
ከ 5 ሰአት በፊት
በአሜሪካ ያለው ሙቀት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ሊበረታ እንደሚችል የተተነበየ ሲሆን በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ለነዋሪዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
አርብ ዕለት የወጡ መረጃዎች እንዳመለክቱት በፍሎሪዳ ፣ በቴክሳስ፣ በካሊፎርኒያ እና በዋሽንግተን ሰሜን ምዕራብ ክፍል ቢያንስ 113 ሚሊዮን ሰዎች በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ ይገኛሉ።
በቴክሳስ ነዋሪዎች ለማቀዝቀዣ የሚጠቀሙት የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ከዚህ ቀደም ግዛቷ ከፍተኛ ብላ ከመዘገበችው በልጧል።
ወደ 27 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በመጭዎቹ ቀናት ከ43 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ የሆነ ሙቀት እንደሚያስተናግዱም ተተንብዩዋል።
የብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት እንዳለው ከፍተኛው ሙቀት የተፈጠረው ከከፍተኛ ቦታዎች በሚመጣ የሞቃታማ የአየር ግፊት ምክንያት ነው።
አገልግሎቱ ጨምሮም አካባቢው እስካሁን ካየው በዓይነቱ ለየት ያለና ከፍተኛ ሙቀት ነው ያጋጠመው ብሏል።
እንደ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ከሆነ በአሜሪካ ከሙቀት ጋር በተያያዘ በየዓመቱ ወደ 700 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወት እንደሚያልፍ ይገመታል።
በአካበቢው ቅዳሜ በተለየ መልኩ ሞቃታማ ሆኖ የሚውል ሲሆን ሙቀቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በቀን ወቅት 46 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሊደርስ እንደሚችልም ተተንብዩዋል።
ከፍተኛው ሙቀትም እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል ይጠበቃል።
- በአሜሪካ ደቡብ ምዕራብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በከፍተኛ ሙቀት እየተገረፉ ነው14 ሀምሌ 2023
- በከፍተኛ ሙቀት እየተገረፈች ባለችው አውሮፓ ኢትዮጵያውያን እንዴት እያሳለፉ ነው?21 ሀምሌ 2022
- የአየር ንብረት ለውጥ ምንድን ነው? ዓለማችንን ሊያጠፋት ይችላል?19 ጥቅምት 2021
ፊኒክስ የምንጊዜም ረጅሙ የሙቀት ቀናቷን ለማለፍ አፋፍ ላይ ያለች ሲሆን በሚቀጥሉት አምስት ቀናት 43 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ወይም ከዚያ በላይ ሙቀት እንደምታይ ተተንብዩዋል።
የምንጊዜም ረጅሙ የሙቀት ወቅቷ 18 ቀናት ሲሆን፣ ከተማዋ እስካሁን 15 ቀናትን በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ አሳልፋለች።
ላስቬጋስም በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት የምንጊዜም ከፍተኛ የተባለውን 47 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት እንደምታስተናግድ ይጠበቃል።
በምሥራቅ ካሊፎርኒያ የሚገኘውና በምድራችን ሞቃታማ ከሆኑ ቦታዎች አንዱ የሆነው ዴዝ ቫሊ ከዚህ ቀደም የምንጊዜም ከፍተኛ ብሎ ያስመዘገበውን 54 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሙቀት መጠን ሊያልፍ ይችላል ተብሏል።
በላስ ቬጋስ የአየር ሁኔታ አገልግሎት ነዋሪዎች ሙቀቱን መቋቋም እችላለሁ በማለት እንዳይዘናጉ አስጠንቅቋል።
የደቡብ ምዕራብ አሜሪካ አካባቢዎች ባለፉት ሳምንት ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበባቸው ሲሆን በቴክሳስ፣ ኤልሳፖ ለ27 ተከታታይ ቀናት ሙቀት መጠኑ ከ100 ፋራናይት አልፏል።
በከፍተኛ ሙቀቱ ሳቢያ በርካታ ፓርኮች፣ ሙዝየሞች፣ መካነ እንስሳት እና የንግድ ተቋማት መዝጋታቸውን ያስታወቁ ሲሆን አንዳንዶች የሥራ ሰዓታቸውን አሳጥረዋል።
ሆስፒታሎችም በሙቀቱ ሳቢያ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎችን እየተቀበሉ ነው።
የአሜሪካው የሙቀት መጠን በጨመረበት ወቅት በተመሳሳይ በአውሮፓ እንደ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ፣ ክሮሽያ እና ቱርክ ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የሆነ ሙቀት አስተናግደዋል።
በጣሊያን ጎብኝዎችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች በሙቀት ምክንያት ራሳቸውን እየሳቱ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን የአንድ ግለሰብ ሕይወት አልፏል።
ባለፈው ሳምንት የምንጊዜም ከፍተኛው የተባለው የዓለም አማካይ የሙቀት መጠን 17.23 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሆኖ ተመዝግቧል።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት የሙቀት መጠን መጨመሩ የተከሰተው በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እና በየሦስት ወይም ሰባት ዓመቱ በሚከሰተው ኤልኒኖ ምክንያት ነው።
ዓለም ከኢንዱስትሪው ዘመን ጀምሮ የሙቀት መጠኗ በ1.1 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ጨምሯል። መንግሥታት የበካይ ጋዝ ልቀትን ካልቀነሱ የሙቀት መጠኑ ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል።