
14 ሀምሌ 2023
የአውስትራሊያ የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም አስተዳዳሪ የነበሩት አባ ሰረቀብርሃን ወልደ ሳሙኤል ወደ ትግራይ መቀለ ለመጓዝ መከልከላቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥም ሦስት ቀናትን ለማሳለፍ መገደዳቸውንም ገልጸዋል።
አባ ሰረቀ ብርሃን በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በወንበር ላይ ተቀምጠው ተኝተው የሚያሳዩ ምስሎችም በስፋት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዛወሩ ይገኛሉ።
እሳቸውም ሁለት ምሽቶችን ወንበር ላይ ተኝተው ማሳለፋቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አባ ሰረቀ ብርሃን ወደ ትግራይ መሄድ እንደማይችሉ እና ከአየር ማረፊያው ወጥተው በአዲስ አበባ ከተማ እንዲቆዩ ወይም ወደ አውስትራሊያ ተመልሰው እንዲሄዱ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት በትግራይ የተከሰተውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በተመለከተ በተለያዩ ሚዲያዎች በመናገር የሚታወቁት አባ ሰረቀ ብርሃን፣ የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ተከትሎም ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት መወሰናቸውን ተናግረዋል።
“እኔም የሰላም መስኮቱ ከተከፈተ በሰላሙ ዙሪያም ሆነ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን በማየት ድርሻዬን መወጣት አለብኝ። ያለውን ሁኔታ ተረድቼ መምጣት አለብኝ በሚል ነበር የመጣሁት” ብለዋል።
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ከ14 ዓመታት በላይ በከፍተኛ ኃላፊነት ያገለገሉት አባ ሰረቀ ብርሃን በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የደረሱት ረቡዕ ሐምሌ 05/2015 ዓ.ም. ሊነገጋ ሲል 11 ሰዓት ላይ ነበር።
ከአውስትራሊያም ሲነሱ አዲስ አበባ ሳያርፉ መቀለ ለመጓዝ ዕቅድም ስለነበራቸው ዕቃቸውም ቀጥታ ነበር ወደዚያው የተጫነው። ክልከላውም የመጣው በአገር ውስጥ በረራ እንደሆነም ይናገራሉ።
በአገር ውስጥ በረራ ወደ መቀለ ወደሚሄደው አውሮፕላን ለመሳፈር አውቶብስ ውስጥ ለመግባት ቲኬቱን ለበረራ ሠራተኛዋ በሚያሳይዋት ወቅት “እርሰዎ ለሴኩሪቲ [ደኅንነት] ይፈለጋሉ” ብላ እንደመለሰቻቸው ተናግረዋል።
ከእርሳቸው ጋር አብረው የመጡ ሌላ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ወደ መቀለ ለመሄድ ባይከለከሉም ከእርሳቸው ጋር ወደኋላ እንደቀሩም ገልጸዋል።
ተመልሰውም ለሰዓታት ቢቀመጡ እና ቢጠይቁም የደኅህንነት ሰዎች ይመጣሉ ተብለው ቢጠብቁም፣ “የፖሊስ መለዮ የለበሰ ግለሰብ መጥቶ” እሳቸውን እና ከእርሳቸው ጋር የመጡትን አባት ወደ ዓለም አቀፍ በረራ ክፍል ይዟቸው እንደሄደ ተናግረዋል።
“ዕቃችሁን ይዛችሁ ከአየር ማረፊያው ውጡ ወደ ከተማ ሂዱ የተባልነው” የሚሉት አባ ሰረቀ ብርሃን “እንዴት አሁን እኮ ሴኩሪቲ [ደኅንነት] ነው እንዳንሄድ ያስቀረን። የሴኩሪቲው ጉዳይ ምንድን ነው? በምን ምክንያት ነው ከጉዟችን እንድንመለስ የተደረግነው? ምርመራ ያደርጋሉ የተባሉት ኃላፊዎችስ የታሉ?” የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡለትም፣ ምላሽ ሳያገኙ ከአየር ማረፊያው ወጥተውም እንዲሄዱ እንደተነጋረቸው ገልጸዋል።
“እኔ ወደ አዲስ አበባ አልመጣሁም፣ የመጣሁት ወደ መቀለ ለመጓዝ ነው። በረራዬም ቀጥታ ነው። ስለዚህ መውጣት አልችልም። አልወጣም ስል። እንግዲያውስ ፖሊስ ጠርተን እናስወጣችኋለን” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል።
- የትግራይ አባቶች ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስለመመለስ ምን ይላሉ?25 ግንቦት 2023
- ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ ይካሄዳል የተባለውን የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንዲያስቆም መንግሥትን ጠየቀ13 ሀምሌ 2023
- ዶ/ር ደብረጽዮን ሥልጣን ለማስረከብ ለምን አመነቱ? ጠቅላይ ሚኒስትሩስ ምን አሉ?14 ሀምሌ 2023
“ፖሊስ ይምጣ ሌላም ይምጣ ታስረን ገርፋችሁ የምትወስዱን ካልሆነ በቀር ይህ የምታደርጉት ህጋዊ አይደለም ብዬ ተከራከርኩ” ብለዋል።
እርሳቸው ጋር የነበሩት አባት ከአየር ማረፊያው ቢወጡም፣ እርሳቸው በዚያው በአየር ማረፊያው ምሽቶቹን እንዳሳለፉ እና ጠያቂም ሆነ፣ ምግብ እና ውሃ ያቀረበላቸው እንደሌለ ገልጸዋል።
በኋላም ሁለት አማራጮች እንዳላቸው የተነገራቸው ሲሆን፣ ይህም ከአየር ማረፊያው ወጥተው በአዲስ አበባ እንዲቆዩ ወይንም ወደ አውስትራሊያ እንዲመለሱ ካለበለዚያ ወደ ትግራይ ግን መሄድ እንደማልችልም ተነግሮኛል ብለዋል።
“በጣም የገረመኝ በዓለም ላይ ተሰርቶ ተደርጎ የማይታወቅ ነገር ነው። ወደ ትግራይ የማልገባበት ምክንያት ይነገረኝ። የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ነው አትግባብ ያለኝ? በትግራይ ተቃውሞ ተነስቶብኝ ነው? ወይስ ምንድን ነው ብዬ ጠየቅኩኝ” ይላሉ።
ለዚህም መልስ እንዳላገኙ እና ከሁለቱ አማራጮች አንዱን መውሰድ እንዳለባቸው እንደተነገራቸው ያስረዳሉ።
ለረጅም ዓመታት በውጭ አገር በኖሩበትም ወቅት የሌላ አገር ዜግነት አለመውሰዳቸውን እና አሁንም ዜግነታቸውም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ የሚናገሩት አባ ሰረቀ ብርሃን “የአሁኑ አማራጭ ሰብዓዊ መብቴ እንደተከበረ ዜግነቴንም በማክበር” ወደ ትግራይ እንዲልኳቸው ቢጠይቁም ምላሽ እንደተነፈጋቸው ተናግረዋል።
ከአየር ማረፊያ “ፖሊሶች በስተቀር” ቀርበው የሚያናግሩ የሥራ ኃላፊዎችም ሆነ ባለሥልጣናት እንዳላገኙም አስረድተዋል።
ዛሬ ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም ምግብ ይዘውላቸው የመጡ ሰዎችም አንዳሉ ነው ለቢቢሲ የተናገሩት።
በትግራይ የተቀሰቀውን ጦርነት ተከትሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት መካከል የነበረው ግንኙነት መሻከሩ ይታወሳል።
የትግራይ አባቶችም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ጋር ያለውን ግንኙነት በማቋረጥም የመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተ ክህነትን የመሠረተ ሲሆን፣ ከሰሞኑም ሐምሌ 09/ 2015 ዓ.ም በአክሱም የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ይህንን ሹመት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ሕገወጥ ነው በማለት መንግሥት ጣልቃ እንዲገባም ጠይቋል።
የአባ ሰረቀ ብርሃን ወደ ትግራይ አይገቡም ተብሎ መከልከል በመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተ ክህነት እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ ከተፈጠረው ውጥረት ጋር የተያያዘ ይሆን? ወደ ትግራይ እንዳይሄዱ የተከለከሉበት ምክንያት ምንድን ነው ብለው ያስባሉ? በሚልም ቢቢሲ አባ ሰረቀ ብርሃንን ጠይቀዋቸዋል።
የትግራይ መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተ ክህነት በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ሕዝብ እየደረሰበት ያለው ግፍና ስቃይ ሰሚ ባጣበት ወቅት በብዙ ልፋት የሕዝቡን እንባ ለማበስ እንደተቋቀመ ገልጸው፣ እንደሌላው የትግራይ ሕዝብ እንደሚደግፉትም ተናግረዋል።
እናም እሳቸው ወደ ትግራይ ከገቡ “በትግራይ ጦርነት ስለተደረገው ከዚያም በፊት ስለነበሩ ጉዳዮች ፍትህ እና ሰላምን በማንሳት ድምጼን ከፍ አድርጌ ነበር የምናገረው። ወደ ትግራይ ከገባ መንበረ ሰላማ ይጠነክራል፤ እዚያ ያሉ ጳጳሶች ድምጽም በሚገባ ይጎላል የሚሉ” እንዳሉም ያስረዳሉ።
ሌላኛው መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት አንደኛው እሳቸው ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ ነገሮች እንዳሉ ጠቅሰው “እናም እሱ ከገባ ይሄንን የሚያስቡ ጳጳሳት የመኖር አደጋ ላይ እንወድቃለን በሚል ይሄንን ማጨናገፍ አለብን በሚል እንደሆነም” እንደሚገምቱ ተናግረዋል።
ሌላኛው የሚገምቱት በትግራይ የተፈጸመውን ግፍና እልቂት ሊያጋልጡ ይችላሉ ከሚል የሚመነጭ እንደሆነም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በጦርነቱ ወቅት ድምጽ ሆኜ ነበር። አባ ሰረቀ ብርሃን ወደዚያ ከሄደ ሚዲያም አለኝ እና አስተማሪም ነኝና ብዙ ተከታዮችም አሉኝና ያንን በትግራይ የተፈጸመውን ግፍ በግልጽ ያሳየዋል ያየዋል። እውነቱን ያወጣዋል የሚል ስጋት ያላቸው አካላት እንዳሉ ይሰማኛል” የሚሉት አባ ሰረቀ ብርሃን “ይሄ ደግሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት የሚመነጭ ብቻ ሳይሆን ከሌላም ይመስለኛል” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“ሰላም ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ሰላም ያለ ፍትህ ምንም የለውም ብዬ ነው የማምነው። ፍትህ ለሰው ልጅ መስፈን አለበት የሚል አቋም አለኝ” ይላሉ።
በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ወደ አራተኛ ቀን እየተሻገሩ ያሉት አባ ሰረቀ ብርሃን ወደ ትግራይ አይሄዱም ተብለው ከተከለከሉ በአየር ማረፊያው ቆይታቸውን ይቀጥላሉ? ወይስ ሌላ አማራጭ ያያሉ ተብለው ተጠይቀው ነበር።
“እኔ የመጣሁት ወደ ትግራይ ለመሄድ ነው። ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነኝ። ከዚህ ወጥተህ እኔ ወዳልፈቀድኩት ወይም እነሱ ወዳዘጋጁልኝ በአዲስ አበባ ቆይ የሚለውን ነገር አልቀበልም። አዲስ አበባ ያገለገልኩት ሕዝብ ነው፤ ይህንን የምለው ከጥላቻ አይደለም። ነገር ግን ፍትህ የማይፈቅድ ስለሆነ ወደ አዲስ አበባ ገፍተው ሊያስወጡኝ አይችሉም” ያሉት አባ ሰረቀ ብርሃን አክለውም ወደ አውስትራሊያም ተመለሱ መባላቸው ተቀባይነት እንደሌለው ያስረዳሉ።
“እኔ አውስትራሊያዊ አይደለሁም፤ እኔ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜግነቴ ወደዚያ የምሄድበት ነገር የለም። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥትም፣ የትግራይ መንግሥትም ወደ ትግራይ የማትገባበት ይህ ነው የሚል አሳማኝ ምክንያት ካላቸው ይንገሩኝ። ዜግነቴንም ነጥቀው ካባረሩኝ መጽሐፉም እንደሚለው በኃይል መግባት ስለማልችል አገሬን ትቼ መሰደድ እችላለሁ። እስከ መጨረሻው የሚመጣውን ነገር ለመቀበል ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።
ስለጉዳዩ ቢቢሲ መረጃ ለማግኘት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የሚሠሩ ሁለት የደኅንነት አመራሮች እና አንድ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ባልደረባን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ቢሞክርም ስልካቸው ባለመነሳቱ ምላሽ አላገኘንም።
ምላሻቸውን እንዳገኘን የምናካትት ይሆናል።