ተቀባይነት ወሳኝ መሆኑን ያነሳሉ።
ክልሎች መመሥረታቸው ሕዝባዊ አገልግሎቶችን ወደ ሕዝቡ ቅርብ እና ተደራሽ ማድረግ አላማንም ይዟል። በፊት ከነበረው ደቡብ ክልል አንጻርም አነስ ስለሚሉ ምቹ ይሆናሉ። ይህንን ተጠቅሞ ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
የሙስና መስፋፋት፣ በፌደራል መንግሥት የሚሠሩ ፕሮጀክቶች አለመኖር፣ የገጠር ጤና ኤክስቴንሽን መበተን መጀመር እና የባለሥልጣናት ተጠያቂነት አለመኖር ግን መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባው ነው።

ቀጣይ ጥያቄዎች እና ፈተናዎች
የክልልነት ጥያቄዎች ተመልሰዋል ቢባልም አሁንም የሚነሱ ጉዳዮች አሉ። የመጀመሪያውም ሊሆን ይችላል ብለው አቶ ደያሞ የሚያነሱት የዋና ከተማ ጥያቄን ነው።
እንደ ደቡብ ምዕራብ ክልል መሥሪያ ቤቶችን የተለያዩ ቦታዎች በማድረግ ለመመለስ ቢሞከርም እንደ ዋና ከተማ የሚወሰደው የርዕሰ መስተዳደሩ መቀመጫ መሆኑን በመጥቀስ፣ የዋና ከተማ ጥያቄ ፈተና ሊሆን ይችላል ይላሉ።
አቶ ደያሞ እንደሚሉት ብልጽግና አንድ ወጥ ፓርቲ ይባል እንጂ፣ የሹመት ምደባው ብሔርን መሠረት ማድረጉ አይቀርም። በዚህም አስቸጋሪ ሁኔታዎች እና ጥያቄዎች ሊቀርቡ እንደሚችሉ አቶ ደያሞ ያነሳ።
“የሥልጣን ቦታን የመከፋፈል ጉዳይ ፊት ለፊት አልተወራም እንጂ ለዚህኛው ብሔረሰብ ይህ ደረሰ፣ ለዚያኛው ይህ የሚለው ከኢህአዴግ ጀምሮ ያለ አካሄድ ነው። በቂ ውክልና አላገኘንም የሚሉ እና ይህ ብቻ ደረሰን የሚል ጉርምርምታ ይኖራል።”
ለአቶ ጎበዜ ይህ ፉክክሩ “በሕዝቦች መካከል ጥርጣሬን እና የእርስ በእርስ መቃቀርን የሚፈጥር አደገኛ ፕሮጀከት ነው” ከማለት ባለፈ መቻቻልን ሳይሆን መፎካከርን፣ በዐይነ ቁራኛ መተያየትንና የሚፈጥር ነው።
የልማት ጥያቄዎችን መመለስ ሌላው ጥያቄ ነው ሚሉት አቶ ደያሞ “ከአዲሱ ክልል ጋር ዞን ትሆናላችሁ ተብለው በካድሬዎች ይፋዊ ባልሆነ መንገድ የተነገራቸው አሉ። ዞን ካላገኙ ኩርፊያው ይቀጥላል” ሲሉ አዲሶቹ ክልሎች የሚገጥሟቸውን ቀጣይ ፈተናዎች አንስተዋል።