
13 ሀምሌ 2023
የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ኤርትራውያን ስደተኞችን በግዳጅ ወደ አገራቸው መመለስ እንድታቆም ጠየቁ።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ዛሬ ሐምሌ 06/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ በሰኔ ወር መጨረሻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያንን በግዳጅ ማባረሯን ጠቅሶ ድርጊቱን አውግዟል።
ተጨማሪ ስደተኞችን በግዳጅ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉ በአስቸኳይ እንዲቆም እንዲሁም የጥገኝነት ጠያቂዎች እና ስደተኞች እስር እንዲቆምም ጠይቀዋል።
“በዓለም አቀፍ የስደተኞች ሕግ መሠረት በጅምላ ስደተኞችን ማባረር የተከለከለ ነው” ያሉት ባለሙያዎቹ፣ ስደተኞቹ በጅምላ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በመገደዳቸው ከሚገጥማቸው የደኅንነት ስጋት በተጨማሪ ወላጆች እና ልጆች እንዲሁም የቤተሰብ አባላት እንዲነጣጠሉ አደርጓል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቅርቡ ባወጣው ሪፖርትም ሕጻናትን ጨምሮ ወደ 200 የሚጠጉት ኤርትራውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በኃይል ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ ከተደረጉ በኋላ ደኅንነታቸው አሳሳቢ ነው ብሎ ነበር።
ሆኖም የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉት ስደተኞች ወይም ጥገኝነት ጠያቂዎች አይደሉም ብሏል።
የተመድ ባለሙያዎች በርካታ ታማኝ ምንጮችን ጠቅሰው እንዳሉት ግን እንዲመለሱ ከተገደዱት መካከል በስደተኝነት የተመዘገቡ እንዲሁም ያልተመዘገቡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ይገኙበታል።
ኤርትራውያኑ የኢምግሬሽንን ሕግ ጥሰዋል በሚል ያለክስ፣ ያለጠበቃ እና ያለፍርድ ሒደት የዘፈቀደ እስር መቀጠሉን የሚያሳዩ ሪፖርቶች መኖራቸውን የገለጹት ባለሙያዎቹ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን ያሉበት ሁኔታ እጅግ እንዳሳሰባቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያዎች ገልጸዋል።
- ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ የተደረጉት በሙሉ ስደተኞች ወይም ጥገኝነት ጠያቂዎች አይደሉም ተባለ26 ሰኔ 2023
- ጀርመን ውስጥ ሁለት ታዳጊ ሴቶችን በስለት የወጋው ኤርትራዊ ዕድሜ ልክ ተፈረደበት4 ሀምሌ 2023
- በኢትዮጵያ አስገድዶ መሰወር፣ የጭካኔ፣ አዋራጅ እና ኢሰብዓዊ ተግባራት መጨመራቸው ተገለጸ13 ሀምሌ 2023
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ብቻ ያነጣጠሩ ይመስላል በማለትም “አድሏዊ አሰራር” መኖሩን ጠቁመዋል።
በመሆኑም የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንን ጨምሮ ለስደተኞች ጥበቃ የሚያደርጉ ድርጅቶች ጥገኝነት ለመጠየቅ ያለውን ችግር ለመፍታት እና ለስደተኞች አስፈላጊ መረጃዎች እንዲያገኙ ለማስቻል ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር እንዲሰሩ ባለሙያዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለሙያዎቹ ጨምረውም አገልግሎቱ አዲስ የሚገቡ ስደተኞችን መመዝገብ ከመጋቢት 2020 ጀምሮ ማቆሙን ገልጸው፣ ይህም ጥገኝነት እንዳይጠይቁ እና በዓለም አቀፍ ስምምነቱ መሠረት ጥበቃ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል ብለዋል።
የተመድ አጣሪ ኮሚሽን እና በኤርትራ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ልዩ ራፖርተር ቀደም ብለው ባወጡት ሪፖርቶችም ስደተኞችን ማሰቃየት፣ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ፣ አስገድዶ መሰወር፣ ሕገ ወጥ ዝውውር፣ የዘፈቀደ እስርን ጨምሮ በግዳጅ የመመለስ ጉዳይን መሰነዳቸውን ባለሙያዎቹ አስታውሰዋል።
በግዳጅ ወደ ኤርትራ የተመለሱት ስደተኞችም የት እንዳሉ የሚያሳይ ምንም መረጃ አለመኖሩንም ባለሙያዎቹ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የኤርትራን ባለሥልጣናት ስለስደተኞቹ የወደፊት ዕጣ ፋንታ እና የት እንደሚገኙ መረጃ እንዲሰጡ እንዲሁም ዘመዶቻቸውን፣ የሕግ ባለሙያዎችን ወይም የሚፈልጉትን ሰው እንዲያገኙ እንዲያደርጉ ባለሙያዎቹ አሳስበዋል።
ከዚህ ቀደም ከሰሜን አፍሪካ አገራት ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ የተደረጉ ስደተኞች ለእስር ተዳርገው እንደነበር መገለጹ ይታወሳል።
የፖለቲካ እና የፕሬስ ነጻነት የለባትም፣ ሰዎች የፈቀዱትን ሃይማኖት እንዳይከተሉ ይከለከላሉ እንዲሁም አስገዳጅ የብሔራዊ አገልግሎት ታካሂዳለች ተብላ በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ከምትከሰሰው ኤርትራ በመሸሽ በርካቶች አገር ጥለው ይሰደዳሉ።
በዚህም ምክንያት አገራት ኤርትራውያንን ወደ ትውልድ አገራቸው በኃይል ሲመልሱ እምብዛም አይስተዋልም።