የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና የያዘች ሴት
የምስሉ መግለጫ,የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና መድኃኒቶች የበሽታውን መስፋፋት በመግታት በኩል ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አላቸው

ከ 5 ሰአት በፊት

አዲስ የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚለው መሠረታዊ የጤና ፕሮግራሞችን በገንዘብ መደገፍ ከተቻለ ኤድስን በአውሮፓውያኑ 2030 ከዓለም ማጥፋት ይቻላል።

በዓለማችን ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ከሚገኝ ጠቅላላ ሕዝብ 65 በመቶ የሚሆኑት ባሉባቸው ከሰሃራ በታች አገራት እንኳ ይህንን ዕቅድ የማሳካት ዕድላቸው ሰፊ ነው ብሏል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የኤችአይቪ/ኤድስ የተቀናጀ ዓለም አቀፍ እርምጃ (ዩኤንኤድስ) ከሆነ ቦትሰዋና፣ ኢስዋቲኒ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ዚምባብዌ 95-95-95 ተብሎ የሚጠራውን ዕቅድ ማሳካት ችለዋል።

95-95-95 ማለት ቫይረሱ ካለባቸው አጠቃላይ ሰዎች ውስጥ 95 በመቶ ስላሉበት የበሽታው ደረጃ ያውቃሉ፣ ቫይረሱ በደማቸው መኖሩን ከሚያውቁት መካከል 95 በመቶው የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት እየወሰዱ ነው፣ ሕክምናውን እየወሰዱ ካሉት መካከል ቫይረሱን ወደ ሌሎች በማያስተላልፉበት ደረጃ የሚገኙት 95 በመቶ ደርሰዋል ማለት ነው።

ከላይ ከተጠቀሱት አምስት የአፍሪካ አገራት በተጨማሪ ሌሎች ተጨማሪ 16 አገራት፤ ስምንቱ ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገራት ናቸው፤ እንዲሁ ይህን 95-95-95 የተባለውን ዕቅድ ለማሳካት ተቃርበዋል።

የዩኤንኤድስ ዋና ዳይሬክተር ዊኒ ብያኚማ፣ ኤድስን ማስቆም አሁን ላይ ያሉ መሪዎች ሊታወሱ የሚችሉበት ትልቅ ቅርስ ይሆናቸዋል ይላሉ።

“የሚሊዮኖችን ሕይወት ከመታደጋቸውም በተጨማሪ የበርካቶችን ጤና ይጠብቃሉ። አመራርነት ምን ማለት እንደሆነ ማሳየትም ይችላሉ።”

ይሁን እንጂ ተመድ እያደጉ ባሉ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ለሚያደርገው የፀረ ኤድስ እንቅስቃሴው እስከ 2025 ድረስ ለሚያከናውናቸው ሥራዎቹ የ8.5 ቢሊዮን ዶላር እጥረት አለበት።

እአአ 2022 ላይ በየደቂቃው በኤድስ ምክንያት አንድ ሰው እየሞተ ሳለ ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚደረገው ጥረት እንደሚፈለገው ውጤታማ ላይሆን ይችላል።

“በዚህ ሪፖርቶች የተገለጹት እውነታዎች እና አሃዞች እንደ ዓለም በትክክለኛው መንገድ ላይ ነን ማለት አይደለም፤ ግን አሃዞቹ የሚያሳዩት ትክክለኛው መንገድ ላይ [ኤድስን ለማጥፋት] መሆን እንችላለን የሚለውን ነው” ይላሉ የዩኤንኤድስ ዋና ዳይሬክተር ዊኒ ብያኚማ።

የበለጠ ተጋላጭ የሆኑት ወጣት ሴቶች

የመንግሥታቱ ድርጅት የኤድስ ስርጭትን በጥቂት ዓመታት ውስጥ መቆጣጠር ይቻላል ቢልም፣ አሁንም ግን ከቫይረሱ ሥርጭት ጋር በተያያዘ በርካታ ፈታኝ ጉዳዮች መኖራቸውን ይገልጻል።

በየሳምንቱ በጉርምስ እና ዕድሜ ውስጥ (ከ10 እስከ 19) እና በወጣትን ዕድሜ ውስጥ ያሉ 4 ሺህ ሴቶች በኤችአይቪ ይያዛሉ።

ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ምንም እንኳ አዎንታዊ ለውጦች ይመዝገቡ እንጂ፣ እአአ 2022 ላይ በመላው ዓለም በቫይረሱ ከተያዙ አጠቃላይ ሰዎች መካከል 63 በመቶ የሚሆኑት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የሚገኙ በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ናቸው።

በደቡባዊ አፍሪካ በምትገኘው ቦትስዋና ለምሳሌ በዕድሜ የገፉ ወንዶች፣ ተጋላጭ የሆኑ ወጣት ሴቶችን ለቫይረሱ ያጋልጣሉ።

በአሁኑ ወቅት የ32 ዓመት ወጣት የሆነችው ጋኦኔ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ነበር ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆነችው።

“አንድ በጣም የቅርብ ዘመዴ ብዙ ይረዳኝ ነበር። በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ነበር። በዚያን ጊዜ በዕድሜ በእጥፍ ይበልጠኝ ነበር። አምነው ነበር። ልጅነቴን መጠቀሚያ አድርጎ ከእኔ ጋር ወሲብ ይፈጽም ነበር” ትላለች።

የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ጋኦኔ ከእአአ 2012 ጀምሮ የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና ስትወስድ ቆይታለች። ሁለቱ ልጆቿ ከኤችአይቪ ነጻ ሲሆኑ ፣ እሷም በፀረ ኤችአይቪ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ ነች።

እርሷ እንደምትለው አሁን ድረስ የምትኖርበት ማኅብረሰብ ስለ ‘መደፈር’ እና ‘ጾታዊ ጥቃቶች’ በግልጽ ለማውራት ዝግጁ አይደለም።

“አንዳንድ ጊዜ እስከ አምስት የሆኑ ሴቶች ዘመዶቻቸው የሆኑ እና በዕድሜ የሚበልጧቸው ሰዎች ኤችአይቪ እንዳስያዟቸው መልዕክት ይልኩልኛል። ወንዶቹ ከዚህ ተግባራቸው ካልተቆጠቡ ምን ማድረግ ይቻላል” ስትል ትጠይቃለች።

ኤድስ ይቁም የሚል መልዕክት

አሃዞች እንደሚያሳዩት ቫይረሱ ካለባቸው ሴቶች በላይ ወንዶቹ የሕክምና ድጋፍ ለማግኘት ብዙ ያንገራግራሉ።

ቦትስዋና ይህንን የወንዶችን አመለካከት ለመቀየር እና የኤችአይቪ ሥርጭትን ለመቀነስ ፊቷን ወደ ሃይማኖት መሪዎች አዙራለች።

“በቦትስዋና 95 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ኤችአይቪ ይኑርበት ወይም አይኑርበት ያውቃል። ኤችአይቪ ያልተመረመሩት አብዛኛው ወንዶች ናቸው” ይላሉ የሃይማኖት መሪው ቄስ ማቻክግ ሞሩክጎሞ።

ሰዎች የሃይማኖት መሪዎችን ስለሚያከብሩ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ወንዶች ምርመራ እንዲያደርጉ እና ቫይረሱ ካለባቸው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የሃይማኖት መሪው ይናገራሉ።

የክርስትና ሃይማኖት መሪው ቄስ የእስልምና፣ የሂንዱ፣ የበሃኢ እንዲሁም የባህል ሃኪሞችን ያካተተ ቡድን በዚህ ጥረት ተሳታፊ መሆኑን ይገልጻሉ።

የቦትስዋና ብሔራዊ የኤድስ እና ጤና ተቋም ኃላፊ ኦንቲሬትስ ሌትለሃሬ አገራቸው ኤድስን በ2030 (እአአ) ለማጥፋት ትክክለኛው መንገድ ላይ ነች ካሉ በኋላ፣ የሃይማኖት መሪዎችም ለዚህ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ይላሉ።

እንደ ኃላፊው ከሆነ መሠረታዊ የሆነው ቁልፍ ጉዳይ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች ላይ መገለል እንዳይደርስ እና ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች የሕክምና አገልግሎት ከማግኘት እራሳቸውን እንዳይቆጥቡ ማድረግ ነው።

የኤችአይቪ ክትባት
የምስሉ መግለጫ,ከዚህ ቀደም በየትም ቦታ ያልተሞከረው የኤችአይቪ ክትባት በኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ደቡብ አፍሪካ እየተከናወነ ይገኛል።

የተቀረው ዓለም

በቀጣይ ዓመታት ኤችአይቪን ለማጥፋት በተያዘው ዕቅድ በእስያ እና ፓስፊክ አገራት የመሳካቱ ዕድል ከተቀረው ዓለም ጋር ሲነጻጸር አናሳ ነው።

በምሥራቅ አውሮፓ፣ በመካከለኛው እስያ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ አሁንም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት በእነዚህ አካባቢዎች የቫይረሱ ስርጭት እንዳይቀንስ ምክንያት የሆኑት ሁለት ዋነኛ ነገሮች ናቸው።

እነዚህም የተገፉ የሕብረሰብ ክፍሎች የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኙ እና እንዲገለሉ መደረጋቸው እንዲሁም የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት በሕግ ወንጀል ሆኖ መደንገጉ ነው።

ይሁን እንጂ ሰዎችን በኤችአይቪ የመያዝ ዕድላቸውን የሚቀንሱ እና ቀድመው የሚወሰዱ ፕሪ-ኤክስፖዘር፣ ፕሮፊላክሲስ (ፕሬፕ) የተባሉ እንክብል መድሃኒቶች ለሰዎች ተስፋን እየሰጡ ነው።

በምሥራቅ እስያዋ አገር ካምቦዲያ ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ በወሲብ ንግድ ላይ ለተሰማሩ እና ለተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች እነዚህ እንክብሎች በነጻ ይታደላሉ።

እነዚህ የመከላከያ እንክብሎችን ቫይረሱ የሌለባቸው ሰዎች በየዕለቱ የሚወስዷቸው ከሆነ በቫይረሱ የመያዝ ዕድላቸውን ይቀንሳሉ።

“ይህን መድኃኒት ለሦስት ተከታታይ ወር ወስጃለሁ። በመጀመሪያዎች ቀናት ራስ ምታት ነበረብኝ፣ ከዚያ በኋላ ግን ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት አላጋጠመኝም። በቀን አንድ ክኒን እወስዳለሁ” ትላለች ጾታዋን ከወንድ ወደ ሴት የቀየረችው የ32 ዓመቷ ኩይ ፖቭ።

የኤድስ አርማ

“ፕሬፕ የምወስደው ከብዙ ሰዎች ጋር ወሲብ ስለምፈጽም ነው። ለቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ እንደሆንኩ አውቃለሁ” የምትለው ኩይ፣ የወሲብ አጋሮቿ ሁልጊዜ ኮንዶም እንዲጠቀሙ ብትጠይቅም ሁሉም ፍቃደኛ ላይሆኑ እንደሚችሉ ታስረዳለች።

ካምቦዲያ ቫይረሱ በደማቸው ያለ በግምት 76ሺህ ሕዝብ ይኖርባታል። ከአጠቃላይ ሕዝቧ 86 በመቶው ቫይረሱ በደማቸው ይኑር ወይም አይኑር በምርመራ አውቀዋል።

እአአ 1996 ከነበረው አሃዝ ጋር ሲነጻጸር በካምቦዲያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ91 በመቶ ቀንሷል። አሁን ላይ በቀን 4 ሰዎች ብቻ በቫይረሱ እንደሚያዙ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም ለካምቦዲያ ትልቅ ስጋት ሆኖ ቀጥሏል።

“ከዚህ በፊት ሰዎች ኮንዶም እንዲጠቀሙ ነበር የሚበረታቱት፣ ነገር ግን ለመጠቀም ፍቃደኛ ያልሆኑ አሉ። ስለዚህ ፕሬፕ መድኃኒቶች በሕብረተሰቡ ውስጥ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ሌላኛው አማራጭ ሆኗል” ይላሉ መንግሥታዊ ድርጅት ላልሆነ ተቋም የሚሰሩት የጤና ባለሙያው ዳኖኡ ቻይ።

እነዚህ እንክብሎች አበረታች የሆነ ውጤት እያመጡ መሆኑን የሚገልጹት የጤና ባለሙያው፣ በመርፌ መልክም ሌላ አማራጭ ይዞ የመቅረብ ዕቅድ እንዳለ ይናገራሉ።

ይህ አዲሱ አማራጭ ለኩይ እራሷን እንድትጠብቅ ዕድል ሰጥቷል።

በቅርቡ ባደረገችው የኤችአይቪ ምርመራ ቫይረሱ እንደሌለባት ማወቋም እረፍ ሆኗታል።