የታሰረ ሰው

13 ሀምሌ 2023, 12:57 EAT

በኢትዮጵያ የዜጎች አስገድዶ መሰወር፣ ተጠርጣሪዎችን በጭካኔ፣ በአዋራጅ እና ኢሰብዓዊ በሆነ መልኩ አያያዝ መጨመሩን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

ኢሰመኮ በተጨማሪም በአገሪቷ ውስጥ ያሉ የኢመደበኛ ማቆያ ቦታዎች መበራከት እንዲሁም ከሕግ ውጪ የሆኑ የዘፈቀደ እስሮች እጅግ አሳሳቢ መሆናቸውን አመልክቷል።

ኢሰመኮ በአገሪቱ ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን በተመለከተ 106 ገጾች ያሉትን ዓመታዊ ሪፖርቱን ረቡዕ ሐምሌ 05/ 2015 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል።

ሪፖርቱ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰቱ ግጭቶች ያስከተሏቸውን መብታዊ ጥሰቶች፣ በፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች ላይ የሚፈጸሙ እስሮችና ወከባዎች መጨመር፣ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት መገደብ እና ሌሎች ጉዳዮችን ዘርዘር ባለ መልኩ አካቷል።

በታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች እርምጃዎች የዜጎች ሞት

በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ከነበሩ እና በአብዛኛው በቀጠሉ ግጭቶች፣ ጥቃቶች እና ሁከቶች ጋር ተያይዞ ታጣቂ ኃይሎች እና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዷቸው እርምጃዎች ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል፣ እንዲሁም ለአካል ጉዳት መጋለጣቸው አስፍሯል።

ሪፖርቱ የመዘገባቸው እነዚህ የፀጥታ መደፍረሶች ከሐምሌ 1/ 2014 እስከ ግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. እንደሆነም አትቷል።

የሰላማዊ ዜጎች የሕይወት ህልፈት እና ጉዳት የተከሰተውም በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ በምሥራቅ ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በሰሜን ሸዋ እና በሌሎችም አካባቢዎች እንደሆነም ተጠቅሷል።

በአማራ ክልል ከጥቂት ወራት በፊት የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና ለማዋቀር ከታያዘው የመንግሥት ዕቅድ ጋር በተገናኘ የተከሰተው የፀጥታ ችግር አሳሳቢ እንደሆነም ሪፖርቱ አመልክቷል።

በሪፖርቱ እንደ ዋቢ ሆኖ ከተገለጸውም ውስጥ ግንቦት 11/ 2015 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ ዞን የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው የኃይል እርምጃ ቢያንስ 5 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

በዚሁ ዞን ራሳ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ መከላከያ ትጥቅ ማስፈታት በሚል በወሰደው እርምጃ አንድ ካህንን ጨምሮ ሰባት ነዋሪዎች ላይ ግድያ መፈጸሙም ተካትቷል።

ሪፖርቱ የመንግሥት የፀጥታ አካላት የሚወሰዷቸው ተመጣጣኝ ያልሆኑ የኃይል እርምጃዎች ለሰዎች ሞት እና ጉዳት ምክንያት መሆናቸውን ለማመላከት ሌላኛው ያነሳው በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ ዕለት የደረሰውን የሰው ሕይወት መጥፋት ነው።

ኢሰመኮ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ የሰው ሕይወት ጠፍቷል እንዲሁም የአካል ጉዳት ደርሷል ብሏል።

በተጨማሪ በሸገር ከተማ መስጊድ መፍረስ ጋር በተያያዘ በተነሳው ተቃውሞ የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ እንዲሁም በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ለውሃ ችግራቸው እልባት እንዲሰጣቸው ለተቃውሞ በወጡ ነዋሪዎች ላይ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ሦስት ሰዎች መገደላቸውም ሰፍሯል።

የዘፈቀደ እስር እና አስገድዶ መሰወር

ኢሰመኮ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የደረሱትን አቤቱታዎች እና ጥቆማዎች መሠረት ባደረገው ክትትሎች አስገድዶ መሰወር እየተፈጸሙ መሆኑን መረጃዎች አግኝቷል።

አብዛኞቹ የአስገዳጅ ስወራ ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታ ወይም ከመንገድ ላይ የሲቪል እና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ፀጥታ እና ደኅንነት ሠራተኞች መወሰዳቸውም ተመልክቷል።

ግለሰቦቹ ያለ ፍርድ የመያዣ ትዕዛዝ ተይዘው ከታሰሩ በኋላም ወዳልታወቀ ስፍራ እንዲሰወሩ መደረጉም ተገልጿል። የተወሰኑት ከቀናት፣ ከሳምንታት ወይም ከወራት መሰወር በኋላ የተገኙ ቢሆንም፣ በግዳጅ እንደተሰወሩ የቀጠሉ በርካታ መሆናቸውንም ነው ሪፖርቱ አመልክቷል።

በግዳጅ ከተሰወሩት በርካቶቹ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ ከተራዘመ እስር በኋላ ፍርድ ቤት መቅረባቸውም ተገልጿል።

በተለይም በመከላከያ ሠራዊት አባላት ተይዘዋል የተባሉ ሰዎች ከመደበኛ ማቆያ ቦታዎች ውጪ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ እንደሚታሰሩ፣ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ እና የመጊብኘት መብታቸውን ተነፍገዋል ተብሏል።

በሶማሌ ክልል የቀድሞ ልዩ ኃይል የነበረ ግለሰብ ከወራት በፊት ትፈለጋለህ በሚል መሰወሩን ጨምሮ፣ ልዩ ኃይሎችን መልሶ ከማደራጀት ጋር በተያያዘ በማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ እስር እና አስገድዶ መሰወር መፈጸሙም ሰፍሯል።

በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦችም እንዲሁ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ እንደተሰወሩም ተካትቷል።

በማረሚያ ቤቶች እና በማቆያ ቦታዎች ጭካኔ የተሞላበት አያያዝ

በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ድብደባ እና ግርፋትን ጨምሮ ሌሎች ኢሰመኮ ኢሰብዓዊ እና አዋራጅ ተግባራት የሚፈጸሙባቸው እስር ቤቶች እና መደበኛ ያልሆኑ የማቆያ ቦታዎች እንዳሉ ተመልክቷል።

በሪፖርቱ ከተካተቱ ውስጥም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች 26 ሰዎች እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ ፓሊስ ጣቢያዎች 13 ተጠርጣሪዎች በፀጥታ ኃይሎች ድብደባ እና ጉዳት እንደገጠማቸው ተገልጿል።

“ጥፋታችሁን በግዴታ ማመን አለባችሁ” በሚል በተፈጸመ ድብደባ የጥርስ መውለቅ፣ በጎማ እና በሽቦ ግርፋት፣ “የማታምን ከሆነ እንገድልሃለን” በሚል አንድ ተጠርጣሪን በጉልበት አንበርክከው በጠጠር ላይ በመጎተት የግድያ ማስፈራሪያ እንዲሁም ሌሎች ስቅይቶች መፈጸማቸውን መዝግቧል።

በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙ እና አንዱን ወይም ሌላኛውን “ታጣቂ ቡድን ትደግፋላችሁ” በሚል ተጠርጠሪዎችን የማሰቃየት ተግባር በስፋት መፈጸሙንም አስፍሯል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልለ ፖሊስ ጣቢያዎች በተጠርጣሪዎች ላይ ድብደባ የተፈጸመ ሲሆን፣ የአዕምሮ ህመም ያለበት ተጠርጣሪን በካቴና ማሰር እንዲሁም ሌላ ግለሰብን ደግሞ በገጀራ መመታቱ ተካትቷል።

በጋምቤላ ክልልም እንዲሁም በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ ድብደባ እና ኢሰብዓዊ አያያዝ መኖሩን፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልልም እንዲሁም በተጠርጣሪዎች ላይ ዛቻ እና ማስፈራራት ተፈጽሟል ብሏል።

“መንግሥት አስቸኳይ እርምጃ ይውሰድ”

በዚህ ሪፖርት ከተካተተ ሌላኛው ጉዳይ በሚድያ አባላት፣ በፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች ላይ የሚፈጸሙ እስሮች፣ ወከባዎች እና ሌሎች እንግልቶች መጨመራቸውን ተጠቅሷል።

ኢሰመኮ “ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ የሲቪክ ምኅዳሩን በተመለከተ በርካታ አሳሳቢ ክስተቶች ተመዝግበዋል” ብሏል።

27 የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች እና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከሐምሌ 01/2014 ዓ.ም. ጀምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው አብዛኛዎቹ ከቀናት እስከ ወራት በእስር ላይ መቆያታቸውን ሪፖርቱ ገልጿል።

ሪፖርቱ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም በእስር ላይ የሚገኙ እና የወንጀል ክስ ቀርቦባቸው በክስ ሂደት ላይ ያሉ በርካታ መሆናቸውም ተጠቅሷል።

ኢሰመኮ እንደ ምክረ ሃሳብ ካቀረባቸው መካከል “በአገር አቀፍ ደረጃ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን ግጭቶችን የማስቆም ጥረቶች ሊጠናከሩ ይገባል” ብሏል።

በተለይም በክልሎች ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች ጋር የተጀመሩ ሰላም የማምጣት እንቅስቃሴዎች አበረታች እንደሆኑ ቢገልጽም፣ ዘላቂነታቸው እንዲረጋገጥ ተጎጂዎችን እና ሴቶችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊካተቱ ይገባል ብሏል።

ግጭቶችን በሰላም ለመቋጨት ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪም በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሱትን እና እየደረሱ ያሉትን የመብቶች ጥሰት ተጠያቂነት እና ፍትሕ የማስገኘት ጥረትም በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት መደረግ እንዳለበት አሳስቧል።

“የአስገድዶ መሰወር፣ የጭካኔ፣ አዋራጅ እና ኢሰብአዊ አያያዝ መጨመር፣ የኢመደበኛ ማቆያ ቦታዎች መበራከት እንዲሁም ከሕግ ውጪ የሆኑ የዘፈቀደ እስሮችም ሆኑ በመብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች እጅግ አሳሳቢ እና በሌሎች ነጻነቶች እና መብቶች ላይ እጅግ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚኖራቸው፣ አጠቃላይ አገራዊውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ ወደኋላ የሚጎትቱ ናቸው። በመሆኑም መንግሥት በአፋጣኝ ተገቢውን እርምጃዎች በመውሰድ ሊያስቆመው የሚገባ ነው” ብሏል የኢሰመኮ ሪፖርት።