
July 12, 2023 – EthiopianReporter.com
ማኅበራዊሸገር ከተማ 58 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት አቅጃለሁ አለ
ሸገር ከተማ 58 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት አቅጃለሁ አለ
ቀን: July 12, 2023
የሸገር ከተማ አስተዳደር በተለያዩ የግንባታ አማራጮች 58 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ማቀዱን ገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ አምስት ከተሞች ይዞ የተቋቋመው ሸገር ከተማ፣ በ2016 ዓ.ም. በከተማው የሚታየውን የመኖሪያ ችግር ለመቅረፍ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ማቀዱን አስታውቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ግንባታዎቹን ለማከናወን የተለያዩ ዘዴዎች ለመከተል ያቀደ ሲሆን፣ ይህም የግል ባለሀብቶች ሽርክና (Private Partnership)፣ ማኅበራትን በማደራጀት፣ እንዲሁም ባለሀብትና የበጎ አድራጎት ድርቶችን በማስተባበር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች መገንባት እንደሆነ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ማስተዳደርና ማስተላለፍ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት መሠረት አበበ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ግንባታ ለማከናወን አቅም ላላቸው የግል ድርጀቶችና ለማኅበራት ከተማ አስተዳደሩ መሬት ማሰናዳቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በውሉ መሠረት ግንባታ ይከናወናል ተብሏል፡፡
ከከተማ አስተዳደሩ መሬት የተረከበ የግል ድርጅት ጥራቱን የጠበቀ ግንባታ አከናውኖ በውሉ መሠረት ለተረከበው መሬት በክፍያ ሥሌት ከገነባቸው ቤቶች የተወሰኑትን ለከተማ አስተዳደሩ ለማስረከብ አማራጭ መቅረቡን የቢሮ ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በከተማ ለሚኖሩ ማኅበራት በተመሳሳይ የመሬት አቅርቦት እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦትና የባንክ ብድር እንደሚያመቻች አስታወቋል፡፡
ማኅበራቱ ደግሞ የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ክፍያ በአግባቡ መክፈል እንደሚገባቸው፣ በባንክ የቆጠቡትን መጠን ከግምት ያስገባ ቀሪ ክፍያ በባንክ እንዲሸፈንላቸው ይደረጋል ተብሏል፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ከአራት እስከ ሰባት ወለል ድረስ የሚኖራቸው ሲሆን፣ ቤቶቹን በዕጣ የማከፋፈል ኃላፊነቱ የማኅበሩ ኃላፊነት እንደሚሆን ወ/ሪት መሠረት ተናግረዋል፡፡
በተለይ የግል ድርጅቶችን በጋራ መኖሪያ ግንባታ ለማሰማራት፣ ለከተማ ቅርብ የሆኑና ምቹ መሠረተ ልማት ያላቸው አምስት ክፍላተ ከተሞች ላይ መሬት መሰናዳቱን ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል በከተሞቹ ለሚኖሩ የመንግሥት ሠራተኞችና በተለያዩ የሥራ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ 28 ሺሕ ነዋሪዎች የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ማታቀዱ ተገልጿል፡፡
ግንባታውን ለማሳካትም የከተማ አስተዳደሩ ከባለሀብቶች ጋር በመሆን፣ የተለያዩ የቁጠባ አማራጮች በማቅረብ ለመገንባት ማቀዱን የቢሮ ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም. በከተማ አስተዳደሩ ሊገነቡ ከታቀዱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል፣ ለ1,200 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚገነቡ ይገኝበታል ተብሏል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በማኅበር ተደራጅተው መገንባት ለሚፈልጉ የዳያስፖራ አባላትና አርሶ አደሮች መሬት ማሰናዳቱን የቢሮ ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡
የሸገር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ለጋራ መኖረያ ቤቶች ግንባታ የሚያስፈልገውን በጀት ከቀናት በኋላ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል፡፡