July 17, 2023 – EthiopianReporter.com


ዘንድሮ በማዳበሪያ ዕጦት የተቸገሩ አርሶ አደሮች በተለያዩ አካባቢዎች አቤቱታ እያሰሙ ነው

ማኅበራዊ ‹‹ማዳበሪያን አጀንዳ ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ›› የክልሉ ግብርና ቢሮ

‹‹ማዳበሪያን አጀንዳ ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ›› የክልሉ ግብርና ቢሮ

ኤልያስ ተገኝ

ቀን: July 16, 2023

‹‹ማዳበሪያን አጀንዳ ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ››

የክልሉ ግብርና ቢሮ

በደቡብ ክልል የጉራጌ ዞን ወረዳዎች የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ባለማቅረቡ፣ አርሶ አደሮች አቤቱታቸውን ከመግለጽ ባለፈ፣ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ መግባታቸው ተገለጸ::
ከሰሞኑ የማዳበሪያ ዕጦት አማሮናል ያሉ በጉራጌ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች አደባባይ በመውጣት አቤቱታቸውን ሲገልጹ፣ በተለያዩ
የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ታይተው ነበር::

ሪፖርተር ጉዳዩን በተመለከተ በዞኑ ውስጥ ከሚገኙት ወረዳዎች አንዱ በሆነው የምሁርና አክሊል ወረዳ አርሶ አደሮችንና የኅብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎችን
አነጋግሯል::

ከምሁርና አክሊል ኅብረት ሥራ ጽሕፈትነ ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚገልጸው፣ በወረዳው ለአርሶ አደሩ ይቀርባል ተብሎ ከታሰበው ስምንት ሺሕ ኩንታል ውስጥ
የቀረበው የማዳበሪያ መጠን ከአንድ ሺሕ ሁለት መቶ ኩንታል አይበልጥም::

የቀረበው የማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የሚዳረስ ባለመሆኑ ጽሕፈት ቤቱ ‹‹በፌስታል›› ለማከፋፈል መገደዱ ተጠቁሟል::

የማዳበሪያ ሥርጭት ችግር የአንድ ወረዳ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በጉራጌ ዞን የገጠመ መሆኑን፣ አብዛኛው ማሳ ታርሶ በማዳበሪያ እጥረት ግን ዘር እየተዘራበት አለመሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አርሶ አደርና የኅብረት ጽሕፈት ቤት ባለሙያ አስረድተዋል::

‹‹የማዳበሪያ አቅርቦቱ አርሶ አደሩን ተስፋ አስቆርጦታል፣ ተስፋ አስቆራጭ ነገር ነው:: ከፍተኛ ብር አውጥቶ መግዛት አይችልም፣ ትንሹን ለማሠራጨት ስንሞክር ሰላማዊ ሠልፍ ስለሚወጣ ለማሠራጨት እንቸገራለን፤›› ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ባለሙያ ተናግረዋል::

የምሁርና አክሊል ወረዳ በአብዛኛው የውርጭ ተጠቂ አካባቢ በመሆኑ መጠን፣ የሚዘራው ከግንቦት ወር ጀምሮ ቢሆንም፣ የተገኘውም ማዳበሪያ እየቀረበ ያለው በሐምሌ ወር ስለሆነ አብዛኛው ሰብል ስላለፈው በመጪው ዓመት ምርት ላይ ችግር እንደሚፈጥር አርሶ አደሮች አስረድተዋል::

የማዳበሪያ አቅርቦት ችግሩ ከምሁርና አክሊል ወረዳ በተጨማሪ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች በተመሳሳይ ያጋጠመ መሆኑን፣ ይህንንም የሁሉም ወረዳዎች የኅብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት የጋራ መድረክ ሰሞኑን በተደረገበት ወቅት መንፀባረቁ ተሰምቷል::

የጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መሐመድ አብራር፣ ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተገናኘ ከአርሶ አደሩ ከፍተኛ ቅሬታ እየቀረበ እንደሆነና በተለይም በእጥረቱ ምክንያት ገበሬው ማዳበሪያ ከጉራጌ ዞን ወጣ ባሉ አካባቢዎች እየሄደ በችርቻሮ ለመግዛት መገደዱን አረጋግጠናል ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል::

‹‹ብዙ መረጃዎችን እየሰበሰብን ነበር:: በጉዳዩ ላይ መግለጫ ለመስጠት አስበናል:: አርሶ አደሮች የእርሻ ወቅት እያለፈባቸው ነው፤›› ሲሉ አቶ መሐመድ አስረድተዋል::

የደቡብ ክልል ግብርና ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ ከፍተኛ የሚባል የማዳበሪያ እጥረት ባይኖርም እጥረቱ ለአጭበርባሪዎች ዋነኛ መግቢያ በር ሆኗል ብለዋል::

‹‹በእርግጥ ከመጠን አንፃር ማነስ አለ፣ ከጊዜ አንፃር የተወሰነ ችግር አለ:: ችግር የለም ማለት አንችልም:: ነገር ግን ማዳበሪያ እየገባ ነው:: ይኼ ሁሉ ሆኖ ሲያበቃ እንደ ከዚህ ቀደሙ መጋዘን የሚከማችና የሚያድር ማዳበሪያ የለም፤›› ሲሉ አስታውቀዋል::

ቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎች በቅድሚያ ማዳበሪያ እንዲደርስ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ኡስማን፣ በቅደም ተከትል ዘር በጀመሩት የላይኛው የጉራጌ አካባቢዎች በተወሰነ ደረጃ፣ ሃድያ የተወሰነ፣ ሥልጤ የተወሰነ በደጋማው ክፍል መቅረቡን፣ የታችኛው ክፍሎች የመኸር ዘር ከሐምሌ 10 ቀን በኋላ የሚጀምር ነው ብለዋል::

‹‹እጥረት የለም፣ ዜሮ ነው የምንለው አይደለም:: ነገር ግን እጥረቱን ለማካካስ ቅደም ተከተል አውጥተን የማድረሱን ሥራ እየሄድንበት ነው፤›› ያሉት አቶ ኡስማን
‹‹ማዳበሪያውን መጋዘን ገብቶ ካላየሁት ብለው እዚም እዚያም የሚያጯጩሁና ማዳበሪያን አጀንዳ ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ:: እኔ ሠልፍ መወጣቱንም አላውቅም፣ እኛ ሥራውን እየመራነው እንገኛለን፤›› ሲሉ አክለዋል::

ለክልሉ በዘንድሮ የምርት ዘመን የቀረበው የማዳበሪያ ፍላጎት 780 ሺሕ ኩንታል ነው:: እስካሁን 500 ሺሕ ኩንትል እንደቀረበ፣ የቀረበውም ወደ መጋዘኖች ሳይሆን ቀጥታ ወደ ሥርጭት ጣቢያ እንደሆነና አሁንም መጠኑ እንጂ ማዳበሪያ በየቀኑ እየገባ መሆኑን ተገልጿል::

በመጠኑ የማዳበሪያ እጥረት ሲኖር ከደቡብ ወደ ኦሮሚያ፣ ከኦሮሚያ ወደ ደቡብ ወስደው የሚሸጡ ሕገወጦች መኖራቸውን፣ ማዳበሪያ ለመሸጥ ሕጋዊ ንግድ ፈቃድም ሆነ መብት አለመኖሩን፣ ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙ እየተያዙ ዕርምጃ እየተወሰደና ለሕግ እየቀረቡ እንደሚገኙ የግብርና ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል: