
ከ 1 ሰአት በፊት
ተቀማጭነታቸው በቻይና የሆኑ መረጃ መንታፊዎች የአሜሪካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ የ25 ተቋማትን የኢሜል ልውውጥ መጥለፋቸውን ማይክሮሶፍት አስታውቋል።
ማይክሮሶፍት ግን በጥቅሉ መረጃ ምዝበራው ተከናውኗል ከማለት ውጭ የትኞቹ ተቋማት ምዝበራ እንደተፈጸመባቸው ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
የአሜሪካ የንግድ ሚንስቴር ግን ከመረጃ ምዝበራው ጋር ተያይዞ በማይክሮሶፍት መረጃ እንደደረሰው ለቢቢሲ አረጋግጧል።
እንደሪፖርቱ ከሆነ የመረጃ ምዝበራው ከተፈጸመባቸው ግለሰቦች መካከል የንግድ ሚንስትሯ ጂና ራይሞንዶ አንዷ ነች። የንግድ ሚንስቴሩ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ “ማይክሮሶፍት ኦፊስ 365 ሥርዓት ችግር እንደገጠመው ማይክሮሶፍት ካስታወቀን በኋላ ወዲያውኑ እርምጃ ወስደናል” ብለዋል።
የመረጃ ስርዓታቸውን እየፈተሹ መሆናቸውን የገለጹት ቃለ አቀባዩ፣ ተጨማሪ ነገር ከተገኘ ወዲያውኑ ርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።
የአሜሪካ ብዙኃን መገናኛዎች እንደዘገቡት ደግሞ በመረጃ ምዝበራው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትም ጥቃት ከደረሰባቸው ተቋማት መካከል ነው። ቢቢሲ ለመሥሪያ ቤቱ ያቀረበው ጥያቄ ግን ምላሽ አላገኘም።
በለንደን የቻይና ኢምባሲ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሰጠው ምላሽ “የተዛባ መረጃ ነው” ብሎታል።
ኤምባሲው በተጨማሪም “በዓለም ትልቁ የመረጃ መዝባሪ እና የሳይበር ሌባ የአሜሪካ መንግሥት ነው” ብሏል። ማይክሮሶፍት እንደሚለው መቀመጫቸውን ቻይና ያደረጉ የመረጃ መንታፊዎች “ስቶርም-0558” በመባል የሚታወቁ ሲሆን፣ በስልክ የሚላኩ የማጣሪያ ኮዶችን በማጥፋት ነው ይህንን ምዝበራ የፈጸሙት።
“ስቶርም-0558 በዋናነት የመንግሥት ተቋማትን መረጃ ለመዝረፍ የሚሰሩ ሲሆን ትኩረታቸውም ምዕራብ አውሮፓ ነው” ብሏል ማይክሮሶፍት።
- በግብፅ ካይሮ በተከሰተ ግጭት አንድ ኢትዮጵያዊ ሲገደል፣ ሰባት ጉዳት ደረሰባቸውከ 5 ሰአት በፊት
- በግብፅ ካይሮ በተከሰተ ግጭት አንድ ኢትዮጵያዊ ሲገደል፣ ሰባት ጉዳት ደረሰባቸውከ 5 ሰአት በፊት
- የተባበሩት መንግሥታት ኤድስን በቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ውስጥ ከዓለም ማጥፋት ይቻላል አለከ 5 ሰአት በፊት
ኩባንያው በሰጠው መረጃ መሰረት መዝባሪዎቹ ይህንን ተግባር የጀመሩት ግንቦት አጋማሽ አካባቢ ሲሆን፣ አሁን ላይ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ተቋማት መረጃ በመስጠት ጉዳቱን መቆጣጠር መቻሉን ገልጿል።
“ጥቃት ሲደርስ ወዲያውኑ መረጃ የሚሰጥ ስርዓት ዘርግተናል። ከዚያ በኋላ ግን ምንም የምዝበራ መረጃ አልደረሰንም” ብሏል ማይክሮሶፍት።
በግንቦት ወር ማይክሮሶፍት እና የምዕራባውያን የስለላ ተቋማት የቻይና መረጃ ሰርሳሪዎች ጉዋም ከሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር ወሳኝ የመረጃ መሰረተ ልማቶችን ለመዝረፍ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው ነበር።
ባለሙያዎች እንደሚሉት በአሜሪካ ላይ ከተፈጸሙ የመረጃ ምዝበራ ሙከራዎች ይህኛው ትልቁ ነው።
ቤጂንግ በማይክሮሶፍት በኩል የቀረበውን ክስ “በእጅጉ ሙያዊ እይታ የተሳነው” እና “የተዛባ መረጃ” በማለት አጣጥላዋለች።
መረጃዎች ቢገኙም ወይም አመላካች ሁኔታዎች ቢታዩም ቻይና በተደጋጋሚ እንደዚህ አይነት ክሶችን ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።