July 16, 2023 – BBC Amharic 

ጥንዶቹ ጆናታን ጆንሰን እና ጆ ኤማ ላርቪን እአአ 2020 ላይ 2.3 ሚሊዮን ፓዎንድ አጓጉዘዋል።
የምስሉ መግለጫ,ጥንዶቹ ጆናታን ጆንሰን እና ጆ ኤማ ላርቪን እአአ 2020 ላይ 2.3 ሚሊዮን ፓዎንድ አጓጉዘዋል።

16 ሀምሌ 2023, 09:52 EAT

ከለንደን ዱባይ የወንጀለኞችን ሚሊዮን ፓውንዶች ሲያመላልሱ የነበሩ ስድስት ሰዎች ቅጣት ተላለፈባቸው።

ጆ ኤማ ላርቪን፣ ጆናታን ጆንሰን፣ ቢትሪስ ኦቲ፣ አሜረ ሃሪሰን፣ ኒኮላ ኤሰን እና ሞሐማድ ኢልያስ የተባሉት ስድስት ግለሰቦች ከ2019-2020 ባለው ጊዜ ነው ገንዘቡን ያመላለሱት ይላሉ መሪማሪዎች።

ረቡዕ ዕለት በዩናይትድ ኪንግደም በነረበው ችሎት ቢትሪስ ኦቲ የ42 ወራት እስር ሲፈረድባት ሌሎቹ ደግሞ ከ12 እስከ 24 ወራት የሚረዝም የገደብ እሥር ተላልፎባቸዋል።

የገደብ እስር የተላለፈባቸው ግለሰቦች ከእስር ቤት ውጪ የሚቆዩ ቢሆንም የገደብ እስሩ በተፈረደባቸው ጊዜ ውስጥ ወንጀል ከፈጸሙ የገደብ ቅጣቱ ተግባራዊ ይሆንባቸዋል።

ባፈለው ሚያዚያ ነበር ግለሰቦቹ የወንጀለኛ ንብረት በማጋዝ በሚል ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉት።

ብሔራዊው የወንጀል ኤጀንሲ እንደሚለው ሁሉም ሰዎች የአንድ ትልቅ ገንዘብ አመላላሽ ቡድን አባላት ናቸው።

ቡድኑ ቢያንስ 104 ሚሊዮን ፓውንድ ከዩኬ እንዲወጣ ያደረገ ሲሆን የቡድኑ መሪ አብደላህ አልፋላሲ ባለፈው ዓመት የዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር እሥር ተፈርዶበታል።

ችሎቱ ላይ እንደተሰማው ግለሰቦች ከ2019 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ለንደን ባለው ሂትሮ አየር ማረፊያ በኩል ባደረጓቸው 83 በረራዎች ነው ገንዘቡን ወደ ዱባይ የወሰዱት።

ለእያንዳንዱ ጉዞ ቢያንስ 3 ሺህ ፓውንድ የሚከፈላቸው ሲሆን ተጨማሪ ሻንጣ መሸከም እንዲያስችላቸው ‘ቢዝነስ ክላስ’ ነው የሚበሩት።

ቡድኑ ዋትስአፕ በተባለው የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ ላይ ‘ሰንሻይን ኤንድ ሎሊፖስ’ የተባለ ቡድን ፈጥረው መልዕክት ይለዋወጡ ነበር።

ዱባይ ገብተው ገንዘቡን ሲያሳውቁ ኦምኒቬስት ከተሰኘ ድርጅት የመጣ ደብዳቤ ያስረክባሉ።

መርማሪዎች እንደሚሉት ገንዘብ አመላላሹ ቡድን ፓውንድ የሚያገኛው ዩኬ ውስጥ ከሚደረገ የአደገኛ ዕፅ ንግድ ነው።

ቢትሪስ ኦቲ
የምስሉ መግለጫ,ቢትሪስ ኦቲ የ42 ወራት እስር ተላልፎባታል።

ገንዘቡን በፕላስቲክ ግጥም አድርገው ካሰሩ በኋላ አነፍናፊ ውሾች በሽታ እንዳይደርሱበት የቡና አሊያም ‘ኤር ፍሬሽነር’ ጠረን ያደርጉበታል።

መርማሪዎች አክለው እንደገለጡት በአንድ ጉዞ ቢያንስ ግማሽ ሚሊዮን ፓውንድ ያጓጉዛሉ።

የ27 ዓመቷ ኦቲ በትንሹ ሰባት ጊዜ በአጠቃላይ 3.4 ሚሊዮን ፓውንድ መጠን ያለው ሻንጣ ይዛ ተጉዛለች።

አልፎም ለሌሎች 16 ጉዞዎች ሁኔታዎችን አመቻችታለች ይላል የወንጀል ቁጥጥር ኤጀንሲው።

ከሌሎች አጋሮቿ ጋር በመሆን 2.2 ሚሊዮን ፓውንድ የያዙ ሰባት ሻንጣዎች ተሸክማ ጉዞ አድርጋለችም ተብሏል።

አንድ ሌላ ግለሰብም እንዲሁ የፍርድ ሂደት ይጠብቀዋል። ሌሎች አራት ግለሰቦች ደግሞ በሚቀጥለው ኅዳር ችሎት ፊት ይቀርባሉ።