
ከ 7 ሰአት በፊት
የሚያስነሳው እንፋሎቱ በሚለበልበው የስዊዝ ፀሐይ፤ ቢኒያም ግርማይ የብስክሌቱን መሪ በክንዱ ተደግፎ፤ ቀኝ እግሩን ደግሞ መርገጫው ላይ ጭኖ ቃለ-ምልልስ ይሰጣል።
እርግጥ ነው እሱ ብቻ አይደለም 15 ሺህ ፓውንድ የሚያወጣውን ብስክሌት እያሽከረከረ የፍፃሜዋን መስመር የተሻገረው።
ነገር ግን ኤርትራዊው ቢኒያም 534 ብስክሌተኞች የተመዘገቡበት የዓለም ፕሮፌሽናል ብስክሌተኞች ረድፍ ላይ ስማቸው ከሰፈረ ስድስት ጥቁር አፍሪካውያን አንዱ ነው።
ቢኒያምን ለየት የሚያደርገው ተሰጥኦው ነው፤ አፍሪካ አሉኝ ከምትላቸው ብስክሌተኞች አንዱ መሆኑ ነው።
ባለፈው ዓመት በሁለት ውድድሮች የመጀመሪያው አፍሪካዊ በመሆን ታሪክ ሠርቷል።
የመጀመሪያው ውድድር ጌንት-ቬቬልጌም ነው። የአንድ ቀን ውድድር። ቢኒያም እነ ክሪስቶፍ ላፓርትን አስከትሎ በመግባት በውድደሩ ታሪክ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ አሸናፊ ሆነ።
ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ በብስክሌት ውድድር ሁለተኛው ትልቁ ወደተሰኘው ዢሮ ዲኢታሊያ አቅንቶ ‘ስቴጅ’ በመርታት ባንዲራውን ከፍ አድርጎ አውለበለበ።
ብዙዎቹ የብስክሌት ውድድሮች ለቀናት የሚካሄዱ ናቸው። በብስክሌት ውድድር ስቴጅ ማለት ቀኑን የሚያመላክት ነው። ለምሳሌ ውድድሩ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን ያሸነፈ ብስክሌተኛ የ‘ስቴጅ 2’ አሸናፊ ይባላል።
የ23 ዓመቱ የአፍሪካ የብስክሌት ውድድር ኩራት ቢኒያም፣ በቱር ደ ስዊስ ለመሳተፍ መጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ተሰልፏል።
ይህ በዓለም ትልቁ የብስክሌት ውድድር ለሆነው ቱር ደ ፍራንስ ማማሟቂያ ይሆነዋል።
- ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን የተመረጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊው እግር ኳስ ተጫዋች9 ሀምሌ 2023
- የማንቸስተር ሲቲ በድል መንበሻበሽ የተሞገሰውን ያህል ለምን ጥያቄ ጫረ?3 ሀምሌ 2023
- “ሊዲያ የሚለው ስም ራሱ ይዳኛል”፡ ‘ፊሽካ የሰቀለችው’ ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ29 ሰኔ 2023
ቢኒያም በቱር ደ ፍራንስ ውድድር ስቴጅ ካሸነፈ ለመላው አፍሪካ ታሪክ ፃፈ ማለት ነው።
ብስክሌታቸውን እየገፉ ሲበሩ ሲመለከቷቸው ደስታን ከሚያጎናፅፉ ስፖርተኞች መካከል ነው – ቢኒ።
ቢኒ ‘ስታይሉ’ የእንግሊዞች የብስክሌት ውድድር ኩራት እንደሆነው ልክ እንደ ማርክ ካቬንዲሽ ነው ይሉታል።
ልክ እንደ ካቬንዲሽ ቢኒ ደልዳላ እና ዳገት ያልበዛባቸው ውድድሮች ላይ አስፈሪ ከሚባሉት ይመደባል።
ኤርትራዊው የብስክሌት ኮከብ በቱር ደ ስዊስ የመጀመሪያውን ስቴጅ [በመጀመሪያው ቀን] ካሸነፈ በኋላ “አፍሪካዊ ብስክሌተኛ ቱ ደ ፍራንስን ቢያሸንፍ ለእኛ ትልቅ ድል ነው. . . ምን እንደምል አላውቅም” ይላል።
የቱር ደ ስዊስ የመጀመሪያውን ስቴጅ አሸንፎ ሲገባ የአገሩ ልጆች በኤርትራ ባንዲራ ከበው እና አቅፈው ተቀበሉት።
ብዙዎች የቢኒያም ድል በነጭ ብስክሌተኞች የተከበበውን ስፖርት ለሁሉም ክፍት ያደርገዋል የሚል እምነት አላቸው።
የአህጉረ አፍሪካ የብስክሌት ታሪክም ሊቀየር ይችላል። አፍሪካ ተወዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆን አሸናፊዎችን ማውጣት ትችላለች።
ቢኒያም ለቤልጂየሙ አንተርማርሼ ሰከርስ ዋንቲ ቡድን ነው የሚወዳድረው። ቡድኑ በፈረንሳይ እና በቤልጂየም ኩባንያዎች የሚደገፍ ነው።
ከቢኒያም በተጨማሪ አራቱ ፕሮፌሽናል ብስክሌተኞች የአገሩ ልጆች ናቸው። ሌላኛው ደግሞ ለጄይኮ አሉላ ቡድን የሚወዳደረው ኢትዮጵያዊው ወላይ ሐጎስ በርሄ ነው።
ነገር ግን በዘንድሮው ቱር ደ ፍራንስ 2023 ብቸኛው ጥቁር አፍሪካዊ ተሳታፊ ነው።
ከምርጦች መካከል ምርጦች ተመልምለው በሚሳተፉበት ቱር ደ ፍራንስ ብዙዎች እነ ታዴ ፖጋቻር እና ዮናስ ቪንጌጋርድን ለመመልከት ቢዘጋጁም ቢኒያም ግን ታሪክ ሊቀይር ተነስቷል።
ቢኒያም በዘንድሮው የቱር ደ ፍራንስ ወድድር ምን ያህል አቅም እንዳለው እያሳየ ነው።
በሰባተኛው ቀን ውድድር (ስቴጅ 7) ፊሊፕሰን እና ካቬንዲሽን ተከትሎ ሦስተኛ በመውጣት ተስፋ ያለው ተወዳዳሪ መሆኑን አሳይቷል።

ቢኒ አሁንም የሚኖረው ኤርትራ ውስጥ ነው። በመዲናዋ አሥመራ። ብስክሌት መንዳት በማይሰለቹ እግሮች የተሞላችው ከተማ።
“ብስክሌት መንዳት ደማችን ውስጥ ነው” ይላል ቢኒ። “ለመጀመሪያ ጊዜ ብስክሌት ስነዳ ትዝ አይለኝም። ምክንያቱም በጣም ትንሽ ልጅ ነበርኩ።”
ግርማይ ታዳጊ ሳለ አሥመራ ውስጥ ኢንተርኔት ካፌ ሊጠቀም ሲመላለስ ብስክሌት ያዘወትር ነበር። ቀጥሎ በከተማዋ በሚካሄዱ ውድድሮች ይሳተፍ ያዘ። ይሄኔ ነው በመልማዮች ዐይን ውስጥ የገባው።
“ግርማይ ወደ ዓለም አቀፉ የብስክሌት ማዕከል ሲመጣ የ18 ዓመት ወጣት ነበር” ይላል ስዊዝ የሚገኘው ማዕከል የባለተሰጥዖዎች መልማይ ፈረንሳዊው ዦን-ዣክ ሄንሪ።
ሄንሪ እንደሚለው ቢኒያም የመጀመሪያዎቹ ወራት እጅግ ከብደውት ነበር። ባሕሉ፣ አየሩ፣ በታክቲክ የተሞላው ሥልጠና. . .
“በጣም ብዙ ነገር አልፎ ነው እዚህ የደረሰው። አሁን ግን የዓለም ቱርን ሊያሸንፍ ይችላል። ሁሌም ፈገግታ አይለየውም። ለሁሉም ነገር ፈገግታ ነው መልሱ። ሕይወትን በፈገግታ ነው የሚያሸንፋት።”
ወጣቷ ሰላም አመሃም በትግራይ የነበረውን ጦርነት ሸሽታ ወደ ስዊትዘርላንድ በመምጣት ማዕከሉን ተቀላቅላለች።
በጦርነቱ የልጅነት ጓደኞቿን አጥታለች። ነገር ግን ብስክሌት ላይ ወጥታ ማሽከርከር ስትጀምር ሰላም እንደሚሰማት ትገልጻለች።
ለአፍሪካውያን የብስክሌት ሕይወት ቀለል አይደለም። ከደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ የመጡ ነጭ ተወዳዳሪ ቢሆኑ እንኳ።
አራት ጊዜ ቱር ደ ፍራንስን ያሸነፈው ክሪስ ፍሩም ተወልዶ ያደገው በኬንያ መዲና ናይሮቢ ነው። ልጅ እያለ ተደብቆ እየወጣ መኪና እየተከተለ ብስክሌት ሲጋልብ ያስታውሳል።
አፍሪካ ያልተነካ የብስክሌት ተሰጥዖ ያለባት አህጉር ናት። ይህን ለማወቅ የቢኒያምን አድናቂዎች መጠየቅ ነው።
“እሱ እኮ የአፍሪካ ንጉሥ ነው” ይላሉ አንዱ። “ኤርትራ በጦርነት ነበር የምትታወቀው። አሁን ግን ቢኒ አለልን” ይላሉ።