
ከ 2 ሰአት በፊት
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ከወሰዱ 150 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት 40.65 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከነዚህም ውስጥ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለፈተና ካስቀመጧቸው ተማሪዎች ውስጥ 17.2 በመቶው ብቻ የማለፊያውን 50 በመቶና ከዚያ በላይ የሆነውን ውጤት ማስመዝገባቸው ተገልጿል።
ከሰኔ 30 ጀምሮ ለስድስት ቀናት ሲሰጥ የቆየውን የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና መጠናቀቁን አስመልክቶ የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ሳሙኤል ክፍሌ ዛሬ ሐምሌ 8/ 2015 ዓ.ም መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው ይህ የተገለጸው።
የመውጫ ፈተናውን ለመውሰድ ከ48 የመንግሥት ተቋማት 84 ሺህ 627 ያህል ተማሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከነዚህም 62.37 በመቶው አልፈዋል። በግል ተቋማት በኩል ከ171 የግል ተቋማት 194 ሺህ 239 ተማሪዎች ተመዝግበው ነበር ተብሏል።
ፈተናውን የወሰዱት የተማሪዎች ቁጥር ከመንግሥት ተቋማት 77 ሺህ 981 እንዲሁም ከግል ተቋማት በድምሩ 150 ሺህ 184 ተማሪዎች መሆናቸውንም ነው የትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ ያመለከተው።
በአጠቃላይም 50 በመቶና ከዚያም በላይ አምጥተው ያለፉ ተማሪዎች ቁጥር 61 ሺህ 54 ተማሪዎች ወይም 40.65 መሆኑም ተጠቁሟል።
ተማሪዎችም ውጤታቸውን ከነገ እሁድ ማታ ጀምሮ ትምህርት ሚኒስቴሩ ባስቀመጠው ድረ ገጽ ላይ ማየት እንደሚችሉ ዶክተር ሳሙኤል አስረድተዋል።
- ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ራስ ገዝነት መቀየር ለምን አስፈለገ?17 ሰኔ 2023
- ቻይናዊው ሚሊየነር ለ27ኛ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወደቀ27 ሰኔ 2023
- ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እየተዘጋጁ የሚገኙት የ61 ዓመት አዛውንት16 ሰኔ 2022
በመውጫ ፈተናው የማለፊያ ውጤት ያላስመዘገቡ ቅድመ ምሩቃን ተማሪዎች ፈተናውን በየስድስት ወሩ ደጋግመው መውሰድ እንደሚችሉም ሚኒስቴር ዲኤታው ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ፈተናውን ደጋግመው መውሰድ እንደሚቻል ቢገለጽም ለምን ያህል ጊዜ መውሰድ እንደሚቻል አልተጠቀሰም።
የመውጫ ፈተናው ከመሰጠቱ አስቀድሞ ተመራቂ ተማሪዎች ከፈተና ሥርዓቱ ጋር እንዲለማመዱ የሙከራ እና የሞዴል ፈተና ወስደው ነበር ተብሏል።
በፈተናው ወቅት በውስን ተቋማት ለተወሰኑ ሰዓታት ካጋጠመ የኃይል መቆራረጥ እን የኢንተርኔት መቆራረጥ ውጪ በፈተናው ሂደት ይህ ነው የሚባል ችግር አልገጠመም ብለዋል ዶ/ር ሳሙኤል በዛሬው መግለጫቸው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከጀመራቸው ማሻሻያዎች አንዱ እንደሆነም ተገልጿል።