
16 ሀምሌ 2023, 11:19 EAT
በደቡብ አውሮፓ አገራት የተመዘገበው ከፍተኛ ሙቀት በቀጣይ ሳምንትም እንደሚኖር ማስጠንቀቂያ ተሰጠ።
ጣልያን፣ ስፔን እና ግሪክ ባለፉት በርካታ ቀናት ከፍተኛ ሙቀት ከተመዘገበባቸው አገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የጣሊያ ጤና ሚኒስቴር በቀጣይ ቀናት ሮም፣ ቦሎኛ እና ፍሎረንስን ጨምሮ በ16 ከተሞች ከፍተኛ ሙቀት ይኖራል የሚል ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።
ሙቀቱ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚኖር የተተነበየ ሲሆን በጣሊያኗ ሳርዲኒያ ከተማ ሙቀቱ 48 ዲግሪ ሴሊሺዬስ ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል።
“የሙቀት መጠኑ ከሐምሌ 12 እስከ 16/2015 ዓ.ም. ባሉት ቀናት በጣሊያን፣ ግሪክ፣ ቱርክ እና ባልካን አገራት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። በእነዚህ ቀናት በተለያዩ ስፍራዎች ከዚህ ቀደም ከተመዘገቡ ከፍተኛ የሙቀት መጠን በላይ ሊመዘገብ ይችላል” ብለዋል የጣሊያ ብሔራዊ ሚቲሪዮሎጂ ባልደረባ ጊዩሊኦ ቤቲ ለቢቢሲ ሲናገሩ።
የጣሊያን መንግሥት ከፍተኛ ሙቀት ይከሰትባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች ከረፋዱ 5 ሰዓት እስከ አመሻሻ 12 ሰዓት ድረስ እራሳቸውን ለሃሩር ጸሐይ እንዳያጋልጡ ማሳሰቢያ አስተላልፏል።
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን 9 ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመች16 ሀምሌ 2023
- ከምዕራባውያን ጋር ፍጥጫ ውስጥ ያለችው ኢራን ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነትን በአራት ነጥቦች16 ሀምሌ 2023
- የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን ተዋጊዎች በከፍተኛ ቁጥር ቤላሩስ መግባታቸውን ዩክሬን ገለጸች16 ሀምሌ 2023
በጣሊያን ያለው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ጎብኚዎች በእግር እየተዘዋወሩ መስህቦችን እንዳይመለከቱ ስለማድረጉ በሮም አስጎብኚ የሆኑት ፌሊሲቲይ ሆንተን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ሮም ሁሌም ሞቃታማ ነው። ይሄ ግን ከተለመደው በተለየ ለረዥም ግዜ በጣም ሙቀት ሆኗል። እኔ እና አስጎብኚ ባልደረቦቼ በዚህ በጣም ተፈትነናል። በጉብኝት ወቅት በሙቀቱ ምክንያት ሰዎች እራሳቸውን እየሳቱ እየወደቁ ነው” ብለዋል።
በተመሳሳይ በግሪክ የሙቀት መጠኑ 40 ዲግሪ ሴሊሺዬስ የተሻገረባቸው በርካታ አካባቢዎች አሉ። በአቴንስ ጎብኚዎችን ለመጠበቅ ሲባል የቱሪዝስት መስህቦች አርብ እና ቅዳሜ ዝግ እንዲሆኑ ተደርገው ነበር።
በስፔን ካናሪ ደሴቶች ደግሞ የተቀሰቀሰው እሳት 4ሺህ ሰዎችን ያፈናቀለ ሲሆን እሳቱ እስካሁን ድረስ 4ሺህ 500 ሄክታር መሬት አውድሟል።
በተለያዩ የዓለማችን ከፍሎች በየዓመቱ እየተመዘገ ያለው የሙቀት መጠን እና ሙቀቱ የሚቆይበት ግዜ እየጨመረ መጥቷል።
“የሙቀት ማዕበሎች በየዓመቱ እየጨመሩ ነው። የንብረት ለውጥ ስለመኖሩ ግልጽ ማሳያ ናቸው” ይላሉ የጣሊያን ሜትሪዮሎጂ ባለሙያው ቤቲ።
“የአውሮፓውያን ሞቃታማ ወራቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጣም ሞቃታማ እየሆኑ መጥተዋል። ሊያሳስበን የሚገባው ሞቃታማ ወራቶች ከአሁን በኋላ በጣም ሞቃታማ መሆናቸው ነው። የተለመደ የምንለው ሞቃታማ ወራት ከአሁን በኋላ በቀላሉ አይገኙም።” ይላሉ የሜትሪዮሎጂ ባለሙያው።
እንደ የአውሮፓ ኅብረት የአየር ንብረት ለውጥ ክትትል አገልግሎት ከሆነ ባለፈው ሰኔ የነበረው ወር በአውሮፓ ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበበት ወር ሆኖ አልፏል።