
ከ 37 ደቂቃዎች በፊት
በመቶዎች የሚቆጠሩ የሩሲያው ቫግነር ቅጠረኛ ቡደን ተዋጊዎች ወደ መካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ መግባታቸው ተሰማ።
ከቫግነር ጋር ግንኙነት ያለው መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ ተዋጊዎች ትናንት ዕሁድ ወደ መካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ መግባታቸውን ገልጿል።
የቡድኑ አባላት በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የጥበቃ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሕዝበ ውሳኔው ሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ፎስቲን-አርቻንጌ ተውዴር ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን መወዳደር ስለመቻላቸው ውሳኔ ይሰጥበታል።
ቫግነር ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። እራሱን ‘የግል ኩባንያ’ ነኝ በሚል የሚገልጸው ቡድኑ፤ ከመካከላኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በተጨማሪ በአፍሪካ ከ10 ባላነሱ አገራት ውስጥ ተሰማርቶ ይገኛል አልያም ተሰማርቶ ነበር።
ሊቢያ፣ ሞዛምቢክ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሱዳን ቫግነር ከተሰማራባቸው አገራት መካከል ተጠቃሽ ነው።
- የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እና ሹመት፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የገጠማት ፈተናከ 5 ሰአት በፊት
- እናት እና አራት ልጆቿን ጨምሮ 13 ሰዎች የሞቱበት የትራፊክ አደጋ በሰሜን ሸዋከ 1 ሰአት በፊት
- በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ችግኝ ለመትከል ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃልከ 5 ሰአት በፊት
ይህ የሩሲያ ቅጠረኛ ቡድን ሞስኮ በኪዬቭ ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ ከሩሲያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ቁልፍ ሚና ሲጫወት ቆይቷል።
ይሁን እንጂ የቡድኑ መሪ በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ አመጽ ከቀሰቀሰ በኋላ፣ በዩክሬን ያለው ተጽእኖ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን አሜሪካ ገልጻለች።
በቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ላይ አመጽ ቀስቅሶ ሩሲያን ለ24 ሰዓታት ትርምስ ውስጥ ከቷት የነበረው ቫግነር፣ አመጹ ከከሰመ በኋላ መሪው ወደ ቤላሩስ እንዲያመራ ተደርጎ ቡድኑ ደግሞ የከባድ መሳሪያ ትጥቅ እንዲፈታ ሆኗል።
ቡድኑ ትጥቅ እንዲፈታ ተደርጎ የቡድኑ ተዋጊዎች ክስ ሳይመሠረትባቸው የሩሲያን ጦር መቀላቀል፣ ወደ ቤላሩስ ማቅናት አልያም ትጥቅ ፈትተው ወደ ቀደመ ሕይወታቸው መመለስ እንደሚችሉ በፑቲን አስተዳደር አማራጭ ተሰጥቷቸው ነበር።
የቅጠረኛው ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ወደ ቤላሩስ እንዲያመራ አማራጭ ተሰጥቶት ነበር። ይሁን እንጂ የቭጌኒ አሁን መገኛው የት እንደሆነ በትክክል አይታወቅም።
ቅዳሜ ዕለት የወጡ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ደግሞ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቫግነር ቅጠረኛ ቡድን አባላት ከሩሲያ ወደ ቤላሩስ ገብተዋል።
ቫግነር እንዲሁም የዩክሬን መንግሥት የቡድኑ አባላት ወደ ቤላሩስ ስለመሻገራቸው ማረጋገጫ የሰጡ ሲሆን፣ 600 የሚሆኑት የቫግነር ቡድን አባላት በቤላሩስ በሚኖራቸው ቆይታ ለቤላሩስ ሠራዊት ወታደራዊ ሥልጣናዎችን ይሰጣሉ ተብሏል።