
ከ 1 ሰአት በፊት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በአካባቢያዊ እና በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ካይሮ ውስጥ መወያየታቸውን የአገራቱ መሪዎች ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ።
በሱዳን በተከሰተው ቀውስ ላይ ጎረቤት አገራት ዛሬ ሐሙስ ይካሄዳል በተባለው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ካይሮ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር ትናንት ሐምሌ 05/2015 ዓ.ም ከግብፅ ፕሬዝዳንት እና ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣንት ጋር ተወያይተዋል።
ረቡዕ ሐምሌ 05/2015 ዓ.ም. ማምሻውን በግብፁ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ከፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር “በትብብር መንፈስ ቁልፍ በሆኑ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ” መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አስፍሯል።
የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ሁለቱ መሪዎች በአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ እና ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ መነጋገራቸውን አመልክቷል።
ወራትን ያስቆጠረ ጦርነት እየተካሄደባት ካለው ሱዳን ጋር የሚጎራበቱት ኢትዮጵያ እና ግብፅ ቀውሱ መፍትሔ እንዲያገኝ በየበኩላቸው ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ተቋም አማካይነት የአካባቢው አገራት መሪዎች እንዲሁም የሌሎች አገራት፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ተወካዮች የተሳተፉበት ተመሳሳይ ስብሰባ ተደርጎ ነበር።
ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ ከዛሬ ሐሙስ ጀምሮ በፕሬዝዳንት አል ሲሲ አስተናጋጅነት ‘የሱዳን ጎረቤት አገራት ስብሰባ’ ካይሮ ውስጥ ይካሄዳል።
በዚህ ስብሰባ ላይ በሱዳን ያለው ግጭት በሚያበቃበት ሁኔታ እና በአጎራባች አገራት ላይ ያለውን ትጽእኖ ለማስወገድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ አካላት እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር ካይሮ ውስጥ አሁን ሲገናኙ ከረጅም ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በካይሮ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ምክንያት ውዝግብ ውስጥ ቆይተዋል።
- በአዲስ አበባው የኢጋድ ስብሰባ ላይ ወደ ሱዳን ሰላም አስከባሪ የማሰማራት ሐሳብ ቀረበ10 ሀምሌ 2023
- በአዲስ አበባ ድርድር በታሰበበት ጊዜ በካርቱም በተፈጸመ የአየር ጥቃት ቢያንስ 22 ሰዎች ተገደሉ9 ሀምሌ 2023
- “ከዚህ ምስኪን ሕዝብ አንድ ብር አንሰርቅም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ6 ሀምሌ 2023
ግብፅ ግድቡ ከአባይ ወንዝ የማገኘው የውሃ መጠንን ይቀንስብኛል በማለት በግድቡ ዙሪያ ያላትን ተቃውሞ አስከ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ወስዳዋለች።
ግብፅ ከሱዳን ጋር በመሆን የግድቡ ውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት መደረስ አለበት ስትል ብትቆይም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ግድቡን በውሃ የመሙላት ሥራ ስታከናውን ቆይታለች።
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩት፣ በዚህ ዓመት የሚካሄደው የውሃ ሙሌት የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ፍላጎት ባገናዘበ ሁኔታ አስከ መስከረም ድረስ እንደሚከናወን ገልጸው ነበር።
የሁለቱ አገራት መሪዎች በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው መካከል በግድቡ ዙሪያ ውይይት ሲያደርጉ የቆየ ቢሆንም፣ ንግግሩ ከተቋረጠ ከረጅም ጊዜ በኋላ አሁን ሁለቱ መሪዎች ጉዳዩን ማንሳታቸው ተነግሯል።
በኢትዮጵያ በኩል ሁለቱ መሪዎች የሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ንግግር መደረጉን ሲያመለክት፣ በግብፅ በኩል ይህንን በማረጋገጥ የግድቡ ጉዳይ መነሳቱ ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታ እና ሙሌት ሳይቋረጥ ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር ንግግር ለማድረግ ፍላጎት እናዳለት በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷ ይታወሳል።
ግብፅ እና ሱዳን ግን ከሁሉ በፊት ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት መደረግ አለበት በማለት የኢትዮጵያን የንግግር ጥያቄ ሲተቹ ቆይተዋል።