
ከ 3 ሰአት በፊት
የኢራን ፖሊስ ከአሁን በፊት አቁሞት የነበረውን በሴቶች ላይ የሚያደርገውን የሂጃብ አለባበስ ቁጥጥር እንደገና ሊጀምር መሆኑን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
እሁድ የአገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ መሠረት ሴቶች ፀጉራቸውን የሚሸፍን ሂጃብ ማድረጋቸውን ለመቆጣጠር “የሥነ ምግባር ፖሊሶች” እንደገና ወደ ጎዳናዎች ይሰማራሉ ብለዋል።
ይህ የሆነው አንዲት ወጣት ሂጃብ አልለበስችም በሚል በፖሊስ እስራት ላይ እያለች ሕይወቷ ካለፈ ከ10 ወራት በኋላ ነው። የእርሷ ሞት በመላ አገሪቱ ቁጣን ቀስቅሶ የፖሊስንም ቁጥጥር እንዲቀር አድርጎ ነበር።
በሌላ በኩል የእስልምና አክራሪ ወገኖች ፖሊስ ቶሎ ተመልሶ ቁጥጥሩን እንዲጀምር ሲጠይቁ ቆይተዋል። በአገሪቱ ሕግ መሠረት ሴቶች ሂጃብ የማድረግ እና ሙሉ ረጅም ቀሚስ የመልበስ ግዴታ አለባቸው።
የሞራል ፖሊስ ተብሎ የሚጠራው የፖሊስ ዘርፍ ዋነኛ ሥራው በጎዳናዎች እየተዘዋወረ ሴቶች ሕጉን አክብረው መልበሳቸውን መቆጣጠር እና ሕግ ተላልፈዋል የተባሉትን ማሰር ነው።
ቃል አቀባይ ለአገር ውስጥ ሚዲያ እንደሰጡት፣ ፖሊስ ሕጉን ያላሟሉ ሴቶችን በመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፣ ድጋሚ ሕጉን የሚጥሱ ከሆነ ግን እስራት ይጠብቃቸዋል ብለዋል።
ባለፈው መስከረም ወር የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ ሆስፒታል ስትሄድ ነበር ሂጃብ በትክክል አልለበስሽም ተብላ በፖሊስ የተወሰደችው።
- የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እና ሹመት፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የገጠማት ፈተናከ 5 ሰአት በፊት
- በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ችግኝ ለመትከል ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃልከ 4 ሰአት በፊት
- ውቅያኖስ ላይ ጠፍቶ የነበረው አውስትራሊያዊ ሁለት ወር ሙሉ ጥሬ ዓሣ እየበላ ከውሻው ጋር ተገኘከ 5 ሰአት በፊት
በፖሊስ እጅ እያለች ራሷን ስታ ሕይወቷ አልፏል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ማህሳ የሞተችው ፖሊሶች ራሷን ከመኪና ጋር አጋጭተዋት እና በኃይል ደብድበዋት ነው።
የእርሷን ሞት ተከትሎም በመላ አገሪቱ ከፍተኛ ተቃውሞ የቀሰቀሰ ሲሆን፣ 600 ለሚደርሱ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።
ተቃውሞው ከተጀመረ በኋላ ብዙ ኢራናውያን ሴቶች ሂጃብ መልበስ አቁመዋል። ይህ ከኢራን የ1979 አብዮት በኋላ ከፍተኛ የሃይማኖት ተቃውሞ ነው።
በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ ፎቶዎች እንደሚያሳዩት ሂጃብ ያልለበሱ ሴቶችን መመልከት በኢራን የተለመደ ሆኗል።
በምላሹ ግን የኢራን መንግሥት ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል።
የአለባበስ ሕጉን ያላሟሉ የንግድ ተቋማትን መዝጋትን ጨምሮ በሴቶች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። ተቃውሞው ብዙ ኢራናውያንን ቢያሰባስብም አሁንም ግን ሕጉ መከበር እንዳለበት አጥብቀው የሚጠይቁ ኢራናውያን አሉ።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ አንድ ሰው ሁለት ሂጃብ ያልለበሱ ሴቶች ላይ እርጎ ሲደፋባቸው በቪዲዮ ታይቷል። ቪዲዮው መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ ግለሰቡ ታስሯል።
ነገር ግን እርጎ የተደፋባቸው ሴቶችም ሕጉን አላከበራችሁም በሚል እነርሱም ለእስራት ተዳርገዋል።
ከአብዮቱ በኋላ ኢራን የተለያየ አይነት አደረጃጀት ያለው የሞራል ፖሊስን ፈጥራለች። አሁን ያለው በ2006 የተቋቋመ ነው።
የፖሊስ ኃይሉ ምን ያክል ሴት እና ወንዶችን እንዳቀፈ የተጣራ መረጃ የለም። ነገር ግን ሙሉ ትጥቃቸው የተሟላ እና “የትምህርት ማዕከል” የተሰኘ ማቆያ ቦታ ያላቸው ናቸው።
ኢራን በሰልፈኞቹ ላይ ለወሰደችው እርምጃ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች ምዕራባውያን በሞራል ፖሊስ እና በሌሎች ከፍተኛ የፀጥታ ሰዎች ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።