
July 12, 2023 – EthiopianReporter.com
ማኅበራዊ ከደቡብ ሱዳን ከሚገቡ ስደተኞች የኢቦላ ቫይረስ ሥጋት እንዳለው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና…
ቀን: July 12, 2023
- የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቅኝት እያደረገ ነው
ከደቡብ ሱዳን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሉ በሚገቡ ስደተኞች ሳቢያ፣ከፍተኛ የኢቦላ ቫይረስ ሥጋት እንደተጋረጠበት የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡
ሪፖርተር ከጤና ቢሮው ባገኘው መረጃ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ክልል እየገቡ ናቸው፡፡ ቫይረሱ በደቡብ ሱዳን ብዙዎችን እየገደለ መሆኑን ከደረሰው መረጃ መረዳቱንና ቫይረሱ በስደተኞቹ አማካይነት የመዛመት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ፣ በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ሥጋት መፈጠሩን ቢሮው አስታውቋል፡፡
የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ክልሉ እየገቡ በመሆናቸው ምክንያት ቫይረሱ እንዳይዛመት ከፍተኛ ሥጋት መፍጠሩን፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዋጮ ዋጊሾ ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ቫይረሱ ወደ ማኅበረሰቡ እንዳይዛመት የጤና ቢሮው ምን እያደረገ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ምርመራ በማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን ተከስቷል የተባለው የኢቦላ ቫይረስ ከ200 በላይ ሰዎችን እንደገደለ፣ ከፍተኛ የመከላከል ሥራ ካልተከናወነ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ቫይረሱ የመስፋፋት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን የገለጸው የጤና ቢሮው፣ በፍጥነት ርብርብ ካልተደረገ ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን ሥጋቱን ገልጿል፡፡
የቫይረሱ ምልክት የሚታይባቸው ስደተኞች መኖራቸው፣ ስደተኞቹ ወደ ክልሉ መሀል ከተማ ድረስ መግባታቸውን ተከትሎ የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ሪፖርተር የተመለከተው የክልሉ ጤና ቢሮ ደብዳቤ፣ በደቡብ ሱዳንና በሱዳን የኢቦላ በሽታ ተጠርጣሪዎች መታየታቸውና ሞት ጭምር እንደተመዘገበ፣ በስደተኞቹ አማካይነት ቫይረሱ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሊሻገር ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግ ያሳስባል፡፡
የጤና ቢሮው ደብዳቤ፣ ‹‹ከደቡብ ሱዳን በተጨማሪ በሱዳን በተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ወደ ክልላችንና የአጎራባች ወረዳዎች በኩል በከፍተኛ ሁኔታ ከመግባታቸው ጋር ተያይዞ በሽታው ሊገባ እንደሚችል አሳውቀውናል፤›› ይላል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ትኩሳት፣ ከፍተኛ የራስ ምታት፣ የመገጣጠሚያ ሕመም፣ ድካም፣ የጉሮሮ ሕመም፣ የምግብ ፍላጎት ማጣትና የሆድ ሕመም፣ በተለያዩ የሰውነት ቀዳዳዎች የደም መፍሰስ የቫይረሱ ምልክቶች መሆናቸው በደብዳቤው ተዘርዝሯል፡፡
በመሆኑም የክልሉ ነዋሪዎች እነዚህ ምልክቶች ከተስተዋሉ በአቅራቢያቸው የሚገኙ የጤና ተቋማት እንዲሄዱና አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ንክኪ ያላቸውን ሰዎችንም የመለየት ሥራ እንዲያከናውኑ አሳስቧል፡፡
በተጨማሪም የጤና ተቋማትም ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እንዲሰማሩ፣ የአሰሳ ቅኝቶችን እንዲያጠናክሩና የአጎራባች አገር መግቢያ በሮች ላይ የልየታ ሥራ እንዲሠሩ፣ ለተጠርጣሪዎች የሚሆን ማቆያ እንዲዘጋጅና የላቦራቶሪ ግብዓቶች እንዲዘጋጁ የክልሉ ጤና ቢሮ ለአሶሳ፣ ለካማሺና ለመተከል ዞኖች ጤና ቢሮ መምርያዎች ማሳሰቢያ መስጠቱን ሪፖርተር የተመለከተው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡
እስካሁን በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች መገኘታቸው ወይም አለመገኘታቸው፣ ቫይረሱ እንዳይስፋፋ ምን እየተደረገ እንደሆነ ምላሽ እንዲሰጥ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄም የክልሉ የጤና ቢሮዎች የልየታ ሥራ እየተሠራ መሆኑን፣ እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ) በቫይረሱ የተጠቃ አንድም ሰው እንደሌለ አስታውቋል፡፡
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተጨማሪ ስደተኞቹ ወደ ጋምቤላ ክልልም እየገቡ መሆኑ እንዳሠጋቸው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ግን ችግሩ እንዳልተፈጠረ በመግለጽ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
በሱዳንና በደቡብ ሱዳን የተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት ሳቢያ ስደተኞች ወደ ጋምቤላና ደቡብ ክልል መግባታቸውን እንዳላቆሙም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ተክለ ማርያም የቅኝት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ወቅት ይህ ነው ለማለት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ አክለውም በሥጋት ደረጃ የሚወራው ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለማረጋገጥ፣ ጥናት እየተደረገና መረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን አክለዋል፡፡
