
ከ 5 ሰአት በፊት
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸውን የከተማዋ አስተዳደር ገለጸ።
ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ምንውየለት ጭንቅሎ የተገደሉት አርብ ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም. እንደሆነ ተገልጿል።
የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው የደብረ ብርሃን ከተማ ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ባወጣው የሐዘን መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የፖሊስ አዛዡ በሥራ ላይ ሳሉ ነው ባልታወቁ ሰዎች በጥይት የተመቱት።
ኮማንደር ምንውየለት ጭንቅሎ በታጣቂዎቹ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ከቆሰሉ በኋላ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ቢሆንም ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
የከተማው ኮሚዩኒኬሽን “ጠንካራ መሪዎችን መርጦ በመግደል፣ የሚመጣ ለውጥ፣ የሚረጋገጥ ፍትህም የለም” በማለት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታዋቂ እና ጠንካራ የፖለቲካም እና የፀጥታ ዘርፍ አመራሮች ላይ ግድያ እንደሚፈጸም አመልክቷል።
- በአማራ ክልል በሁለት ቀናት በተለያዩ ቦታዎች ሦስት የአካባቢ ባለሥልጣናት ተገደሉ5 ሀምሌ 2023
- ሳሙኤል ሞላልኝ፡ በነዋሪዎች እየተወደሱ ያሉት የደሴ ከተማ ከንቲባ4 ሀምሌ 2023
- ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ስለወልቃይት የወደፊት ዕጣ እና ስለሚቀርብባቸው ክስ ምን ይላሉ?19 ሰኔ 2023
የፌደራል መንግሥቱ እና የክልሉ መስተዳደር በአማራ ክልል ውስጥ ሕግ የማስከበር ተግባር እያካነወኑ መሆናቸውን በገለጹባቸው ባለፉት ጥቂት ወራት፣ በክልሉ የተለያዩ ስፍራዎች በከፍተኛ የፖለቲካ እና የፀጥታ ኃላፊዎች ላይ ግድያዎች ተፈጽመዋል።
ከእነዚህም መካከል ከሁለት ወራት በፊት የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ የሺጥላ ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በታጣቂዎች መገደላቸው ይታወሳል።
በተፈጸመው ጥቃት ጨምሮ ቢያንስ አምስት ሰዎች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች የተገደሉት ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ 250 ኪሎ ሜትር በስተሰሜን በሚገኝ ስፍራ ሚያዚያ 19/2023 ዓ.ም. ነበር።
እንዲሁም ከሳምንት በፊት በተከታታይ ቀናት በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ እና በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ ውስጥ በሚገኙ የአካባቢ የፀጥታ ኃላፊዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት የፖሊስ አዛዦች እና አንድ የፀጥታ ኃላፊ ተገድለዋል።
በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች በተፈጸሙት ጥቃቶች የሸዋ ሮቢት ከተማ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት የአቶ አብዱ ሁሴን እና የደጀን ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ዘውዱ ታደለ እና የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ወርቁ ሽመልስ መገደላቸው አይዘነጋም።
እንዲህ ያለው በአማራ ክልል በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ባልታወቁ ሰዎች የሚፈጸሙ የአካባቢ ባለሥልጣናት ግድያን በተመለከተ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደም ሆነ ተጠያቂ የሆነ ወገን የለም።