ፀሐይ ላይ 'Stop' የሚል ምልክት የያዘ ግለሰብ

14 ሀምሌ 2023, 12:48 EAT

የአሜሪካ ደቡብ ምዕራብ ክፍል በከፍተኛ ሙቀት እየተመታ ሲሆን በአሪዞና ግዛት ከፍተኛ የተባለ የሙቀት መጠን እንደሚመዘገብም ተተንብዩዋል።

የአገሪቱ ብሔራዊ የአየር ንብረት አገልግሎት እንዳስታወቀው ከ115 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች የከፍተኛ ሙቀት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

አሪዞና ውስጥ የምትገኘው ፎኒክስ ከተማ ለ14 ተከታታይ ቀናት 43 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሆነ የሙቀት መጠን ያስመዘገበች ሲሆን በዚህ ሳምንት ከዚህም በላይ የሙቀት መጠን እንደምታስመዘገግብ ተተንብይዋል።

ሌሎች በርካታ ከተሞችም ከ38 ሴንቲግሬድ በላይ የሙቀት መጠን ያስመዘግባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የብሔራዊ የአየር ንብረት አገልግሎቱ ከአሪዞና በተጨማሪ ኔቫዳ፣ ኦክላሆማ፣ ቴክሳስ እና ካሊፎርኒያ የመሳሰሉ ግዛቶችንም አስጠንቅቋል።

በደቡባዊው የአሜሪካ ክፍልም እስከ 46 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርስ የሙቀት መጠን እንደሚከሰት ይጠበቃል።

ሙያተኞች እንደሚሉት በአንዳንድ አካባቢዎች የአየር ሁኔታ መዛባቱ የሚቀጥል ሲሆን ሌሊት ላይ ለተወሰነ ጊዜ መስተካከል ሊኖር ይችላል።

የፀሐይ ግለቱ በሚጨምርበት ሰዓታት ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ፣ ሕጻናትን እና እንደ ድመት እና ውሻ የመሳሰሉ የቤት እንስሳትን መኪና ውስጥ ቆልፈው እንዳይወጡ እንዲሁም በቂ ፈሳሽ እንዲወስዱ ባለሥልጣናት አስጠንቅቀዋል።

እንደ ማዕከላዊ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ተቋም መረጃ ከሆነ በአሜሪካ ከሙቀት ጋር በተያያዘ በየዓመቱ 700 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ።

በኔቫዳ ግዛት ውስጥ የምትገኘው ላስ ቬጋስ ከተማ በመጪው እሑድ 47 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሆነ የሙቀት መጠን ታስተናግዳለች ተብሎ የተተነበየ ሲሆን፣ይህም ከ1942 እና በ2021 ላይ ከተከሰተው በበለጠ የምንጊዜም ከፍተኛው የሙቀት መጠን ሆኖ ይመዘገባል።

በቴክሳስ ኤል ፓሶ የሙቀት መጠኑ በዲግሪ ፋራናይት ለተከታታይ 27 ቀናት ከ100 በላይ ሆኖ ቆይቷል። ይህም ከተማዋ በ1994 ለተከታታይ 23 ቀናት ካስመዘገበችው ከፍተኛ ሙቀት በእጅጉ ያየለ ሲሆን እንደሚቀጥልም ተነግሯል።

በፎኒክስ በጎዳና ላይ ሕይወታቸውን ለሚገፉ ሰዎች ማቀዝቀዣ ያላቸው መጠለያዎች ተዘጋጅተውላቸዋል።በጎ ፈቃደኛ ሠራተኞችም እድሜያቸው ለገፉ ሰዎችና ረዳት ለሌላቸው ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ከተማዋ በሺዎች የሚቆጠር የቀዘቀዘ የታሸገ ውሃ ለነዋሪዎቿ እያደለች ነው።

የአሜሪካው የሙቀት መጠን በጨመረበት ወቅት በተመሳሳይ በአውሮፓ እንደ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ፣ ክሮሽያ እና ቱርክ ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ በሆነ የሙቀት መጠን ተመትተዋል።

በጣሊያን ጎብኝዎችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች በሙቀት ምክንያት ራሳቸውን እየሳቱ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን የአንድ ግለሰብ ሕይወት አልፏል።

ባለፈው ሳምንት የምንጊዜም ከፍተኛው የተባለው የዓለም አማካይ የሙቀት መጠን 17.23 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሆኖ ተመዝግቧል።

ሳይንቲስቶች እንደሚሉት የሙቀት መጠን መጨመሩ የተከሰተው በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እና በየሦስት ወይም ሰባት ዓመቱ በሚከሰተው ኤልኒኖ ምክንያት ነው።

ዓለም ከኢንዱስትሪው ዘመን ጀምሮ የሙቀት መጠኗ በ1.1 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ጨምሯል። መንግሥታት የበካይ ጋዝ ልቀትን ካልቀነሱ የሙቀት መጠኑ ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል።