የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የኢራንኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢስ
የምስሉ መግለጫ,የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የኢራንኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢስን በተቀበለቡት ጊዜ

16 ሀምሌ 2023

የአፍሪካ እና ኢራን ወዳጅነት አንዴ ጠበቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲላላ አሁን ካለበት ደረጃ ደርሷል። የአፍሪካ እና የባሕረ ሰላጤዋ አገር ግንኙነት ከፖለቲካ እስከ ሃይማኖት፤ ከኪነ ጥበብ እስከ ምጣኔ ሃብት የተገነባ ቢሆንም ግንኙነታቸው ግን ሁሌም ውስብስብ ነው።

ፖለቲካ

የኢራን እና አፍሪካ ፖለቲካዊ ግንኙነት ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲገነባ ቆይቷል። በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት በ1970ዎቹ የኢራን መሪ የነበሩት ሻሃ፣ ፀረ ኮሚኒስት ከሆኑ የአፍሪካ አገራት ጋር ወዳጅነትን ለመመሥረት ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አዙረው ነበር።

እስላማዊ ሪፐብሊክ ኢራን ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ስትጠር ብትቆይም ዲፕሎማሲዋ ሁሌም ውጤታማ አልነበረም።

አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢስ በኬንያ፣ በኡጋንዳ እና በዚምባብዌ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ። የኢራን ፕሬዝዳንት ወደ አፍሪካ ለጉብኝነት ሲመጣ ይህ ከ10 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው ነው።

ከዚህ ቀደም ኢራንን ለሁለት የሥልጣን ዘመናት የመሩት ሐሰን ሩሃኒ በሥልጣን ዘመናቸው አንድ ጊዜ እንኳን ወደ አፍሪካ አላቀኑም ነበር።

ለመጨረሻ ጊዜ ወደ አፍሪካ የመጡት የኢራን መሪ መሐሙድ አሕመዲነጃድ ሲሆኑ፤ በአውሮፓውያኑ 2013 ቤኒን፣ ኒጀር እና ጋናን ጎብኝተው ነበር።

ኢራን በኑክሌር ጉዳይ ከአውሮፓ ኅብረት እና ከአሜሪካ ጋር ከስምምነት ስትደርስ አብዛኛው የአፍሪካ አገራት በጉዳዩ ገለልተኛ አቋም መያዝን መርጠው ነበር።

እአአ 2006 ኢራን ሁሉንም አይነት ዩራኒየም የማበልጸግ ሥራዋን እንድታቆም የሚከለክለውን የተባበሩት መንግሥታት የውሳኔ ሐሳብን ደግፈው ኮንጎ፣ ጋና እና ታንዛኒያ ድምጽ ሰጥተው ነበር።

ሃይማኖት

የሃይማኖት ጉዳይ በኢራን እና በአፍሪካ ግንኙነት ዙሪያ ጉልህ የሆነ ተጽእኖ አሳድሯል። የአብዛኛው የሺዓ እስልምና ዕምነት ተከታዮች መገኛ የሆነችው ኢራን፤ ሱኒ ሙስሊሞች ከሚበዙባት አፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ብትሞክርም ብዙ ስኬት አልተመዘገበም።

ለእዚህ ሁነኛ ማሳያ ናይጄሪያ ናት። ከአውሮፓውያኑ 1990 ጀምሮ ኢራን በምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጄሪያ የሺዓ ሙስሊም ስብስብ የሆነውን እስላማዊ እንቅስቃሴ ለመደገፍ ጥረት አድርጋ ነበር።

ኢራን ‘ኢስላሚክ ሙቭመንት ኢን ናይጄሪያ’ የተባለውን ቡድን ለመደገፍ ጥረት ማድረጓ የናይጄሪያን መንግሥት ያስደሰተ አልነበረም። ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ኢራን በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባች ነው ስትል ትከሳለች።

እአአ 2015 ማብቂያ ላይ የናይጄሪያ ጦር ከ350 ያላሱ የእንቅስቃሴው ቡድን አባላትን በመግደል የቡድኑ መሪ የነበረውን ሼክ ኢብራሂም ዛክዛሊን በቁጥጥር ሥር አውላላች።

ኢራን ይህን ክስተት አውግዛ የቡድኑ መሪ ከእስር እንዲፈታ በይፋ ስትጠይቅ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጡን ሻከረ።

የኢራኑ ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በኬንያ
የምስሉ መግለጫ,የኢራኑ ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በኬንያ በጀመሩበት ጊዜ የተደረገላቸው አቀባበል

ባሕል እና ኪነ ጥበብ

ባሕል ልውውጥ የአፍሪካ እና የኢራን ግንኙነትን ለማጠናከር ትልቅ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል። የኢራን ፊልሞች በአፍሪካ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ለዕይታ ሲቀርቡ ቆይተዋል።

በግብፅ እና በዛንቢዛበር ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ለዓመታት የኢራን ፊልሞች ለተመልካች ሲቀርቡ ቆይተዋል።

በተመሳሳይ በኢራኑ ፋጀር ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ የተመረጡ የአፍሪካ ፊልሞች ይታያሉ።

ከዚህ በተጨማሪም እንደ ሴኔጋል፣ ኡጋንዳ እና ኬንያ ባሉ አገራት የኢራን ባሕል ማዕከላት የፋርስ ቋንቋን እና የኢራን ባሕልን ከሃያ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል።

ምጣኔ ሃብት

ኢራን ከአፍሪካ አገራት ጋር ለበርካታ አስርት ዓመታት የንግድ ልውውጥ ስታደርግ ቆይታለች። በኃይል፣ በግንባታ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች በአፍሪካ ውስጥ መዕዋለ ነዋይ አፍስሳለች።

በተለይ በ1990ዎቹ እና በ2000ዎቹ ኢራን በሱዳን የነዳጅ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ኢንቨስት አድርጋ ነበር። ይሁን እንጂ ኢራን በምዕራባውያኑ የተጣሉባት ማዕቀቦች ከአፍሪካ አገራት ጋር በምጣኔ ሃብት ያላት ግንኙነት እንዳይጠናከር ምክንያት ሆኗል።