የሱዳን ሠራዊት

ከ 5 ሰአት በፊት

የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በኬንያ መሪነት በሱዳን እየበረታ የመጣውን ግጭት ለመፍታት ደፋ ቀና እያሉ ይመስላሉ።

አንደኛው አማራጭ ቀጠናዊ ወታደራዊ ኃይል ወደ ሱዳን ገብቶ በጦርነት አረንቋ ውስጥ ያሉ ሰላማዊ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ነው።

ነገር ግን ጦርነት ውስጥ ያሉት ሁለቱን ወገኖች ወደ ጠረጴዛ ማምጣት እንዲህ ቀላል አይደለም።

ባለፈው ሚያዚያ ወደ ለየለት ጦርነት የገቡት ሁለቱ ተዋጊዎች ግጭቱን በድል ከመጨረስ ውጭ ሌላ አማራጭ የሚቀበሉ አይምስሉም።

በጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን የሚመራው ወታደራዊው ኃይል አብዛኛውን ምሥራቃዊ እና መካከለኛ የሱዳን ክፍል ይቆጣጠራል።

የቡርሃን ኃይል በመዲናዋ ሱዳን የበላይነቱን ለማስረገጥ እየታገለም ይገኛል።

ተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (ራፒድ ሰፖርት ፎርስ/አርኤስኤፍ) ደግሞ የሚመራው በጄኔራል ሞሐመድ ሃምዳን ደጋሎ ነው። በቅፅል ስማቸው ሄሜድቲ።

የሄምድቲ ጦር ካርቱም ውስጥ ድል ቀንቷቸዋል። ነገር ግን ወታደሮቻቸው ሰላማዊ ሰዎች ገድለዋል፤ ደፍረዋል፤ ሆስፒታሎችን ተቆጣጥረዋል ተብለው ይወቀሳሉ።

የቡርሃን ጦር ካርቱም ውስጥ የአርኤስኤፍ ኃይሎችን ለመምታት የጣለው ቦምብ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል።

የሱዳን ጦር

በሱዳን ምዕራባዊው የዳርፉር ግዛት በጣም አሰቃቂ ግጭት እንዳለ እየተነገረ ነው።

ኤርኤስኤፍ አብዛኛውን የምዕራቡን ክፍል ተቆጣጥሯል። አረብ ሚሊሻ ከተባለው ቡድን ጋር በማበር የማሳሊት ብሔር አባላትን ከታሪካዊ መኖሪያቸው ምዕራብ ዳርፉር እያስወጡ ይገኛሉ።

የብሔረሰቡ መሪ የሆኑትን ሱልጣን መናገሻ አቃጥለዋል። የአካባቢው አገረ ገዢ ኻሚስ አባካር “ዘር ማጥፋት ነው” ሲሉ የአርኤስኤፍ መለዮ የለበሱ ታጣቂዎች አፍነው ወስደው ገድለዋቸዋል።

ከ160 ሺህ በላይ የማሳሊት ተፈናቃዮች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት አገር ቻድ ተሰደዋል።

ኤርኤስኤፍ የዛሊንጌይ ከተማን ተቆጣጥሯል። ከተማዋ የፉር ማሕበረሰብ መኖሪያ ናት።በክልሉ ትላልቅ የሚባሉት አል-ፋሺር እና ኒያላ ከተማዎችን ከበዋታል።

በርካታ የዳርፉር ሰዎች ይህ ረዥም ጊዜ የታሰበበትና በርካታ ማሕበረሰቦችን የሚያስጠልለውን ክልል አረብ የሚመራው ለማድረግ ያለመ ዕቅድ ነው ይላሉ።

በምዕራብ ዳርፉር በአስቸኳይ የሚያስፈልገው ምላሽ ሰላማዊ ዜጎችን መጠበቅ ነው።

የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ሕብረት ሚሽን ወደ ዳርፉር ያቀናው ይህን ሰንቆ ነበር። ነገር ግን ከሁለት ዓመት በፊት እንዲወጣ መደረጉ የተጣደፈ ውሳኔ መሆኑን ያሳያል።

የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች የሰሜን ኮርዶፋን ግዛት መዲና የሆነችውን ኤል-ኦቤይድንም አዳርሰዋል።

በደቡብ ኮርዶፋን የሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጭ ንቅናቄ የተሰኘ አማፂ ቡድን ላለፉት 12 ዓመታት ጥቃት ሲያደርስ ቆይቷል።

ወታደራዊው ኃይል አርኤስኤፍን በመዋጋት ውጥረት ላይ ሳለ ይህ ንቅናቄ ወደ ካዱግሊ እያቀና ይገኛል።

አሁን ቀጠናው በዲፕሎማሲያዊ ርብርብ ተጠምዷል። ነገር ግን ማን ይምራው የሚለው እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ከሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በጄዳህ የተኩስ አቁም ውይይት ሲያመቻቹ ቆይተዋል።

ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተገቡ የቱኩስ አቁም ስምምነቶች ተፈፃሚነታቸው እምብዛም ነው።

አሜሪካ እና ሳዑዲ በሚቀጥሉት ቀናት አዲስ ዕቅድ ይዘው እንደሚመጡ ይፋ አድርገዋል። ሁለቱ አገራት፤ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ወደ ድርድሩ እንድትመጣ ይፈልጋሉ።

ዩኤኢ የአርኤስኤፍ ደጋፊ ተደርጋ ትቆጠራለች። አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ዩኤኢ ለቡድን የመሣሪያ ድጋፍ ታደርጋለች።

የሱዳን ጦርነት ያደረሰው ውድመት

ዩኤኢ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እስካሁን አስተያየት መስጠት አልሻተችም።

ከአንድ ወር በፊት የአፍሪካ ሕብረት ግጭቱን ለማስቆም ያደረገው ጥረት አልተሳካም ያሉ የምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች በቀጠናዊ ክንፍ [ኢጋድ] አማካይነት ድርድር ለማድረግ ወሰኑ።

የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጂቡቲ መሪዎች የተካተቱበት አሸማጋይ ቡድን የሱዳንን ግጭት እንዲያስቆም አደራ ተሰጠው።

የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ቡድኑን እንዲመሩ ሆነ።

ሩቶ፤ ጦርነቱ “ስሜት የለሽ ነው” አሉ። ሁለቱም ቡድኖች “አገሪቱን ለማጥፋትና ሰላማዊ ዜጎችን ለመግደል ተነስተዋል” ሲሉ ወቀሱ። ዳርፉር አካባቢ “የዘር ማጥፋት” ምልክቶች እንደታዩ አወሱ።

ባለፈው ሰኞ በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ የተጀመረው ድርድር ቀጣናዊ ጣልቃ ገብነት እንዲመጣ የመጀመሪያው እርምጃ ሆኖ ተወስዷል።

ሁለተኛው እርምጃ ከአሜሪካና ሳዑዲ ጋር በመተባበር ሁለቱን ጀኔራሎች [ቡርሀን እና ሄምድቲ] ፊት ለፊት ማገናኘት ነው።

ሦስተኛው ደግሞ “አካታች የፖለቲካ ሂደት” ወርሃ ነሐሴ እንዲጀምር ማድረግ ነው።

ነገር ግን ጄኔራል ቡርሃን ይህን ዕቅድ አልተቀበሉትም። ምክንያታቸው ደግሞ ፕሬዝደንት ሩቶ ለአርኤስኤፍ ያደላሉ የሚል ነው። በሰኞው ስብሰባ የአርኤስኤፍ ተወካዮች ተገኝተዋል። ጄኔራል ቡርሃን ግን አሻፈረኝ ብለዋል።

ምንም እንኳን ወታደራዊ ኃይል በ2019 ከአርኤስኤፍ ጋር በመተባበር በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን ቢመጣም ሥልጣኑ የሚገባው ለኔ ነው የሚል አቋም አለው።

የቡርሃን ኃይል፤ በደጋሎ ቤተሰብ የሚመራው አርኤስኤፍ ከወርቅ፣ ከቅጥር ገዳይትና ከሌሎች ንግዶች በሚያገኘው ገቢ የበለጠገ ነው ሲል ያምናል።

የቡርሃን ወታደሮች ሕዝቡንም ሆነ መንግሥታቸውን መጠበቅ አልቻሉም። መዲናዋንም አይቆጣጠሩም። አፍሪካ ውስጥ መንግሥት ተብሎ ለመጠራት ቢያንስ ዋና ከተማን መቆጣጠር ያሻል።

የሱዳን ጦርነት ለደቡብ ሱዳንም አደጋ እየሆነ ነው። ሄሜድቲ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት እንድታቋርጥ ይሻሉ።

የግብፁ ፕሬዝደንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ከኳታር ጋር በመተባበር ባዘጋጁት መድረክ ላይ የኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂና የኢትዮጵያው አቻቸው አቢይ አሕመድ ተገኝተዋል።

ግብፅ በግላጭ የምትደግፈው የጄኔራል ቡርሃንን መንግሥት ነው።

በዚህ መሐል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተረስቷል። ጄኔራል ቡርሃን የተባበሩት መንግሥታት ተወካይ የሆኑት ግለሰብ አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል።