የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል
የምስሉ መግለጫ,የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል

ከ 5 ሰአት በፊት

አምስት አስርት ዓመታት ለሚሆን ጊዜ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ጉልህ ሚና የነበረው ህወሓት ለሁለት ዓመታት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ውስጥ ቆይቷል። ጦርነቱ በአጠቃላይ በአገሪቱ ላይ በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል ላይ ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመትን አስከትሏል።

በጦርነቱ ወቅት በትግራይ በኩል ዋነኛ ተዋናይ የነበረው ህወሓት በሽብር ቡድንነት ተፈርጆ ሕገወጥ ሆኖ ቢቆይም፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በተደረሰው የሰላም ስምምነት አማካይነት ይህ ፍረጃው ተነስቶለታል። ቢሆንም ግን አሁንም የተገፈፈውን ሕጋዊ ዕውቅና አላገኘም።

ለበርካታ አስርት ዓመታት ትግራይ ክልልን በብቸኝነት ሲያስተዳደር የቆየው ህወሓት፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት በፌደራል መንግሥቱ ሥር ሌሎችንም በማካተት ጊዜያዊ አስዳደር ሲያቋቁም፣ የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ቦታቸውን ለቀዋል።

የትግራይ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳደር እና የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ስለፓርቲያቸው እና በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ዋና ዋና ነጥቦችን እነሆ፡

ቢቢሲ፡ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ ጊዜያዊ መንግሥት ለመመሥረት 5 ወራት ወስዷል።ይህ የሆነው ደግሞ በህወሓት አባላት መካከል ስምምነት ባለመኖሩ ነው ተብሏል። ይህ ከነበረ ችግሩ ለምን እርስዎ ሥልጣንዎን አልለቀቁም?

ዶ/ር ደብረጽዮን፡ የእኔ ጉዳይ ለብቻው በራሱ ተነጥሎ የሚታይ ጉዳይ አይደለም።ማነው [በእኔ መነሳት ጉዳይ] የሚወስነው የሚለው ነው ዋናው ነጥብ። የሚወስነው ፓርቲው ነው። አመራር ነው የሚወስነው።

የእኔ የግለሰብ ፍላጎት ከሆነ ያ ሌላ ጉዳይ ነው። የድርጅታችን አሰራርም አይደለም። በእኛ አሰራር ሥልጣን የግል ፍላጎት ስላልሆነ። ማን ይቀጥል ማን አይቀጥል የሚለውን የሚወስነው ህወሓት እንጂ በግለሰብ ፍቃድ የሚመለስ ጥያቄ አይደለም።

ቢቢሲ፡ እርስዎ የሥልጣን ፍላጎት ስላልዎ እኔ ካልሆንኩ ብለው ከማስቸገርዎም በላይ፣ ድምጽ ተሰጥቶኛል ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድ መሄድዎ ነው የሚነገረው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም “እርስዎ አይሆኑም፤ ሥልጣን ለወጣቶች ይስጡ” ብለው እንደመለስዎ ነው የተሰማው።

ዶ/ር ደብረጽዮን፡ ተናገርኩ እኮ። ውሳኔው የእኔ ሳይሆን የፓርቲው ነው። እኔ ካልሆንኩ የሚባል ነገር የለም። ምርጫ እኮ ተካሄደ። 38 ይቀጥል አለ፤ 3 ተቃውሞ ነበር።በድምጽ ብልጫ ነው የሚጸድቀው። በአሰራሩ መሠረት ነው የሄድነው። ዐቢይ ይህን ነበር ያልተቀበለው።

በኋላ ላይ ሌሎች ምሁራን፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ቢመሩ የሚል ነገር መጣ። ይህን ማዕከላዊ ኮሚቴ ነው ያጸደቀው አልን። ከዚያ በኋላ ነው ህወሓት እና ፌዴራል መንግሥት ውይይት ያደረገው። ተመካክረን ብንሰራ ይሻላል ብለን ወጣት ቢሆኑ ተቃውሞ ስላልነበረን በሐሳቡ ተስማማን። ነገሩን በቀና ልብ ወስደን ምርጫ አድርገን በመጨረሻ ጌታቸው ተመረጠ።

ቢቢሲ፡ ከዚያ ሁሉ እልቂት በኋላ ህወሓት ለምንድነው ከሥልጣን ያልወረደው? ለዚህ ሁሉ ለደረሰው እልቂት ማነው ኃላፊነት የሚወስደው?

ዶ/ር ደብረጽዮን፡ አሁንም እራሳችን በመከላከል ላይ ነው ያለነው። የትግራይ ሕዝብ አሁንም በወራሪዎች ሥር ነው የሚገኘው። ምን ጎደለ?፣ ምንድነው ያጠፋነው? ብለን እንገመግማለን።ይህ የራሱ ጊዜ አለው።

ወደ ሥልጣን የሚያወጣንም፣ ከሥልጣን የሚያወርደንም ሕዝብ ነው። ማንም ሰው መጥቶ ‘ውረድ’ ስላለ ወይ ደግሞ ማንም ሰው መጥቶ ‘በቃ ተው’ ስላለ ሥልጣን አይለቀቅም።

ህወሓትን ሕዝብ እኮ ነው የመረጠው። በትግራይ ሕዝብ ትግራይ ውስጥ ነው የተመረጠው፣ ስለዚህ ሕዝቡ ነው የሚያወርደው።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ሌላ ነው። ለሰላም ሲባል የተከፈለ ዋጋ ነው። ከዚህ ሌላ ግን ለምን ከሥልጣን አልወረዳችሁም የሚባለው ወዴት ነው ከሥልጣን የምንወርደው? ኃላፊነት የሰጠን እኮ ሕዝቡ ነው።

ቢቢሲ፡ ሕዝብ መርጦናል ካላችሁ ሕዝቡ ድምጽ የሰጣችሁ ከአደጋ እንድትጠብቁት ነበር ። ሆኖም ብዙ ሕዝብ ህወሓት ከዚህ አደጋ ሊጠብቀን አልቻለም ይላል፤ ይህ እርስዎ ከሚሉት ነገር ጋር አይጋጭም?

ዶ/ር ደብረጽዮን፡ አይጋጭም። ደጋግሜ እንደገለጽኩት ሁሉንም ነገር ገና ለግምገማ አላቀረብንም። ምን ጎደለ? ማን አጠፋ? የሚለው ወደፊት በግምገማ የሚታይ ነው።

አላዳናችሁንም የሚባለው ነገር ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ ግንባሩን ነው የሰጠው። ሳይሰስት ነው የመከተው። ከቀድሞ አመራሮች ጀምሮ መስዋዕት ሆነዋል። የሚችለውን እና የሚገባውን ሁሉ አድርጓል። እንዲያም ሆኖ ግን አጉድሏል ከተባለ በግምገማ የሚታይ ነው የሚሆነው።

ቢቢሲ፡ ህወሓት ሕጋዊነቱን ለመመለስ ከምርጫ ቦርድ ጋር ስምምነት ላይ አልደረሰም። ይህ ጉዳይ እንዴት ነው የሚፈታው?

ዶ/ር ደብረጽዮን፡ በአዲስ መልክ ተመዝገቡ ነው የሚሉት። በአዲስ መልክ ልንመዘገብ አንችልም። 50 ዓመት የደፈነ ፓርቲ አዲስ ሕጻን ልጅ ሆኖ እንደ አዲስ ፓርቲ ሊመዘገብ አይችልም። ይህ ተቀባይነት የለውም።

በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት እኛን ፌዴራል መንግሥት እውቅና ሰጥቶናል። እውቅና ሰጥቶም ነው ሊፈራረም የቻለው። አሸባሪ ነው የፈረመው ቢሉም፣ አሸባሪም ብለው እውቅና ሰጥተውን ተፈራርመናል። አሸባሪነቱን በኋላ እናየዋለን፣ መፈረም ነው የሚበጀን ብለን ተፈራርመናል።

ይህ ቀድሞውንም በስምምነት ያለቀ ጉዳይ ነው። በኋላ የተወካዮች ምክር ቤት ከአሸባሪነት ስሙን ፍቆታል። የህወሓት አመራሮች እስር ቤት ያሉትም ክሳቸው ተነስቷል። ምርጫ ቦርድ ፍርድ ቤት አቤት እንድንል ነው የሚፈልገው። የፓርቲያችን ማዕከላዊ ኮሚቴ የወሰነው ደግሞ ፍርድ ቤት አንሄድም መፍትሔው ፖለቲካዊ ነው ብሎ ወስኗል። እንደ አዲስ የመመዝገብ ነገረ የማይታሰብ ነው።

ቢቢሲ፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህወሓት ሃብት ተወርሶ ዕዳው እንዲከፈል እና የተረፈ ካለ ደግሞ ለሥነ ዜጋ ትምህርት እንዲውል መወሰኑ ይታወሳል። ይህ የታገደው ገንዘብ መጠኑ ስንት ነው?

ዶ/ር ደብረጽዮን፡ በባንክ የነበረው ገንዘብ 70 ሚሊዮን ይሆናል።

ቢቢሲ፡ 70 ሚሊዮን ብር ነው ወይስ ዶላር?

ዶ/ር ደብረጽዮን፡ እንዴ! በኢትዮጵያ ባንክ እኮ ነው ያለው። ውጭ አገር አይደለም እኮ። ብር ነው እንጂ።

ቢቢሲ፡ በእርስዎ የመሪነት ዘመን ከግማሽ ሚልዮን በላይ የትግራይ ተወላጆች ሕይወታቸው እንዳለፈ ይነገራል፤ የትግራይ ሕዝብ እርስዎን በምን የሚያስታውስዎት ይመስለዎታል? እርስዎስ ምን ዓይነት መሪ ነኝ ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር ደብረጽዮን፡ ስለዚህ ጉዳይ የምገልጽበት ጊዜ ነው ብዬ አላስብም።

ግራጫ መሥመር
የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል
የምስሉ መግለጫ,የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል

የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከዚህ በተጨማሪ በሌሎች ጉዳዮችም ላይ ከቢቢሲ ትግርኛ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር።

የፕሪቶሪያው ስምምነት

ዶ/ር ደብረጽዮን ስምምነቱ አገሪቱን ከከባድ ጦርነት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ምዕራፍ ያሸጋገራት መሆኑን በመግለጽ፣ አንዳንድ ተግባራዊ የተደረጉ እና አሁንም በሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

“ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኗል ማለት አይቻልም፤ ነገር ግን ሰላሙን ለማጠናከር በፌዴራል መንግሥት እና በትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት የተወሰዱ ጥሩ እርምጃዎች አሉ” ብለዋል።

ነገር ግን በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ ከፈቱ በኋላ የፌደራል መንግሥት የኤርትራ ጦርን እና የአማራ ኃይልን ከትግራይ የማስወጣት ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም፣ እስካሁን ተፈጻሚ ባለመሆኑ የተፈናቀሉ ሰዎች ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የተፈናቀለው ሕዝብ

በደም አፋሳሹ ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ላለፉት ሦስት ዓመታት በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ በአስከፊ ሁኔታ እየኖሩ መሆኑን የሚገልጹት ዶ/ር ደብረጽዮን፣ “ወራሪዎች” ብለው በገለጿቸው የአማራ እና የኤርትራ ኃይሎች ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸውና ወደ ንብረታቸው ሊመለሱ አልቻሉም ብለዋል።

“መሬት ላይ የተለወጡ ነገሮች አሉ፤ አዲሶቹ ሰፋሪዎች ሊወጡ ይገባል” በማለት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ እንዲችሉ የትግራይ አስተዳደር ፖሊስ እና የፀጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው ገብተው በወረራ ሥር ከቆየው ሕዝብ እና የአገር ሽማግሌዎች ጋር መመካከር እና መግባባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

“[ከጦርነቱ በኋላ] የገቡ ሰፋሪዎች ሳይለቁ [እነሱን] መደረብ አይቻልም። ሰፋሪዎች መጀመሪያ አካባቢውን መልቀቅ አለባቸው። አስፈላጊው ሎጅስቲክስ ተዘጋጅቶለት ሕዝቡም ተደራጅቶ መግባት አለበት” በማለት ያሉትን የአፈጻጸም ዝርዝር ጠቁመዋል።

የምዕራብ እና የደቡብ ትግራይ ዕጣ ፈንታ?

ዶ/ር ደብረጽዮን የምዕራብ እና የተወሰነ የደቡብ ትግራይ አካባቢን ተቆጣጥረው የሚገኙት የአማራ ኃይሎች እና የክልሉ አስተዳደር አዳዲስ ሰፈራዎች እያቋቋሙ እና መታወቂያ እየሰጡ እንዳሉ መረጃ እንዳላቸው በመግለጽ፣ ተቃውሟቸውን ለፌደራል መንግሥት እንደገለጹና “ጊዜ ስጡን እንፈታዋለን” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይገልጻሉ።

በአቶ ጌታቸው ረዳ የተመራ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ልኡካን ቡድን በቅርቡ ባሕር ዳርን በጎበኘበት ወቅት መሬት ላይ መፈጸም ስላለበት ነገር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየቱንም ተናግረዋል። ግንኙነቱ በፌዴራል መንግሥት ሸምጋይነት እንደሚካሄድ እና የፕሪቶሪያን ስምምነት እንደሚያጠናክርም አስረድተዋል።

የኤርትራ ጦር ትግራይ ውስጥ ስለመኖሩ

ዶ/ር ደብረጽዮን እንደገለጹት የኤርትራ ጦር በምሥራቃዊ እና በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ ይገኛል።

“የኤርትራ ጦር በአልጀርስ ስምምነት ተወስኖልኛል በሚላቸው አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን በትግራይ መሬት ውስጥ በእገላ፣ በዓዲ አርባዕተ እና በሰሜን ምዕራብ ድንበሮች አለ” ብለዋል።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በተካሄደው የድንበር ጦርነት ማዕከል የነበረችው ባድመ በአሁኑ ጊዜ በኤርትራ ጦር ይዞታ ሥር የምትገኝ ሲሆን፣ ዶ/ር ደብረጽዮን የኤርትራ ሠራዊት ከባድመም እንዲወጣ ይፈልጉ እንደሆነ እና የአልጀርስ ስምምነትን ጉዳይ ተጠይቀው ነበር።

“የድንበር ጉዳይ የኤርትራ እና የትግራይ ጉዳይ አይደለም። የድንበር ጉዳይ የፌደራል መንግሥቱ ጉዳይ ነው። ነገር ግን የትግራይ መሬት ላይ ስላሉ ከትግራይ መውጣት አለባቸው። በምንም መልኩ የድንበር ጥያቄ በጉልበት የሚፈታበት ሁኔታ መኖር የለበትም፤ የፌደራል መንግሥትም በዚህ ነው የሚያምነው።

ስለዚህ በድንበር ጉዳይ የሚደራደረው የፌደራል መንግሥት ነው፤ አሁን ድንበር የማጥራት ጉዳይም አይደለም።በኃይል የተወረረ አካባቢ መልቀቅ አለበት! የአልጀርስ፣ የባድመ የሚባል ነገር አሁን ሊመጣ አይችልም። በጉልበት ሳይሆን በሕግ እና በሥርዓት ተግባብተን ነው መፈጸም ያለበት። አቋማችን በኃይል የተያዘ ቦታ መኖር የለበትም ነው” ካሉ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ ወታደሮች ለቀው የሚወጡበት የጊዜ ገደብ እንዳላስቀመጠ ተናግረዋል።

ከኤርትራ ፕሬዝዳንት ስለመታረቅ

ወታደራዊውን መንግሥት ለመጣል አጋር የነበሩት ህወሓት እና የኤርትራ ነጻ አውጪ በድንበር ይገባኛል ምክንያት ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ከገቡ በኋላ በጠላትነት ፍጥጫ ውስጥ ቆይተዋል።

በሁለት ዓመቱ ጦርነት ወቅትም የኤርትራ ሠራዊት ከፌደራሉ መንግሥት ኃይሎች ጎን ተሰልፎ መዋጋቱ ይታወቃል። ቢሆንም ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ሰላም ሲያወርድ የኤርትራ መንግሥት ተሳታፊ አልነበረም። ህወሓት ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር ለመታረቅ ይፈልግ ይሆን?

“የትግራይ መሪዎች ወደ ጦርነቱ ከመግባታችን በፊትም ጉዳዮቻችንን በሰላማዊ፣ በሕጋዊ እና በሥርዓት መፍታት አለብን ብለን ከሁሉም አካላት ጋር እየሰራን ነበር” በማለት እንደ ሕዝብ እና ፓርቲ ከኤርትራ ጋር ሁሉም ነገር በሰላም እንዲፈታ ፍላጎት እንደነበራቸው ዶ/ር ደብረጽዮን አስረድተዋል።

ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ከኤርትራ ጋር ለመታረቅ የተወሰደ ምንም ዓይነት እርምጃ ባይኖርም፣ አገራዊ ግንኙነቱ በፌዴራል መንግሥት በኩል እንደሚተገበር በመጠቆም “የኤርትራ ጦር አሁንም ድረስ በትግራይ ግፍ እየፈጸመ ስለሆነ የሰላም ዝግጁነቱ እንዲጠናከር ሠራዊቱ ከትግራይ መውጣት አለበት” ብለዋል።

የተሰረቀ ሰብአዊ እርዳታ

ባለፈው ግንቦት ወር የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ለተረጂዎች የላኩት የእርዳታ አቅርቦት ተሰርቆ ላልተገባ አላማ መዋሉ እና ለገበያ መቅረቡን ገልጸው ነበር።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ማጭበርበር ያጋጥም እንደነበር እና ይህንንም ለማስተካከል በየጊዜው እርምጃዎች ይወሰዱ እንደነበር ዶ/ር ደብረጽዮን ተናግረዋል።

በእርሳቸው የአመራር ወቅት የተፈፀመውን የእርዳታ ምግብ ስርቆት በተመለከተም በእርዳታው ሥርጭት ወቅት ማጭበርበር እና የሕዝብ ቅሬታዎች እንደነበሩ፣ አስፈላጊው ማጣራት እየተደረገ ተገቢ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ እንደነበርም ተናግረዋል።

በዚህ ጦርነት የተከፈለው የሰው ሕይወት

በትግራይ በኩል በጦርነቱ በአጠቃላይ ስንት ሰው እንደሞተ የተጠየቁት ዶ/ር ደብረጽዮን፣ “በጊዜው ይገለጻል” በማለት ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ የትግራይ ቤተሰቦች ልጆቻቸው ያሉበትን ሁኔታ ለማሳወቅ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።