
ከ 5 ሰአት በፊት
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኒዩ በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን የምግብ ዋጋ መናርን ለማረጋጋትና እጥረትን ለመቅረፍ የአስቸኳይ ጊዜ አወጁ።
በቅርቡ ከተነሳው የነዳጅ ድጎማ የተቆጠበውን ገንዘብ ለአርሶ አደሮች ማዳበሪያና ዘር ማቅረብም መንግሥት የምግብ ዋጋ ገበያውን ለማረጋጋት ከወጠናቸው አንዱ መሆኑም ተጠቅሷል።
በርካታ አርሶ አደሮች በወሮበሎች እየታገቱ ካሳ እየተጠየቀባቸው በመሆኑም መሬታቸውን ጥለው ለመሄድ ተገደዋል።
ይህንንም ለማስቀረት መንግሥት ለአርሶ አደሮች ጥበቃ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
በተጨማሪም በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ያሉ ሰዎችም በየወሩ 10 ዶላር ለስድስት ወራት ያህል እንዲረዱ ይደረጋል።
“ለሁሉም ናይጄሪያውያን የማረጋግጠው ነገር ቢኖር መንግሥት በሚያደርገው ድጋፍ ማንንም ወደኋላ እንደማንተው ነው” ሲሉም በግንቦት ወር ሥልጣን የተረከቡት ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኒዩ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዘንድሮው ዓመት ጥር ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት በዚህ ዓመት 25 ሚሊዮን የሚሆኑ ናይጄሪያውያን የተመጣጠነ ምግብ እጦት ከፍተኛ ስጋት ላይ ይወድቃሉ በሚልም ተንብይዎ ነበር። ይህም ማለት ሚሊዮኖች በየቀኑ በቂ የተመጣጠነ ምግብ መግዛት አይችሉም።
የምግብ ዋስትና ስጋት በአፍሪካ ሕዝብ ቁጥሯ በቁንጮነት ሥፍራ ላይ የተቀመጠችውን ናይጄሪያን ሲያሳስባት የቆየ ጉዳይ ነው። ከምግብ ዋስትና እጦት በተጨማሪም ለዓመታት ያህል በርካታ ግጭቶችን አስተናግዳለች።
በባለፈው ዓመት ብቻ ከ350 በላይ አርሶ አደሮች ታግተዋል ወይም ተገድለዋል ሲል የናይጄሪያ የደህንነት ክትትል ድረ ገጽ ዘግቧል።
ከእነዚህ ጥቃቶች መካከል አብዛኛዎቹ የተፈጸሙት በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ነው።
ነገር ግን መንግሥት አዳዲስ የጸጥታ እርምጃዎችን የሚዘረጋ ከሆነ አርሶ አደሮች “ጥቃትን ሳይፈሩ ወደ እርሻ መሬታቸው ሊመለሱ ይችላሉ” ሲሉም የመንግሥት አማካሪው ዴሌ አላኬ ተናግረዋል።
- ቅጥረኛው ቫግነር ከሩሲያ ጦር ጋር እንዲቀላቀል የቀረበለትን ሃሳብ ውድቅ ማድረጉን ፑቲን አስታወቁከ 7 ሰአት በፊት
- “የአፍሪካ የብስክሌት ንጉሥ” የተባለው ኤርትራዊው ቢኒያም ግርማይከ 7 ሰአት በፊት
- የሆሊውድ የፊልም ባለሙያዎች አድማ ለወራት ሊቆይ እንደሚችል ተነገረከ 6 ሰአት በፊት
መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የተንሰራፋውን የተደራጁ የወንጀለኞች ቡድኖችን እንዴት ሊታገል እንዳሰበ ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።
ከምግብ እና ውሃ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በሙሉ የአገሪቱ የደህንነት ኃላፊዎችን ያቀፈው እና በፕሬዚዳንቱ የሚመራው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ኃላፊነት ይሆናል።
ፕሬዚዳንት ቲኒቡ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የመጀመሪያ የፖሊሲ እርምጃቸው አገሪቷ ለአስርት ዓመታት ስትተገብር የነበረውን የነዳጅ ድጎማ ማስቀረት ነው።
የነዳጅ ድጎማ ከመነሳቱም ጋር ተያይዞ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ነዳጅ 200 በመቶ እጥፍ እንዲጨምር ያደረገው ሲሆን ፕሬዚዳንቱ ግን ገንዘቡን የበለጠ ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም ረገድ ትክክለኛነቱን ተከራክረዋል።
ነዳጅ መጨመሩም በአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል።
ከጥቂት ቀናት በፊትም የናይጄሪያ ጋጋሪዎች እና አቅራቢዎች ማህበር የዳቦ ዋጋ 15 በመቶ እንደሚጨምር አስጠንቅቋል።
አንዳንድ ቤተሰቦች ዳቦ ለመግዛት እንኳን አቅም እንዳጠራቸው ለቢቢሲ ፒጂን ተናግረዋል።