
15 ሀምሌ 2023
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ፖለቲከኞችን እና ፖሊሲ አውጪዎችን እያሳሰቡ ካሉ ጉዳዮች አንዱ ሕገወጥ ስደት ነው።
ዩኬ ሕገወጥ ያለችውን ስደት ለመቆጣጠር ረቂቅ ሕግ ያወጣች ሲሆን፣ መጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሶ ለአገሪቱ ፓርላማም ቀርቧል።
ሆኖም ግን ሂደቱ ቀላል አልሆነም፣ ረቂቁ በፓርላማው ውስጥ ፈተናዎች እየገጠሙት እንደሆነ ተጠቅሷል።
ረቂቅ ሕጉ በዋነኝነት በፈረንሳይ በኩል በትንንሽ ጀልባዎች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚገቡ ስደተኞችን ለማስቆም ያለመ ነው።
በባለፈው ዓመት ከፍተኛው ቁጥር ነው የተባለው ስደተኞች ወደ አገሪቱ መግባታቸውን ተከትሎ ነው ይህ ረቂቅ ሕግ የተዘጋጀው።
ረቂቅ ሕጉ ምን ይዟል? በስደተኞችስ ላይ ምን አይነት ተጽእኖ ያስከትላል? እንዲሁም ረቂቁ ሕግ የገጠመው ፈተና ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን እንመለስባቸዋለን።
መጀመሪያ ግን ስደተኞች በሕጋዊ መንገድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚያቀኑበትን መንገዶች እንመልከት።
“ደኅንነታቸው የተጠበቀ እና ሕጋዊ መንገዶች”
የስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከተው የዩኬው ‘ሆም ኦፊስ’ የተሰኘው የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መምጣት ለሚፈልጉ “ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ሕጋዊ” መንገዶች እንዳሉ አበክሮ ሲያስታውቅ ይሰማል።
ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የመንግሥት መርሃ ግብሮች እንደ አፍጋኒስታን እና ዩክሬን ካሉ አገራት ለሚመጡ ስደተኞች የተወሰነ ነው።
ሌሎቹ መንገዶች ደግሞ የተወሰኑ ስደተኞችን የሚቀበሉ ናቸው። እስካለፈው መጋቢት ድረስ ዩኬ በተለያዩ መንገዶች በጥገኝነት የተቀበለቻቸው ስደተኞችን ቁጥር እና መንገዶችን እንመልከት።
- የዩኬ የመልሶ ማስፈር መርሃ ግብር (ሪሴትልመንት ስኪም) – ይህ መርሃ ግብር በጦርነት እና በግጭት እየታመሱ ላሉ አገራት ቅድሚያ ይሰጣል። በዚህ ፕሮግራም 1056 ግለሰቦች የዩኬ ጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል።
- የማኅበረሰብ ስፖንሰርሺፕ መርሃ ግብር (ኮሚዩኒቲ ስፖንሰርሽፕ ስኪም) – ይህ ፕሮግራም ግለሰቦች ተሰባስበው ወይም ማኅበረሰብ ስደተኞችን ለመደገፍ እና ‘ስፖንሰር’ የሚያደርጉበት መንገድ ነው። ስደተኞችን ከአካባቢው ባህል እና ወግ ጋር እንዲላመዱ መርዳትን ጨምሮ የቋንቋ እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ በዩኬ ሕይወታቸውን እንዲገነቡ በጋራ የሚደግፉበት ፕሮግራም ነው። በዚህም ፕሮግራም 309 ግለሰቦች ተጠቃሚ ሆነዋል።
- ስደተኞችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት መርሃ ግብር (ሪፊውጂ ፋሚሊ ሪዩኒየን ስኪም) – በዩኬ ዜግነት ያገኙ ወይም ጥበቃ የተሰጣቸው ስደተኞች ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆቻቸውን፣ እንዲሁም የትዳር አጋሮቻቸውን የሚያመጡበት ፕሮግራም ነው። በዚህም መንገድ 6029 ሰዎች ቪዛ አግኝተዋል።
- የሞግዚት መልሶ የማስፈር መርሃ ግብር (ማንዴት ሪሴትልመንት ስኪም) -ስደተኞቹ በዩኬ የቅርብ ቤተሰብ (ዘመድ) ካላቸው እና መኖሪያ የሚሰጧቸው ከሆነ በአገሪቱ ተቀባይነት የሚያገኙበት ፕሮግራም ነው። እስካሁን ድረስ ስድስት ሰዎች የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ከአውሮፓውያኑ 2004 ጀምሮም 430 ግለሰቦች ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል።
በሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላም ግጭቱን ሸሽተው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መምጣት ለሚፈልጉ ታዳጊዎች “ደኅንነታቸች የተጠበቀ እና ሕጋዊ መንገዶች” አሉ ወይ? ይህ ጥያቄ ሚያዝያ መጨረሻ ላይ ለዩኬ የኢሚግሬሽን ሚኒስትር ሮበርት ጄንሪክ በፓርላማ የቀረበላቸው ነው።
እሳቸውም በምላሹ “የተሻለ ምክር ብዬ የምሰጠው ግለሰቦች ጉዳያቸውን ለተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ (ዩኤንኤችሲአር) እንዲያቀርቡ ነው። እኛ ከኤጀንሲው ጋር ደኅንነቱ በተጠበቀ እና እና ሕጋዊ በሆኑ መንገዶች እንሰራለን” ብለዋል።
ነገር ግን የተመድ ስደተኞች ኤጀንሲ በበኩሉ “በዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ለመጠየቅ የሚያስቡ ስደተኞች በዩኤንኤችሲአር በኩል የሚመጡበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም” ብሏል።
- “ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከዩኬ ወደ ሩዋንዳ መላክ ዓለም አቀፍ ሕግን ይጻረራል” ተመድ16 ሚያዚያ 2022
- በዩኬ 12 ሺህ ጥገኝነት ጠያቂዎች ቃለ መጠይቅ አያስፈልጋቸውም ተባለ23 የካቲት 2023

ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ዩኬ ምን ዕቅድ ይዛለች?
በአውሮፓውያኑ 2023 ሕገወጥ ስደትን በሚመለከት በተዘጋጀ ረቂቅ ሕግ መሠረት፦
- የስደተኞችን ጉዳይ በበላይነት የሚቆጣጠረው ሆም ኦፊስ በሕገወጥ መንገድ ወደ ዩኬ የገቡ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር ሊያውሉ ወይንም ወደ ሩዋንዳ ወይም ወደ ሌላ “ደኅንነቱ የተጠበቀ” ሦስተኛ አገር የማስወጣት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
- ሕገወጥ የተባሉት ስደተኞች ወደ ዩኬ በገቡ በመጀመሪያዎቹ 28 ቀናት የዋስ መብታቸው አይጠበቅም፣ እንዲሁም ሕጋዊ መፍትሄዎችን መሻት አይችሉም።
- ሆኖም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ፣ በጤና ምክንያት ለመጓዝ ብቁ ያልሆኑ ወይም በሚሄዱበት አገር ለከባድ ጉዳት የሚጋለጡ ከዩኬ የሚወጡበት ሁኔታ እንዲዘገይ ይደረጋል።
ዩናይትድ ኪንግደም “በአስተማማኝ እና ሕጋዊ መንገዶች” የምታሰፍራቸው ስደተኞች ቁጥር ከፈረንሳይ ጋር በተደረገው አዲስ ስምምነት መሠረት እንዲገደብ ተደርጓል።
ይህም ስምምነት ስደተኞች ፈረንሳይን ተሻግረው ወደ ዩኬ እንዳይገቡ ለማደረግ ለተጨማሪ የጥበቃ መኮንኖች እንዲሁም እንደ እስር ቤት ሊቆጠር የሚችል አዲስ የማቆያ ግንባታ 500 ሚሊዮን ፓውንድ የሚከፈልበት ነው። ዩኬ ይህንን ክፍያ ለፈረንሳይ በሦስት ዓመታት ውስጥ ትከፍላለች።
በተጨማሪም የዩኬ መንግሥት እንዳለው ከአልባኒያ ጋር በተደረገ የመመለሻ ስምምነት በትንንሽ ጀልባዎች ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ቀንሷል።

በረቂቅ ሕጉ ላይ ፓርላማው ምን ለውጦችን አደረገ?
በላይኛው ምክር ቤት አንዳንድ የምክር ቤት አባላት በረቂቅ ሕጉ ላይ ለውጦች እንዲደረጉ ጫና ማድረጋቸውን ተከትሎ አንዳንድ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።
አንደኛው የቀረበው ወደ ዩኬ ለመምጣት የሚያስችሉ “ደኅንነታቸው የተጠበቁ እና ሕጋዊ” የተባሉ መንገዶችን መንግሥት ማስረጃ ማቅረብ አለበት የሚል ነው።
እንዲሁም እነዚህም መንገዶች የሚሰፉበትን ዕድል መፈለግ የሚል ሲሆን፣ ሌላኛው የዘመናዊ ባርነት ሰለባ ነን ለሚሉ ስደተኞች ከለላ እና ጥበቃን የሚመለከት አንቀጽ በረቂቅ ሕጉ እንዲካተት ሐሳብ ቀርቧል።
በሕዝብ ምክር ቤት በመጨረሻው ዙር ድምጽ አሰጣጥ ወቅት ከአንዳንድ ወግ አጥባቂ የፓርላማ አባላት ትችት ቢያስተናግድም፣ በምክር ቤቱ አባላት የተሰጡ ማሻሻያዎች በሙሉ ተቀባይነት እንዳገኙ ውሳኔ ተላልፏል።
በተጨማሪም መንግሥት ህጻናት አና ነፍሰ ጡር ሴቶች በቁጥጥር ስር የሚቆዩበትን ጊዜ የሚገድብ እና ሌሎች ለውጦችን እንዳካተተ አስታውቋል።
ረቂቅ ሕጉ እንደገና ወደ ፓርላማው ይመለስና የፓርላማ አባላቱ የተደረጉ ማሻሻያዎችን ያጤናሉ።
ዓለም አቀፍ ሕግ ስለስደተኞች ምን ይላል?
የዩኬ የስደተኞች የጥገኝነት ረቂቅ ሕግን የሚቃወሙ እንደ የስደተኞች ምክር ቤት ያሉ ተቋማት፣ ይህ ዓለም አቀፍ ሕግን የመጣስ አደጋን የጋረጠ ነው በማለት ይተቻሉ።
የአውሮፓውያኑ 1951 የስደተኞች ስምምነት ዋነኛ መርኅ ስደተኞች ለሕይወታቸውም ሆነ ለነጻነታቸው ስጋት ወደ ሚያድርባቸው አገራት ሊመለሱ አይገባም ይላል።
የዩኬ መንግሥት ግን የጥገኝነት ጉዳያቸው እንዲታይ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ዕቅድ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር አይጣረስም ይላል።
ነገር ግን የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ መላክ ሕገወጥ እንደሆነ እና የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 3ን ሊጥስ እንደሚችል በመጥቀስ ባለፈው ሰኔ ወር ውሳኔ አሳልፏል።
የዩኬ መንግሥት ይህንን ውሳኔ ይግባኝ በማለት ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊወስድ መሆኑንም አስታውቋል።
የዩኬ መንግሥት ስለ ስደተኞች መጠለያ ምን አለ?
በኢሴክስ፣ ሊንከንሻየር እና ምሥራቅ ሰሴክስ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ የቀድሞ ወታደራዊ ጣቢያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን እንደሚያስተናግዱ በመጋቢት ወር ተነግሯል።
በዶርሴት ግዛት የሚገኘው ቢቢ ስቶክሆልም የተሰኘው ጀልባ እስከ 500 የሚደርሱ ጎልማሳ ጥገኝነት ጠያቂዎች እንደሚስተናገዱበት ሚያዝያ ወር ላይ ተገልጿል።
በዮርክሻር በሚገኘው ካተሪክ ጋሪሰን በተሰኘው ስፍራ ሌላ የመጠለያ ጣቢያ በቅርቡ ይከፈታል።
የሊንከንሻየር እና ኢሴክስ የአካባቢ ምክር ቤቶች የቀድሞ ወታደራዊ ጣቢያዎች የጥገኝነት ጠያቂዎች መቆያ እንዳይሆኑ ያቀረቡት መከራከሪያ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጎባቸዋል።
የዩኬ መንግሥት የስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ እየወሰደ ያለው እርምጃ ለመጠለያዎች የሚያወጣውን የገንዘብ መጠን እንደሚቀንስ ተስፋ አድርጓል።
በአሁኑ ወቅት በዩኬ ከ51 ሺህ በላይ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች በተለያዩ ሆቴሎች ውስጥ ይኖራሉ። አንድ የሆም ኦፊስ ባለሥልጣን በቅርቡ እንደተናገሩት በማቆያ ማዕከላት ያለውን መጨናነቅ ለመቀነስ ወደ 5 ሺህ የሚጠጉ የሆቴል አልጋዎችን ባዶ ለማድረግ መሥሪያ ቤታቸው እየከፈለ እንደሆነ ነው።
ማብራሪያ፦ ይህ ጽሁፍ መንግሥት “ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ሕጋዊ” መንገዶች የሚላቸው አማራጮች ቀድሞውኑ የስደተኛ እውቅና ለተሰጣቸው፣ እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ነዋሪነታቸውን ላደረጉ የስደተኞች ቤተሰብ አባላት ብቻ እንደሆነ ግልጽ ለማድረግ ማሻሻያ ተደርጎበታል።