
ከ 5 ሰአት በፊት
በግብፅ መዲና ካይሮ በአንድ ኢትዮጵያዊ እና በግብፃዊ መካከል በተከሰተ ጸብ አንድ ኢትዮጵያዊ ሲገደል ሌሎች ሰባት ደግሞ መቁሰላቸውን በቦታው የነበረ የዐይን እማኝ እና የማኅበረሰብ ተወካይ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የዐይን እማኝ እንደገለጹት በግለሰቦች መካከል የተከሰተው ግጭት ሰፍቶ ነው ለኢትዮጵያዊው ሞት እና ለበርካቶች መጎዳት ምክንያት ለመሆን የበቃው።
በግብፅ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጣሂር ዑመር በግጭቱ የአንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ሕይወት ማለፉን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የጸቡ መነሻ “ባጃጅ የሚነዳ ግብፃዊ፤ የኢትዮጵያዊ ከሆነ ሱቅ ፊትለፊት የተቀመጠ ከሰል ረግጦ ያልፋል። ባለሱቁም ኢትዮጵያዊ ከሰሉን ረግጠህ አድቅቀህብኛል” በሚል እንደሆነ የዐይን እማኙ ገልጸዋል።
ይህ የሁለቱ ግለሰቦች ውዝግብ ወደ ግብግብ ሲሸጋገር በቦታው የነበረ ሌላ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ጸቡን ለመገላገል መሐል በገባበት ጊዜ ግብፃዊው ስለት አውጥቶ ደረቱን እንደወጋው በስፍራው ነበርኩ ያሉት የዐይን እማኝ ተናግረዋል።
ግርግሩ እንደተከሰተ የግብፃዊው ግብረ አበሮች ወደ ቦታው ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያውያን እና በአገሪቱ ዜጎች መካከል የነበረው ግጭት መስፋቱን ጨምረው ገልጸዋል።
“ልጁ የተወጋው በግራ በኩል ደረቱ ላይ ነው። የመጀመሪያ እርዳታ የሚሰጡ ሐኪሞች ከስፍራው ሲደርሱ ልጁ ሕይወቱ አልፎ ነበር። ምንም አይነት እንቅስቃሴ አያደርግም ነበር።”
የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ሰብሳቢው አቶ ጣሂር፣ ግጭቱ መከሰቱን በመግለጽ በ20ዎቹ አጋማሽ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ባለትዳር እና በባጃጅ ሹፌርነት ይታዳደር የነበረው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በስለት ተወግቶ መሞቱን አረጋግጠዋል።
ሰኞ ዕለት በተከሰተው የግለሰቦች ፀብ እና እሱን ተከትሎ በኢትዮጵያውያን እና በግብፆች መካከል በተፈጠረው ግጭት ከተገደለው ወጣት ስደተኛ በተጨማሪ ሰባት ኢትዮጵያውያን በስለት ጉዳት እንደደረሰባቸው የዐይን እማኙ ተናግረዋል።
- አፍሪካን እና አፍሪካውያንን ብዙ እያሳጣቸው ያለው እጅግ ውዱ የአየር ቲኬት ዋጋ12 ሀምሌ 2023
- የአዳዲስ ክልሎች መፈጠር በደቡብ ኢትዮጵያ ሲነሳ ለቆየው ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል?12 ሀምሌ 2023
- ከቀበሌ ጥበቃ እስከ ፕሮፌሰርነት የደረሰው የዶ/ር እውነቱ ኃይሉ የሕይወት ጉዞ11 ሀምሌ 2023
በክስተቱ ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ሕክምና ቦታ መወሰዳቸውን የገለጹት ይህ የዐይን እማኙ፣ በግብፃውያኑ በኩል የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የሚያውቁት ነገር እንደሌላ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ግጭቱ ባጋጠመበት መዓዲ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ የዐይን እማኙ እና የኢትዮጵያውያን ማኅብረሰብ ተወካዩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት “ከጥቃቱ በኋላ በስፍራ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጡ። ኢትዮጵያውያኑ በግድያው ተቆጥተው ወደ ጎዳና በመውጣት ለበርካታ ሰዓታት ቁጣቸውን ገልጸዋል። ትልቅ ረብሻ ተከስቶ ነበር” ብለዋል የዐይን እማኙ።
ይህንንም ክስተት ተከትሎ የተወሰኑ ፖሊሶች ከስፍራው ቢደርሱም ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ የወጣ ሲመስል በሁለት መኪኖች ተጨማሪ የፖሊስ አባላት በአካባቢው ተሰማርተው እንደነበር ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያውያኑን ቁጣ ለማብረድ ፖሊስ ከማኅበረሰቡ ተወካዮች ጋር በመነጋገር የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው ግብፃዊ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ከተገለጸ በኋላ ሁኔታው ለመረጋጋት ችሏል።
የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጣሂር ዑመር የሟቹ የቀብር ሥነ ሥርዓት እዚያው ካይሮ ውስጥ በሚገኝ ኮዚካ በሚባል የቀብር ስፍራ በቤተሰቡ ፈቃድ መፈጸሙን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሟቹ ወጣት ከሰባት ዓመት በላይ በሕጋዊ ስደተኝነት ግብፅ ውስጥ የቆየ ሲሆን፣ ባለትዳር እና በባጃጅ ሹፌርነት ሕይወቱን ሲመራ መቆየቱን አቶ ጣሂር ተናግረዋል።
በግድያው የተጠረጠረው ግብፃዊ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ አረጋግጠው፣ የኢትዮጵያውያኑ ማኅበረሰብ ጠበቃ በመቅጠር ጉዳዩን ለመከታተል ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ጨምረውም የሟች መርዶ ለቤተሰብ ተነግሮ እዚያው እንዲቀበር በመፍቀዳቸው ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ሥርዓተ ቀብሩ መፈጸሙን ገልጸዋል።
በቀብሩ ወቅትም ችግር እንዳይከሰት በርካታ ፖሊሶች ተሰማርተው ቀብሩ በሰላም ተፈጽሞ ወደ መጡበት መመለሳቸውን አረጋግጠዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ ካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚያውቀው ነገር ስለመኖሩ አቶ ጣሂር እርግጠኛ እንደልሆኑ ገልጸዋል።
ቢቢሲም ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በኤምባሲው በኩል ያለውን ተጨማሪ መረጃ ለማወቅ ያደረገው ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ ሳይሳካ ቀርቷል።
በግብፅ ውስጥ ከ15 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የሚገኙ ሲሆን፣ የተወሰኑት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተመዝግበው አገሪቱን ወደ ሌላ ሦስተኛ አገር መሸጋገሪያነት ይጠቀሙባታል።
በተጨማሪም በርካቶቹ ሴት ኢትዮጵያውያን በቤት ሠራተኝነት፣ ወንዶቹ ደግሞ በምግብ ቤቶች፣ በካፍቴሪያዎች እና በግንባታ ስፍራዎች ተቀጥረው እንደሚሰሩ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ያመለክታሉ።