
ከ 2 ሰአት በፊት
ፈረንሳይ ለዘገባ በተሰማራባት ዩክሬን ለተገደለው የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የቪዲዮ ጋዜጠኛ የአገሪቱን ከፍተኛ ሽልማት ሰጠች።
አርማን ሶልዲን የተባለው የ32 ዓመቱ ጋዜጠኛ ግንቦት መጀመሪያ ላይ ነበር ባክሙት አቅራቢያ በሮኬት ጥቃት የተገደለው።
ጋዜጠኛው ከህልፈቱ በኋላ ለክብሩ የአገሪቱ ትልቁ ሽልማት ተበርክቶለታል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤክ ማክሮን ለአገሪቱ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ጋዜጠኛ ሶልዲንን “ደፋር” ሲሉ ገልጸውታል።
እንደ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ (ሲፒጄ) ከሆነ ሩስያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተች በኋላ ሶልዲን የተገደለ 17ኛው ጋዜጠኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
ጋዜጠኛው በፕሬዝዳንታዊ አዋጅ ከፍተኛው ክብር ትናንት ሐሙስ በስሙ ተሰጥቷል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን ጋዜጠኛውን በተመለከተ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል በላኩት ደብዳቤ የሶልዲንን “ጥንካሬ፣ ባሕርይ፣ የሕይወት ጉዞ እና ተነሳሽነት” አሞካሽተዋል።
የኤጀንሲው የአውሮፓ ዳይሬክተር ክርስቲን ቡሃጊአር በበኩላቸው ጋዜጠኛው ለሥራው ያደረ “ከፍተኛ ተነሳሽነት ያለው እና ደፋር ” ነበር ሲሉ ገልጸውታል።
- ዶ/ር ደብረጽዮን ሥልጣን ለማስረከብ ለምን አመነቱ? ጠቅላይ ሚኒስትሩስ ምን አሉ?ከ 5 ሰአት በፊት
- የሱዳን ቀውስ፡ ከዐቢይ እስከ አል ሲሲ፤ መሪዎች በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን እየታገሉ ነውከ 5 ሰአት በፊት
- አሜሪካ ቅጥረኛው ቫግነር አሁን ላይ በዩክሬን ጦርነት ጉልህ ሚና የለውም አለችከ 5 ሰአት በፊት
ሶልዲን ግንቦት 1/2015 ዓ.ም. ከባክሙት በምዕራብ አቅጣጫ ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር በመሆን በዩክሬን ወታደሮች ታጅቦ ሲንቀሳቀስ ነበር በሮኬት ጥቃት ተመትቶ የተገደለው።
ከሶልዲን ጋር የነበሩት የተቀሩት የኤኤፍፒ ጋዜጠኞች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከጥቃቱ ተርፈዋል።
“የቪዲዮ ካሜራውን በእጁ እንደያዘ ነው የሞተው” ብሏል የሥራ ባልደረባቸው ኢማኑኤል ፔውቾት።
ጋዜጠኛው በተገለደበት ወቅት ባክሙት ለወራት የዘለቀ ከፍተኛ ውጊያ ስታስተናግድ ነበር።
የጋዜጠኛው ግድያን ተከትሎ የፈረንሳይ የጸረ-ሽብር ዐቃቤ ሕግ ቢሮ በግድያው የጦር ወንጀል ምርመራ መዝገብ ከፍቷል።
ሶልዲን ትውልዱ ቦስኒያ ቢሆንም ዜግነቱ የፈረንሳይ ነው። ጋዜጠኛው የሩስያን ወረራ ተከትሎ ከመስከረም 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ዩክሬን ተልኮ ሲዘግብ ቆይቷል።
በናፖሌዎን ቦናፓርቴ አስተዳደር ወቅት ከእአአ 1802 ጀምሮ መሰጠት የጀመረው የፈረንሳይ ትልቁ የክብር ሽልማት ‘ዘ ሌግዮን ኦፍ ሆነር’ በውትድርናም ሆነ በሲቪል መስክ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች የሚሰጥ የከበረ ሽልማት ነው።