
July 12, 2023 – EthiopianReporter.com

ዜና ኢትዮጵያን ሰላም ነች ማለት እንደማይቻል አፍሪካ ውስጥ የሚሠራ የሲቪክ ማኅበራት ንቅናቄ አስታወቀ
ኢትዮጵያን ሰላም ነች ማለት እንደማይቻል አፍሪካ ውስጥ የሚሠራ የሲቪክ ማኅበራት ንቅናቄ አስታወቀ
ቀን: July 12, 2023
ከስምንት ወራት በፊት በፕሪቶሪያ የተደረገውን የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት ጦርነት የማቆም ስምምነት አተገባበርን አስመልክቶ፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ሰላም ነች ብሎ መናገር አዳጋች ሊሆን እንደሚችል አፍሪካ ውስጥ የሚሠሩ የሲቪክ ማኅበራት ንቅናቄ አስታወቀ፡፡
‹‹አፍሪካውያን ለአፍሪካ ቀንድ›› (Africans for the Horn of Africa) የተባለ አራት አፍሪካ ውስጥ የሚሠሩ የሲቪክ ማኅበራት ንቅናቄ፣ የሰላም ስምምነቱን የሚገመግም ሙሉ ሪፖርት ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡
ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈራረም በኋላ በርካታ ክፍተቶች ታይተዋል ያለው ንቅናቄው፣ የስምምነቱ አተገባበር የንፁኃን ደኅንነት ማስጠበቅ እንዳላስቻለ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡ በስምምነቱ የተሳኩ እንዳሉ አስታውቆ፣ መደረግ አለበትም በማለት ምክረ ሐሳብ ያስቀመጣቸው ነጥቦች በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡
የፓን አፍሪካ ጠበቆች ኅብረት፣ የአፍሪካ አመራር ማዕከል፣ እንዲሁም ዓለም አቀፉ የስደተኞች መብት ንቅናቄን ጨምሮ ‹‹አፍሪካውያን ለአፍሪካ ቀንድ›› ንቅናቄን የሚመራው መቀመጫውን ኡጋንዳ ካደረገው ‹‹አትሮሲቲስ ዎች አፍሪካ›› ጋር በጋራ ነው ሪፖርቱ ተዘጋጅቶ ይፋ የተደረገው፡፡
‹‹አሁን ኢትዮጵያ ሰላም ውስጥ ነች ማለት አደገኛ ነው፤›› ያለው ሪፖርቱ፣ ይህንንም ሲያብራራ በትግራይ አስፈሪ ሁኔታዎች ተቀርፈዋል ብሎ አቋም መውሰድ፣ በሁለቱ ተፈራራሚ አካላት መካከል የጥይት ድምፅ አለመሰማቱ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ስህተት እንደሆነ አስረድቷል፡፡
የሰላም ስምምነቱ ካሳካቸው ድርጊቶች መካከል በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩት አካላት ተኩስ ማቆማቸውን፣ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀርብ መመቻቸቱን፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ መጀመራቸውን፣ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙንና ኢትዮጵያም በሽግግር ፍትሕ ላይ ውይይት መጀመሯን እንደ ጥሩ ጎን በሪፖርቱ ተወስተዋል፡፡
በስምምነቱ አተገባበር ላይ የታዩ ክፍተቶች ብሎ ሪፖርቱ ያቀረባቸው ደግሞ በኤርትራና የመከላከያ አካል ባልሆኑ የታጠቁ አካላት፣ በተወሰኑ ቦታዎች ንፁኃን ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በምግብ ዕርዳታ ላይ የታየውን ዘርፉ፣ የሕክምና መሣሪያዎችና አገልግሎቶች በበቂ መጠን አለመኖር፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው፣ በርካታ የትግራይ አካባቢዎች የሲቪክ ማኅበራት ድጋፍ የማይደረስባቸው መሆናቸው ስምምነቱ ካላሳካቸው መካከል መሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
ለምርመራ ሥራው ትግራይ ለመግባት በመቸገራቸው ሪፖርቱን ከተለያዩ ምንጮችና ከውስጥ አዋቂዎች በተደረገ ቃለ መጠይቅ መሠረት እንዳዘጋጁት የሪፖርቱ አዘጋጆች ለሪፖርተር ገልጸው፣ ሌሎችም በርካታ የሲቪክ ማኅበራት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡
የአትሮሲቲስ አፍሪካ ዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዲስማስ ንኩንዳን ዋቢ በማድረግ፣ የሪፖርቱ አዘጋጆች ለሪፖርተር በላኩት ምላሽ የፌዴራል መንግሥትንና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን በሪፖርቱ ውጤት ላይ ለማነጋገር በሒደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡