July 16, 2023 – BBC Amharic

ሳልማ ሃየክ ብላክ ሚረር በተሰኘው የኔትፍሊክስ ፊልም ላይ ስትተውን

16 ሀምሌ 2023, 12:56 EAT

ተሻሽሏል 16 ሀምሌ 2023, 12:56 EAT

የሆሊውድ ተዋንያን ከ43 ዓመታት በኋላ አድማ መተው፤ ለተቃውሞ መንገድ ወጥተዋል።

እርግጥ ተዋንያኑ አድማ እንዲመቱ ያደረጋቸው አንደኛው ጉዳይ ክፍያ ነው።

አንደኛው ምክንያታቸው ደግሞ ሰው ሠራሽ አስተውሎት [አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ] የደገነባቸው አደጋ ነው።

ስክሪን አክተርስ ጊልድ የተሰኘው የባለሙያዎቹ ማሕበር ኤአይን በተመለከተ ከስምምነት መድረስ አልቻለም።

ማሕበሩ “ይህ ቴክኖሎጂ ለተዋንያን ሕይወት አደጋ የደቀነ ነው” ይላል።

የማሕበሩ ዋና ተደርዳሪ ደንካን ክራብትሪ-አየርላንድ እንደሚሉት ፊልም አምራቾች የተዋንያንን ፊት ወስደው የአንድ ቀን ብቻ ከፍለው “ለዘላለሙ መጠቀም ይፈልጋሉ።”

ይህ ብላክ ሚረር በተሰኘው ታዋቂ የኔትፍሊክ ተከታታይ ፊልም ያለውን ትዕይንት ይመስላል።

“ጆዋን ኢዝ ኦውፉል” በተሰኘው አንድ የብላክ ሚረር ክፍል ላይ ሳልማ ሃየክ የተሰኘችው ተዋናይት ኤአይ ያለፍላጎቷ ድምፅና ምስሏን ወስዶ እንዳሻው ፊልም ሲሰራ ይታያል።

እነሆ ይህ ፊልም እውን ሊሆን የሚለው የሆሊውድ ተዋንያን ስጋት ነው።

እርግጥ ነው ቻትጂፒቲ አሊያም ባርድ አንድ አስደናቂ ፊልም የሚወጣው ድርሰት መፃፋቸው የጊዜ ጉዳይ እንጂ የሚቀር አይመስልም።

አንዳንዶች ሰው ሰራሽ አስተውሎት የፊልም ፅሑፍ ለመፃፍ የሚያስችል ሰው ሰው የሚሸት ነገር የለውም ይላሉ።

የሆሊውድ ብቻ ሳይሆኑ የዩናይትድ ኪንግደም ተዋንያንም ጭምር የኤአይ ነገር ያሳሰባቸው ይመስላል።

ቴክኖሎጂ “ማንኛውንም ነገር ማድረግ ይችላል” በሚባልበት ዘመን ተዋንያንና ፀሐፊያን ይህ ጉዳይ ቢያሳስባቸው የሚገርም አይደለም።

ፊልም ደራሲዋ ጀስቲን ቤትማን “ሲጀመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወደ መዝናኛው ኢንዱስትሪ ሊመጣ አይገባም ነበር” ትላለች።

“ቴክኖሎጂ ችግር ሊፈታ ነው እንጂ የሚገባው እንጂ ወደዚህ ኢንዱስትሪ የሚያመጣው ምንም የለመው። የፀሐፊ እጥረት የለብንም፤ የተዋናይ ችግር የለብንም፤ ፊለም የሚሠራ አልጠፋም። ኤአይ አያስፈልገንም።”

እሷ እንደምትለው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ወደ ፊልም ኢንዱስትሪ የመጣበት ምክንያት ትርፍ ለማጋበስ ነው።

አሁን የዩኬም ሆነ የሆሊውድ ተዋንያን ፀሐፊያን የሚፈልጉት አንድ ነገር ነው።

ፊልም የሚያመርቱ ትላልቅ ድርጅቶች ከተዋናይ አሊያም ከፀሐፊ ፈቃድ ውጭ አንድን ሥራ ለገበያ እንዳያቀርቡ የሚል።

አልፎም ኤአይ የአንድን ሰው ሥራ አስመስሎ ከመፈብረኩ በፊት ሁሉም በግልጥ ሊያሳውቅ ይገባል ይላሉ።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት በተለይ ባለፈው ዓመት ያሳየው ፈጣን ዕድገት የባለቤትነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።

አብዛኛዎቹ ኤአይ የሚያመርታቸው ፎቶዎችም ሆነ ቪደዮዎች የንብረት ባለቤትነታቸው በኮፒራይት ሕግ የተጠበቀ አይደለም።

በርካቶች ይህ ሊቀየር ይገባል፤ አዲስ ሕግ ይፋ መሆን አለበት የሚል ጥያቄ አላቸው።