
16 ሀምሌ 2023
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳን ስትሾም በተመሳሳይ ቀን በትግራይ አስር ኤጲስ ቆጶሳት መመረጣቸው ተገለጸ።
ቤተክርስቲያኗ የሾመቻቸው አባቶች በቅርቡ ቅዱስ ሲኖዶሱ የመረጣቸው ዘጠኝ የአህጉረ ስብከት ቆሞሳትን ሲሆን፣ ሥነ ሥርዓት መሠረት ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም. ተካሂዷል።
የዘጠኙ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ መሪነት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተከናውኗል።
እራሳቸውን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመለየት መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መመሥረታቸውን የገለጹት የትግራይ አባቶችም በበኩላቸው 10 ኤጲስ ቆጶሳትን መርጠዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተሾሙት ዘጠኙ ኤጲስ ቆጶሳት የተሾሙት ለጌዴኦ፣ አማሮ እና ቡርጂ ሀገረ ስብከት፣ ለምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ ለዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት፣ ለምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት፣ ለድሬዳዋ ሀገረ ስብከት፣ ለቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት፣ ለሆሮ ጉድሩ ሀገረ ስብከት፣ ለምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት እና ለምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ነው።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ፓትሪያርኩ አቡነ ማትያስ ባደረጉት ንግግር በቤተ ክርስቲያኒንቱ ውስጥ ባልተጠበቀ እና ባልተለመደ ሁኔታ እየታዩ ነው ያሏቸው “ራስን በራስ የመሾም አባዜ መገታት አለባቸው” ብለዋል::
ጨምረውም የሚከሰቱ ችግሮች በውይይት እና በምክክር የተበደለውንም በመካስ መፈታት ይገባዋል በማለት “ከዚህ ውጭ በጥፋት ላይ ጥፋት እየተከሠተ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተን ድርጊት ማቆም አለብን” ሲሉ አሳስበዋል።
በሥርዓተ ሢመት እና የሥራ ምደባው ላይ ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስን ጨምሮ የቅዱስ ሲኖዶስ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የሃማኖት አባቶች፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና የእምነቱ ተከታይ ምዕመናን ተገኝተዋል።
ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት የተካሄደው የትግራይ የሃይማኖት አባቶችም ተመሳሳይ ሹመት እንሰጣለን ባሉበት ዕለት ነው።
በትግራይ የተቀሰቀውን ጦርነት ተከትሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የነበረው ግንኙነት መሻከሩ ይታወቃል።
ይህን ተከትሎ የትግራይ አባቶች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጥ መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተ ክህነትን መስረተዋል።
- የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና ከወሰዱት ውስጥ ያለፉት 40 በመቶ መሆናቸው ተገለጸ15 ሀምሌ 2023
- ከምዕራባውያን ጋር ፍጥጫ ውስጥ ያለችው ኢራን ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነትን በአራት ነጥቦች16 ሀምሌ 2023
- በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን አምክነዋል በሚል በሐሰት የተከሰሱት ዶክተር16 ሀምሌ 2023
የትግራይ የሃይማኖት አባቶች ዛሬ ሐምሌ 09/ 2015 ዓ.ም. በአክሱም የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንሰጣለን በማለት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ገደማ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።
በዚህ መሠረትም በታሪካዊቷ አክሱም ፅዮን ቤተክርስቲያን በተካሄደ ሥነ ሥርዓትም 10 ኤጲስ ቆጶሳት የተመረጡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አምስቱ በትግራይ ውስጥ ቀሪዎቹ አምስቶች ደግሞ በውጪ አደራት ያገለግላሉ ተብሏል።
የትግራይ አባቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የቀረበባቸውን ተቃውሞ ሳይቀበሉት ምርጫውን ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም. ያካሄዱ ሲሆን፣ በቀጣይም ሹመቱ በይፋ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ይህንን ሹመት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገወጥ ነው በማለት መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት ካበቃ በኋላ የተፈጠረውን ቅሬታ ለመፍታት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲያደርግ መቆየቱን፣ ነገር ግን በክልሉ ያሉት አባቶች እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን “የሰላም እና የውይይት በርን ከመጠቀም ይልቅ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን ጥሰዋል” ብሏል።
በዚህም መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት መሥርተናል በማለት “ተገቢነት የሌለው መግለጫ ከመስጠትም አልፎ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት” ለመስጠት መዘጋጀታቸው ተቀባይነት የለውም በማለት የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ድርጊቱን እንዲያስቆም ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህን የኤጺስ ቆጶሳት ሹመት በማውገዝ የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ገብነትን ብትጠይቅም ዛሬ በአክሱም የሚሰጠው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንደሚከናወን ከክልሉ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች ያመላክታሉ።