
ከ 4 ሰአት በፊት
ትናንት ሐምሌ 5/2015 ዓ.ም በናይሮቢ እና ሌሎች የኬንያ ከተሞች የአደባባይ ተቃውሞ ተካሂዷል።
በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤታቸው በመሄድ ላይ እያሉ ፖሊስ የተኮሰው አስለቃሽ ጭስ ብዙዎቹ ላይ ጉዳት አድርሷል።
ሐሙስ ማለዳ ሐምሌ 6/2015 ዓ.ም የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ቢያንስ 53 ሕጻናት ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተዋል።
የሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ህጻናቱ ራሳቸውን ስተው የነበረ ሲሆን ከህክምና ዕርዳታ በኋላ መንቃት መጀመራቸው ታውቋል።
በመላ አገሪቱ የኑሮ ውድነትን በመቃወም በተቃዋሚ ፓርቲዎች የተጠራ ሰልፍ ተደርጓል።
ነገር ግን ሰልፉ ወደ ብጥብጥ አድጎ ሞትን አስከትሏል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት 12 ኬንያውያን በተቃውሞው ተገድለዋል። ሌሎች በመቶዎ ችየሚቆጠሩ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ሁለት ግለሰቦች አንድ የፖሊስ ጣቢያ በእሳት ሲያቃጥሉ ሞተዋል፣ በሌላ በኩል አንዱ ደግሞ ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ መሞቱን ምንጮች ገልጸዋል።
ተቃውሞው ክልከላ ተደርጎበት የነበረ ቢሆንም ኬንያውያን ግን ክልከላውን ጥሰው አደባባይ ወጥተዋል። የተቃውሟቸው ዋና ምክንያትም እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነት እና በመንግሥት የተዘጋጀው አዲሱ የግብር ጭማሬ ነው።
በአዲሱ የግብር ማሻሻያ መሰረት ነዳጅ ላይ የሚደረገው ግብር በእጥፍ የሚያድግ ሲሆን ለቤት ኢንቨስትመንት ደግሞ ከእያንዳንዱ ተቀጣሪ የ1.5 በመቶ የግብር ጭማሪ ይደረጋል።
መንገግሥት አዲሱ የግብር ማሻሻያ አገሪቱ ያለባትን ብድር ለመክፈል እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል የሚል ሃሳብ አቅርቧል። ነገር ግን ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በሚል ፍርድ ቤት ለጊዜው አግዶታል።
- በግብፅ ካይሮ በተከሰተ ግጭት አንድ ኢትዮጵያዊ ሲገደል፣ ሰባት ጉዳት ደረሰባቸውከ 5 ሰአት በፊት
- በኬንያ የግብር ጭማሬን ለመቃወም በወጡ ሰልፈኞች ላይ በተከፈተ ተኩስ አንድ ሰው ተገደለ12 ሀምሌ 2023
- ወሲባዊ ይዘት ላላቸው ፎቶዎች ከፍሏል የተባለው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሆስፒታል ገባከ 4 ሰአት በፊት
ባለፈው ዓመት በተደረገው ምርጫ በፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የተሸነፉት ዋነኛው ተቃዋሚ ራይላ ኦዲንጋ፣ የግብር ማሻሻያው እንዳይጸድቅ ሕዝባዊ እምቢተኝነትን ጠርተዋል። በሌላ በኩል ይህንን ተላልፈው ሕጉን የሚያጸድቁትን አካላት ደገግሞ “ከሃዲዎች” ብለዋቸዋል።
የትናንትናውን ሰልፍ ተከትሎ ፖሊስ ሰልፉን ለመበተን ሁሉም ሕጋዊ አማራጮች ጥቅም ላይ ይውላሉ ብሏል።
ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለትም ተመሳሳይ ሰልፍ ተካሂዶ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰልፈኞች ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል። የሰብዓዊ መብት ተቋማት ፖሊስ ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሟል በማለት ወንጅለዋል።
ኬንያውያን በአደባባይተቃውሞው ላይ የተከፋፈለ ሃሳብ አላቸው። አንዳንዶቹ በየጊዜው ከሚጨምረው የኑሮ ውድነት አንጻር ሰልፉን ይደግፉታል።
በሌላ በኩል ደግሞ የአደባባይ ተቃውሞውን ለዝርፊያ ማስፈጸሚያ አድርገውታል በማለት ይነቅፋሉ።
ወጣቶች በቡድን እየተደራጁ ሱቆቹንና መጋዝኖችን በኃይል ሰብሮ በመግባት ዘረፋ ፈጽመዋል። በዚህ ምክንያት የተቃውሞውን አለመካሄድ የሚደግፉ ኬንያውያንም አሉ።