
16 ሀምሌ 2023, 07:51 EAT
ሴቶች እንዲመክኑ የሚያደርግ ክኒን አለ? ምናልባት በሴቶች የውስጥ ሱሪ ላይ የሚደረግ ቅባት መሰል ፈሳሽ (ጄል)?
አንድ ዶክተር ሴቶች በቀዶ ሕክማና (ሲሴክሽን) በሚወልዱበት ጊዜ በምስጢራዊ ሁኔታ እያመከኑ ስለመሆኑ ሰምተዋል?
ይህ የተሰማው ሲሪላንካ ውስጥ ነው።
ፀረ ሙስሊም የሆኑ አክራሪ ቡድሂስቶች ያዛመቱት ሐሰተኛ ወሬ ነው።
በአገሪቱ ውስጥ አናሳ ቁጥር ያላቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች ቁጥራቸውን የማሳደግ ህልም አላቸው ተባለ።
ይህንንም ለማድረግ ከፍተኛ የሕዝብ ድርሻ ያላቸውን የቡድሂስት እምነት ተከታይ ሴቶችን በምስጢራዊ ሁኔታ እያመከኑ ነው የሚል የሴራ ጽንሰ ሐሳብ ተጠነሰሰ።
ለዚህ ሐሰተኛ ውንጀላም አንድ ዶክተር ዒላማ ተደረጉ።
ዶክተሩ በሰሜን ምዕራብ ኩሩኔጋላ ከተማ ነዋሪ ናቸው።
“እኔ ሙስሊም ነኝ። 4 ሺህ የቡድሂስት ሴቶችን በድብቅ በማምከን ተከስሼ ነበር” ሲሉ የቀዶ ጥገና ህክምና ባለሙያ የሆኑት መሐመድ ሻፊ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ዶክተር ሻፊ ቡድሂስት ሴቶችን በቀዶ ሕክምና በሚያወልዱበት ወቅት የማህጸን ቱቦዎቻቸውን (ፋሎፒያን ቲዩብ) በመሳሪያ ይጨምቁታል ተባሉ። ይህም ሴቶቹ ተጨማሪ ልጆች እንዳይወልዱ አምክነዋቸዋል በሚል ተወነጀሉ።
በውንጀላ ብቻ አልቀረም በአውሮፓውያኑ 2019 በቁጥጥር ስር ዋሉ።
በሽብር ወንጀልም ተከሰሱ።
“ከወንጀለኞች ጋር ታሰርኩ። ለምንድን ነው በእኔ ላይ ይህንን የሚያደርጉት ብዬም አስብ ነበር? ለባለቤቴ እና ለልጆቼ ስል በሕይወት መቆየት እንዳለብኝ ተሰማኝ” ሲሉ ዶክተር ሻፊ የነበሩበትን ሁኔታ ተናግረዋል።
የሦስት ልጆች አባት የሆኑት ዶክተሩ 60 ቀናትን በእስር ቤት አሳልፈዋል።
ከሁለት ወራት እስር በኋላም ፍርድ ቤቱ የዋስ መብታቸው እንዲጠበቅ ብይን ሰጠ።
ነገር ግን እየተካሄዱ ባሉ ምርመራዎች ምክንያት ከሥራቸው የግዳጅ ፍቃድ ይውጡ ተባሉ።
በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ከአራት ዓመታት በኋላም በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ላይ ወደ ሥራቸው ተመልሰዋል።
የሲሪላንካ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ሐኪሙ የቀረበባቸውን ክስ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ባለማግኘቱ ነው ዶክተሩ ወደ ሥራቸው የተመለሱት።
- የተባበሩት መንግሥታት ኤድስን በቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ውስጥ ከዓለም ማጥፋት ይቻላል አለ13 ሀምሌ 2023
- በአሜሪካ ባለፉት 20 ዓመታት የእናቶች ሞት በእጥፍ መጨመሩን አንድ ጥናት ገለጠ4 ሀምሌ 2023
- ምልክት የማያሳየው እና ሰባ በመቶ ሴቶች የሚገጥማቸው የማሕፀን ግድግዳ እጢ22 ሰኔ 2023
የትንሳዔ ዕለቱ የቦምብ ጥቃቶች
የሲሪላንካ የሕዝብ ቁጥር 22 ሚሊዮን ያህል ነው።
ከዚህ ሕዝብ ውስጥ አብዛኛው ወይም 70 በመቶ ያህሉ የቡድሂዝም እምነት ተከታይ፣ 10 በመቶ ሙስሊሞች፣ ወደ 12 በመቶ የሚሆኑት ሂንዱዎች እንዲሁም 7 በመቶ የክርስትና እምነት ተከታዮች ናቸው።
ዶክተር ሻፊ ሴቶችን እንዲመክኑ በማድረግ ከመወንጀላቸው በፊት፣ ሃይማኖት ሳይለዩ ሁሉንም ሲያክሙ ቆይተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2019 የትንሳዔ በዓል ላይ ተከታታይ የቦምብ ጥቃቶች ተፈጽመው ነበር።
ጥቃቶቹ በአብያተ ክርስቲያናት እና ቱሪስቶች በሚያዘወትሯቸው ሆቴሎች ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ።
በዚህም ከ250 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል። ይህ ጥቃትም የዶ/ር ሻፊን ሕይወት ለዘለዓለም ቀየረው።
ለዚህም ጥቃት ተጠያቂው ከኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ጋር ግንኙነት ያላቸው አክራሪ ጽንፈኛ ቡድኖች ነበሩ።
በአውሮፓውያኑ 2009 ከታሚል ታይገር ተገንጣዮች ጋር ሲካሄድ የቆየው የእርስ በርስ ጦርነት ካበቃ በኋላ ያጋጠሙት የቦምብ ጥቃቶቹ እጅግ እሰከፊ ነበሩ ተብሏል።
የቦምብ ጥቃቱ በመላው ስሪላንካ ፀረ ሙስሊም ስሜት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆነ።
በአጸፋውም መስጂዶች፣ የሙስሊሞች መኖሪያ ቤቶች እና ሱቆች ተቃጠሉ። አንድ ሙስሊምም በደቡ ጥቃት ተደብድቦ ተገደለ።

ሐሰተኛ ክስ
የትንሳዔ ዕለት ከተፈጸሙት የቦምብ ጥቃቶች ከአንድ ወር በኋላም ‘ዲቫይና’ የተሰኘው ጋዜጣ የፊት ገጹ ላይ አንድ አወዛጋቢ ጽሑፍ አወጣ።
አንድ ዶክተር 4 ሺህ ቡድሂስት እናቶችን ማምከኑን፣ ዝርዝሩ ከማስረጃ ጋር እንዳለ እና ዶክተሩንም በቁጥጥር ስር ለማዋል ሰፊ ምርመራዎች ተካሂደዋል የሚል ነበር። በዚህም ጽሑፍ ላይ የታውሂድ ጃማዝ ዶክተር በሚል ነው የህክምና ባለሙያው የተጠሩት።
‘ናሽናል ታውሂድ ጃማዝ’ ለትንሳዔው ዕለት የቦምብ ጥቃት ተጠያቂ ከሆኑ ሁለት ጽንፈኛ እስላማዊ ቡድኖች መካከል አንዱ ነበር።
ጋዜጣው የቡድሂስት ሴቶች በዶክተሩ መክነዋል ለሚለው ዘገባ ግን ማስረጃ አላቀረበም። በጽሑፉ ላይ ዶክተር ሻፊ በስም አልተጠቀሱም። አምክነዋል የተባሉት ዶክተር ማንነትም አልተገለጸም።
ነገር ግን ቡድሂስት ሴቶችን ያመከኑት ዶክተር ሻፊ ናቸው በሚል ፎቷቸው ጋር የተያያዘ ጽሑፎች ፌስቡክ ላይ መውጣት ጀመሩ።
“በቀጥታ በይፋ የተወነጀልኩት ለመጀመሪያ ጊዜ በዚያ ሁኔታ ነው” ሲሉ ዶክተሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዶክተር ሻፊ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የቀረበባቸውን ሐሰተኛ ውንጀላ ዝም አላሉም። ጉዳዩንም ለሚሰሩበት የኩሬኔጋራ ማስተማሪያ ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶክተር ሳራ ዌራባንዳራ አሳወቁ።
ይህ ሐሰተኛ ወሬ በሕይወታቸው ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ስጋት ለዳይሬክተሯ ገለጹ። ሆኖም ዳይሬክተሯ ሆስፒታሉ ውስጣዊ ጉዳዮች እንጂ፣ ከሆስፒታሉ ውጪ ያለ ነገር አይመለከተውም አሉ።
ከሁለት ቀናት በኋላ ዶክተር ሻፊ በቁጥጥር ስር ዋሉ።
“ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድኩ። ሕዝባዊ ረብሻ እንዳይፈጠር ነው በሚል እስር ቤት ከተቱኝ” ይላሉ።

አደገኛው ሚዲያ
የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስለሁኔታው መዘገባቸውን ተከትሎ ጉዳዩ የበለጠ ትኩረት አገኘ። የሐሰት ውንጀላዎቹ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በስፋት ተጋሩ።
“ተወነጀልኩ። በይፋ አሸባሪ ተብዬ ተፈረጅኩ። መርዛማ አካሄድ ያላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቁ ሐሰተኛ ዜናዎች ሕይወቴን አበላሹት” ሲሉ ዶክተር ሻፊ ያለፉበትን ሁኔታ ይናገራሉ።
አንድ የቡድሂስት መነኩሴም የዶክተር ሻፊ ባለቤት ፋጡማ ኢማራ ትሰራበት ከነበረው ሆስፒታል ውጭ ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ።
“ባለቤቴ የግድያ ዛቻ ደርሶባታል። ለልጆቻችን ሕይወት ትፈራም ነበር” ሲሉም ዶክተር ሻፊ ባለቤታቸው ሥራዋንም ልታጣ ተቃርባ እንደነበር ያስረዳሉ።
“ታላቋ ልጄ ለፈተና እየተዘጋጀች ነበር፤ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ብትፈልግም በነበረው የሕዝብ ቁጣ የተነሳ ያንን ማድረግ አልቻለችም። እሷም በጣም ጭንቀት ውስጥ ገባች። ለልጆቻችን አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን መፈለግ ነበረብን” ሲሉም አክለዋል።
ዶክተር ሻፊ ከታሰሩ በኋላም ባለቤታቸው እና ሦስት ልጆቻቸው ወደ ዋና ከተማዋ ኮሎምቦ ተዘዋወሩ። ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ልጆቻቸው በሦስት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ገብተዋል።
“ባለቤቴ እና ልጆቼ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተሳደዱ ለመኖር ተገደዱ። የባንክ አካውንቴም ስለታገደ ገንዘብ አልነበራቸውም” ሲሉ ዶክተር ሻፊ ያስረዳሉ።
የሆስፒታሉ ባለሥልጣናት ወደ 800 ከሚጠጉ ሴቶች ስለ ዶክተር መሐመድ ሻፊ “ቅሬታ” ደርሶናል ቢሉም፣ ሰኔ ወር 2019 ላይ የሲሪሊንካ የወንጀል ምርመራ ክፍል (ሲአይዲ) በዶክተር ሻፊ ምስጢራዊ የማምከን ውንጀላ ላይ ምንም ማስረጃ አላገኘሁም ሲል ለፍርድ ቤት አስታወቀ።
በተጨማሪም የሲሪላንካ የደኅንነት አገልግሎትን ጨምሮ የሕግ አስከባሪ አካላት እና የፀጥታ ቢሮዎች ዶክተር ሻፊ ከየትኛውም የሽብር ተግባር ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም አሉ።

የምርጫ ዘመቻ
የትንሳዔ ዕለቱን የቦምብ ጥቃት ተከትሎ የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ኃላፊ ጎታባያ ራጃፓክሳ ለምርጫ እንደሚወዳደሩ እና የእስልምና አክራሪነትን መስፋፋት እንደሚያስቆሙ ቃል ገቡ።
ጎታባያ የአገሪቱ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ማሂንዳ ራጃፖክሳ ወንድም ናቸው።
በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2019 በተደረገው የምርጫ ዘመቻ ፀረ ሙስሊም እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ሁኔታ ታዩ።
“ዘረኝነት ሱስ ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ የዘረኝነት ሱስ ያለባቸው ሰዎች፣ ስለጉዳዩ በኩራት ያወራሉ” ይላሉ ዶክተር ሻፊ።
“የሲሪላንካ ፖለቲከኞች እኔን እንደ ጭራቅ ነው የሚስሉኝ። ይህ ደግሞ በቃላት የማይገለጽ ህመም ነው” ብለዋል።

የማምከኛ ክኒኖች እና ጄል
ሴቶችን ማምከን ሙስሊሞች ሲሪላንካን ለመቆጣጠር የሚጠቀሙበት መሳሪያ ነው የሚለው የሴራ ጽንሰ ሐሳብ ከዚህ ቀደምም ተከስቶ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2018 አንድ የሙስሊም ሬስቶራንት ባለቤት ቡድሂስት ደንበኞቹን ኢላማ በማድረግ የማምከኛ ክኒኖችን በምግብ ላይ ይጨምራል በሚልም ተከሰሰ።
ይህም ሁኔታ በሬስቶራንቱ እንዲሁም በሙስሊም በተያዙ ሱቆች እና ሆቴሎች ላይ የተነጣጠረ ጥቃት በጽንፈኛ ቡድሂስቶች እንዲፈጸም አነሳስቷል።
ዶክተር ሻፊ ከታሰሩ በኋላ ታዋቂው የቡድሂስት መነኩሴ ዋራካጎዳ ስሪ ግናራታና፣ የሙስሊሞች በድንጋይ ነወገርን በይፋ ደገፉ። ከዚህም በተጨማሪ ቡድሂስቶች በሙስሊም ባለቤትነት ወደ ተያዙ መደብሮችም ሆነ ሬስቶራንቶች ከመሄድ እንዲቆጠቡ ቀሰቀሱ።
ሌላኛው የተነዛው ወሬ የሙስሊም የልብስ መደብሮች በቡድሂስት ሴቶች የውስጥ ልብሶች እና ሱሪዎች ላይ የማምከኛ ጄል ያስቀምጣሉ ተባለ።
ወሬው በማኅበራዊ ሚዲያ በከፍተኛ ሁኔታ የተሰራጨ ሲሆን፣ አክራሪ ቡድሂስቶች በሙስሊም መደብሮች ግብይት እንዳይካሄድ ከመልከልም በላይ ጥቃት ሰነዘሩ።
ይህ ክስተትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የማምክኛ ክኒኖችም ሆነ ጄል የሉም የሚል መግለጫ እንዲያወጣ አስገድዶታል።
የመገናኛ ብዙኃን ሥነምግባር
የሲሪላንካ ወጣት ጋዜጠኞች ማኅበር በአገር ውስጥ ጋዜጦች፣ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እና ድረ-ገጾች ላይ እየወጣ የነበረውን ሐሰተኛ ዘገባ በመቃወም ድምጽ ካሰሙ ጥቂት ተቋማት መካከል አንዱ ነው።
የማኅበሩ ሊቀመንበር ታሪንዱ ጃያዋርዴና እንዳለው፣ በወቅቱ ስለክስተቱ ብዙ ተጨባጭ የሆኑ እና ምርመራ የተካሄደባቸው ጽሑፎች አልታተሙም።
ቢቢሲ የተለያዩ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞችን ባናገረበት ወቅት የሁለቱንም ጎን የሚሸፍኑ የምርመራ ጽሑፎቻቸው አይታተምም ተብለው የቀሩት ጋዜጠኞችን አግኝቷል።
አዘጋጆቹ “አንባቢዎችን ያስቆጣል እንዲሁም በጋዜጣው ሸያጭ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል” ብለው ስለሚፈሩ ከማተም እንደተቆጠቡም ተናግረዋል።
ታሪንዱ እንደሚሉት በዶክተር ሻፊ ላይ በጋዜጦች፣ በቴሌቪዥኖችም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይወጡ የነበሩ የጥላቻ ዘመቻ ዘገባዎች የቡድሂስት መነኮሳት ሙስሊሞች በድንጋይ ተወግረው እንዲገደሉ ጥሪ እንዲያቀርቡ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። የሚቀርቡት ዘገባዎች በሙሉ መሠረት የሌላቸው ነበሩ ይላሉ።
“ስለ ዶክተር ሻፊ ምስክርነታቸውን ከሰጡት መካከል 168ቱ ያህሉ ብቻ ለማርገዝ የተቸገሩ እንደሆኑ ደርሰንበታል። ሌሎቹ ለምርመራ የመጡ እንዲሁም ዜናውን ከሰሙ በኋላ ቅሬታቸውን ለማቅረብ እንደመጡ አውቀናል። ዶክተር ሻፊ ከታሰሩ በኋላም ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል 120 ሴቶች ወልደዋል” ሲሉም አክለዋል።

ንጽህናን ማረጋገጥ
የተከሰሱበትን ወንጀል የሚደግፉ ማስረጃዎች ባለመገኘታቸው ዶክተር ሻፊ ይሰሩበት በነበረው ኬሩኔጋላ ማስተማሪያ ሆስፒታል በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ላይ ወደ ሥራ ተመለሱ።
ለሦስት ዓመታት ያልተከፈላቸው ወደ 8 ሺህ 750 ዶላር እንዲከፈላቸው ተወሰነ። እሳቸው ይህንን ገንዘብም ለአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶችን እንዲገዛበት ለገሱ።
ሲሪላንካ በምጣኔ ሃብት ቀውስ እየታመሰች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የሲሪላንካ ዶክተሮች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ መሰደድን መርጠዋል።
ዶክተር ሻፊ ግን በሐሰት በተከሰሱበት ሆስፒታል ለመቆየት እና ሕዝባቸውን መልሰው ለማገልገል ቆርጠዋል።
“የቤተሰቤ አባላት በዚህ ሆስፒታል እንዳልሠራ ደጋግመው መክረውኛል። ነገር ግን ንጹህ መሆኔን የማረጋግጥበት ብቸኛው መንገድ ወደ ነበርኩበት ሆስፒታል ተመልሼ በተመሳሳይ የኃላፊነት ቦታ ላይ በመቀመጥ ማገልገል ብቻ እንደሆነ አውቃለሁ” ብለዋል።