
13 ሀምሌ 2023, 15:55 EAT
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የትግራይ አባቶች እናደርገዋለን ያሉት የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ሕገ ቤተክርስቲያንን ያልተከተለ በመሆኑ መንግሥት እንዲያስቆም ጠየቀ።
የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ያለው ሐምሌ 05 እና 06/2015 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት ያካሄደውን አስቸኳይ ስብሰባ ማጠናቀቁን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ነው።
ለሁለት ዓመት በተካሄደው ጦርነት ምክንያት በትግራይ የሚገኙ አባቶች ቤተክርስቲያኗ ጦርነቱን በማውገዝ እና አስፈላጊውን ድጋፍ ለምዕመናኑ አላደረገችም በሚል ከቅዱስ ሲኖዶሱ በመለየት የተናጠል ቤተክህነት ማቋቋማቸውን አሳውቀው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ቤተክርስቲያኗ የተፈጠረውን ቅሬታ ለመፍታት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ስታደርግ መቆየቷን ቅዱስ ሲኖዶሱ ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውሶ፣ ነገር ግን በክልሉ ያሉት አባቶች እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን “የሰላም እና የውይይት በርን ከመጠቀም ይልቅ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን ጥሰዋል” ብሏል።
በዚህም መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት መሥርተናል በማለት “ተገቢነት የሌለው መግለጫ ከመስጠትም አልፎ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት” ለመስጠት መዘጋጀታቸው ተቀባይነት የለውም በማለት የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ድርጊቱን እንዲያስቆም ጠይቋል።
የትግራይ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶች በመጪው እሁድ ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም. አስር ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም ማቀዳቸውን ሐምሌ 05/2015 ዓ.ም. ይፋ አድርገዋል።
ይህንንም ተከትሎ ቅዱስ ሲኖዶስ ባካሄደው ስብሰባ ይህ የትግራይ አባቶች ውሳኔ “ሕገ ቤተ ክርስቲያን ያላከበረ እና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር ተገቢ ያልሆነ፣ የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊነት የሚጥስ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚጎዳ ነው” በማለት ተቃውሞታል።
ጨምሮም ይህ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት “በጦርነት የተጎዳውን፣ ሀብት እና ንብረቱ የወደመበትን፣ ገዳማቱ እና አብያተ ክርስቲያናቱ የተጎዱበትን ሕዝብ የማይጠቅም ተገቢነት የሌለው በመሆኑ እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል” ብሏል።
- የትግራይ ቤተ ክርስቲያን አባቶች በመቀለ በተካሄዱ ሥነ ሥርዓቶች ላይ አለመገኘታቸው ተነገረ10 ሀምሌ 2023
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የትግራይ ሕዝብን ይቅርታ ጠየቀ6 ሀምሌ 2023
- የትግራይ አባቶች ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስለመመለስ ምን ይላሉ?25 ግንቦት 2023
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ አባቶች በኩል ሲሰነዘርበት የነበረውን ወቀሳ ተቀብሎ በጦርነቱ ወቅት እና ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ የሚጠበቅበትን ባለማድረጉ ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ የጠየቀው ባለፈው ሳምንት ነበር።
በተጨማሪም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በክልሉ ከሚገኙ አባቶች ጋር ለመገናኘት እና ለሕዝቡ ድጋፍ ለማድረግ በፓትሪያርኩ የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ መቀለ ቢያቀናም ከክልሉ የቤተክርስቲያን አባቶች ጋር ሳይገናኝ ተመልሷል።
በዚህም በፓትሪያርኩ የተመራው “የሰላም ልዑክ በመቀሌ ሀገረ ስብከት በደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል የተገኘ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን መዘጋቱ” ቅዱስ ሲኖዶሱን በእጅጉ እንዳሳዘነው በመግለጫው ጠቅሷል።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ካስከተለ በኋላ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ስምምነት ላይ የተደረሰው ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪካ ላይ በተፈረመው የሰላም ስምምነት ነበር።
ቅዱስ ሲኖዶሱም የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ችግሩን በውይይት የፈቱት መሆኑ በማስታወስ “የሰላም ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን እስካሁን ሰላም መፈለጓ ያልተቋረጠ ቢሆንም፣ አለመሳካቱ የሚያሳዝን በመሆኑ ለሰላም የሚደረገው ጥረት ዘላቂ መፍትሔ እስከሚገኝ ድረስ የማይቋረጥ መሆኑን” በመግለጫው አመልክቷል።
አክሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት እንዲሁም የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች “የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫውን እንዲያስቆሙል” እና ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ እንዲያግዙ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪ አቅርቧል።