በቄለም ወለጋ ዞን የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በባንኮች እና በንግድ ቤቶች ላይ ዝርፊያ መፈጸማቸው ተገለጸ
በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን መቻራ፣ ሰደን ጨንቃ እና ሀዋ ገላን ወረዳዎች ሰኞ ሐምሌ 04/2015 ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በማለት የሚጠራው እና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ በመባል በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድን በባንኮች እና በግለሰብ የንግድ ቤቶች ላይ ዝርፊያ መፈጸሙን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ሐምሌ 04/2015 ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትና እና በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ ውጊያ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
በተለይም በመቻራ ከተማ የታጣቂ ቡድኑ አባላት በባንኮች እና በግለሰብ የንግድ ቤቶች ላይ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ ሲፈጽሙ ነበር ነው የተባለው።
ሆኖም በታጣቂ ቡድኑ የደረሰውን የዝርፊያና የውድመት መጠን ማወቅ ያልተቻለ ሲሆን፤ በከተማው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መካከል ሲደረግ በነበረው ውጊያ፣ የንጹሃን ዜጎች ሕይወት መጥፋቱ እና የአካል ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በዞኑ ወደ ደምቢ ዶሎ በሚወስደው መንገድ ላይ በምትገኘው ዕሮብ ገበያ ከተማ፤ ከፍተኛ ሆነ የተኩስ ልውውጥ በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መካከል ሲደረግ ነበርም ተብሏል።
በዚህ ውጊያም የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን እና የጦር መሳሪያ ሳይማርኩ እንዳልቀሩ ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።
አክለውም ታጣቂ ቡድኑ በመቻራ ከተማ አቅራቢያ ትልቅ ካምፕ እንዳለው ጠቅሰው፤ በእዚያው አቅራቢያ የአገር መከላከያ ሠራዊት ካምፕ መኖሩንም ገልጸዋል።
ላለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት በስፍራው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት አብዛኞቹ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው መውጣታቸው የተነገረ ሲሆን፤ አሁን ላይ ቁጥራቸው ጥቂት የሚባሉ ዜጎች ብቻ በቦታው እንደሚኖሩ ነው የተጠቆመው።
በአካባቢው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱ መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ ውጥረት መኖሩም ተመላክቷል።
ታጣቂ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎችን አፍኖ የወሰደው በዚሁ አካባቢ ጥር 2012 ላይ መሆኑን ያወሱት ነዋሪዎቹ፤ ያገተውም በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ የነበሩ 18 ተማሪዎችን መሆኑን አውስተዋል።
በወቅቱ በኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንድ ተማሪ ከማምለጧ በስተቀር ቀሪዎቹ እስካሁን ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ከአካባቢው የመንግሥት አካላት ምላሽ ለማግኘት ጥረት ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡