የቫግነር ወታደሮች

ከ 5 ሰአት በፊት

አሜሪካ ቅጥረኛው ቫግነር ተዋጊ ቡድን በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ውጊያ አሁን ላይ ያለው ተፅዕኖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም አለች።

ይህ የተባለው ቅጥረኛው ቡድን በፕሬዝዳንት ቫላድሚር ፑቲን አስተዳደር ላይ የመራው እና ለ24 ሰዓታት የቆየው አመጽ ሳይሳካ ከቀረ በኋላ ነው።

ሩሲያ እአአ 2014 ላይ የዩክሬን አካል የነበረችውን ክሬሚያን በኃይል ስትይዝ ይህ ቡድን ትልቅ ድጋፍ እንዳደረገ ይታመናል።

ሞስኮ ኪዬቭ ላይ በከፈተችው በዚህ ጦርነትም ቫግነር ከፑቲን ቀለብ እየተሰፈረለት ከሩስያ ጦር ጎን ተሰልፎ ተዋግቷል።

በተለይ በምሥራቅ ዩክሬን የምትገኘውን ባክሙት ከተማን ለመያዝ በተደረገው ደም አፋሳሽ ውጊያ ቫግነር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ይሁን እንጂ ይህ ቡድን ከአመጹ በኋላ በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ያለው ተሳትፎ እየተዳከመ መጥቷል።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ቡድኑ በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ጉልህ ሚና የለውም ብለዋል።

በቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ላይ አመጽ ቀስቅሶ ሩሲያን ለ24 ሰዓታት ትርምስ ውስጥ ከቷት የነበረው ቫግነር አመጹ ከከሰመ በኋላ መሪው ወደ ቤላሩስ እንዲያመሩ ተደርጎ ቡድኑ ደግሞ የከባድ መሳሪያ ትጥቅ መሳሪያ እንዲፈታ ሆኗል።

የቡድኑ ተዋጊዎች ደግሞ ክስ ሳይመሰረትባቸው የሩስያን ጦር መቀላቀል፣ ወደ ቤላሩስ ማቅናት አልያም ትጥቅ ፈትተው ወደ ቀደመ ሕይወታቸው መመለስ እንደሚችሉ በፑቲን አስተዳደር አማራጭ ተሰጥቷቸው ነበር።

ይሁን እንጂ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የቫግነር ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በሞስኮ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝቶ እንደነበር ክሬምሊን አስታውቋል።

ፑቲን ከቫግነር ቡድን መሪ ጋር ከተገናኙ በኋላ የቡድኑ አባላት “አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ” ነግሬያቸዋለሁ ብለዋል።

ፑቲን የግል ወታደራዊ ድርጅት በሩሲያ እንዲኖር ሕግ እንደማይፈቅድ ገልጸው “ቫግነር የሚባል ነገር የለም” ሲሉ በደፈናው ከተናገሩ በኋላ የቡድኑ አባላት በሩሲያ መደበኛ ጦር ውስጥ መካተትን መምረጥ ይችሉ ነበር ብለዋል።

“ሁልግዜም ቢሆን ትክክለኛው አዛዣቸው በነበረው ሰው ሥር መተዳደር ይችሉ ነበር” በማለት እራሳቸውን የቅጥረኛው ቡድን ትክክለኛ መሪ አድርገው አቅርበዋል።

ፑቲን ይህ ካሉ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፊላንድ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የቫግነር መሪ እንዳይመረዝ ለራሱ መስጋት አለበት ሲሉ ተናግረዋል። ባይደን “እኔ እርሱን ብሆን ስለምበላው ነገር እጠነቀቅ ነበር” ብለዋል።

ባይደን ከኖርዲክ አገራት መሪዎች ስብሰባ በኋላ በሰጡት መግለጫ ፑቲን በዩክሬን ላይ የከፈቱትን ጦርነት የሚያሸንፉበት ዕድል የለም ብለዋል።

ባይደን “በጦርነቱ ተሸንፏል [ፑቲን]” ካሉ በኋላ ወደፊት የሆነ ግዜ ላይ ጦርነቱ ለሩሲያ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅምን አያስጠብቅም በሚል ምክንያት ሞስኮ ጦርነቱን ታቆማለች ሲሉ ተንብየዋል።

ባይደን ጨምረውም ዩክሬን አሁን የጀመረችው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ሩሲያ ተገዳ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንድትመጣ ሊያደርግ እንደሚችል “ግምቴ እና ተስፋዬ ነው” ብለዋል።

ባይደን ይህን ይበሉ እንጂ አንድ ወር የደፈነው የዩክሬን መልሶ ማጥቃት እንደታቀደው ብዙ አልገፋም በሚል ዩክሬናውያን እና አጋሮች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

ሌሎች ደግሞ በግዜ ሂደት የሩሲያ የመከላከል አቅም ተዳክሞ ዩክሬን እንደ ክሬሚያ ያሉ አካባቢዎችን እና ቁልፍ ቦታዎችን መልሳ ትይዛለች ይላሉ።