ከሕንድ ደቡብ ምሥራቅ ባሕር ዳርቻ ወጣ ብሎ የሚገኘው የህዋ ምርምር ማዕከል
የምስሉ መግለጫ,ቻንድራያን 3 ዛሬ አርብ ከሕንድ ደቡብ ምሥራቅ ባሕር ዳርቻ ወጣ ብሎ ከሚገኘው የህዋ ምርምር ማዕከል ትነሳለች

ከ 4 ሰአት በፊት

ሕንድ እምብዛም ምርምር አልተካሄደበትም ወደተባለው የጨረቃ ደቡብ ዋልታ አቅራቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ መንኮራኩር ልታመጥቅ ነው።

ቻንድራያን 3 የተባለው መንኮራኩር ከስሪሃሪኮታ የህዋ ምርምር ማዕከል ዛሬ አርብ ረፋድ 5፡00 ገደማ ላይ ይነሳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከነሐሴ 17-18 ጨረቃ ላይ እንደሚያርፍ የህዋ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

አርብ ረፋድ ላይ ከመጠቀ በኋላም ጨረቃ ላይ ለመድረስ ከ15 እስከ 20 ቀናት ይወስድበታል ተብሏል።

ይህ የጨረቃ ተልዕኮ ስኬታማ ከሆነ ሕንድ አሜሪካን፣ የቀድሞዋን ሶቭየት ሕብረትን እና ቻይናን በመከተል ጨረቃ ላይ ያረፈች አራተኛዋ አገር ትሆናለች።

በጨረቃ ምርምር ላይ በሦስተኛው የሕንድ ፕሮግራም ቻንድራያን 3 ቀድሞ ከነበሩት የጨረቃ ተልዕኮዎች ስኬታማ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ሕንድ ጨረቃ ላይ የውሃ ፍለጋን ጨምሮ ጥልቅ ምርምር ያደረገችውን እና ጨረቃ በቀን ከባቢ አየር እንዳላት ያገኘችውን የመጀመሪያዋን መንኮራኩር ያመጠቀችው እንደ አውሮፓውያኑ 2008 ሲሆን የአሁኑ ተልዕኮ ከ13 ዓመታት በኋላ የሚካሄድ መሆኑን የቻንድራያን 1 ፕሮጀክት ዳይሬክተር ማይልስዋሚ አናዱራይ ተናግረዋል።

ለሁለተኛ ጊዜ የመጠቀችው ቻንድራያን 2 እንደ አውሮፓውያኑ ሐምሌ 2019 ነበር የተላከችው። ይሁን እንጂ የተላከችበትን ተልዕኮ የፈፀመችው በከፊል ነበር።

መንኮራኩሯ በምህዋር ላይ መዞር የሚችል መንኮራኩር [ ኦርቢተር] ፣ ጨረቃ ወለል ላይ የሚያርፍ [ ላንደር] እና በጨረቃ ላይ የሚገኙ ናሙናዎችን ምስሎች የሚልክ [ሮቨር] አካል ይዛ የነበረ ሲሆን፣ በምህዋር ላይ መዞር የሚችለው መንኮራኩር [ ኦርቢተር] ጨረቃን መክበቡንና እና ዛሬም ድረስ ጨረቃ ላይ ምርምር ማካሄዱን ቀጥሏል።

ሆኖም ጨረቃ ወለል ላይ የሚያርፈው አካል በዝግታ ማረፍ ያልቻለ ሲሆን በመጨረሻው ደቂቃ ባጋጠመ ችግር መከስከሱን አናዱሪያ ተናግረዋል።

የሕንድ የህዋ ምርምር ድርጅት (ኢስሮ) ኃላፊ ስሬድሃራ ፓኒከር ሶማናት እንዳሉት የመጨረሻው ችግር ካጋጠመ በኋላ መረጃዎችን በጥንቃቄ በማጥናት ጉድለቶቹን ለማስተካከል ልምምዶች ተካሂደዋል።

3 ሺህ 900 ኪሎ ግራም የምትመዝነውና 75 ሚሊየን ዶላር የወጣባት ቻንድራያን 3 ቀድሞ ከተላከው መንኮራኩር ጋር ተመሳሳይ ግብ ያላት ሲሆን ይህም ጨረቃ ላይ ማረፍ እንደሚቻል ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ጨረቃ ላይ በርካታ ምርምሮች የተካሄዱ ሲሆን ፕላኔቷ ላይ ዓይኗን ያሳረፈችው ሕንድ ብቻ አይደለችም። በፕላኔቷ ላይ ምርምር ለማድረግ ያለው ዓለም አቀፍ ፍላጎትም እያደገ ነው።

ተመራማሪዎች እንደሚሉትም አሁንም ስለፕላኔቷ ሊታወቅ የሚገባ በርካታ ነገሮች አሉ።