ኢላን መስክ

ከ 4 ሰአት በፊት

ትዊተር የተሰኘውን ማሕበራዊ ሚድያ ባለፈው ጥቅምት ኢላን መስክ ንብረቱ ካደረገው በኋላ ከማስታወቂያ የሚገኘው ገቢ በግማሽ መቀነሱን ባለቤቱ ገለጠ።

ትዊተር ባለፈው ሰኔ ምንም ዓይነት የሽያጭ ጭማሪ አላሳየም በያዝነው ሐምሌ ግን “ይሻላል” ብሏል።

ኢላን መስክ ባለፈው ዓመት ትዊተርን ሲሸምት ከነበሩት 7500 ሠራተኞች መካከል ግማሹን ማባረሩ አይዘነጋም።

በቅርቡ ይፋ የሆነው ትሬድስ የተባለው የትዊተር ተቀናቃኝ 150 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳጋበሰ ይገመታል።

ከኢንስታግራም ጋር ግንኙነት እንዲኖረው ተደርጎ በሜታ የተሠራው ትሬድስ ሁለት ቢሊዮን ተጠቃሚዎች የመመዝገብ አቅም አለው።

ትዊተር ደግሞ በፊናው በከፍተኛ ዕዳ በመዘፈቁ ገቢ ለማግኘት እየተቸገረ ይገኛል።

ኢላን፤ የማስታወቂያ ገቢው 50 በመቶ መች እንደቀነሰ የሚጠቁም የጊዜ ሠሌዳ ይፋ አላደረገም።

መስክ በትዊተር ገፁ “ከዜሮ በታች ያለውን የገንዘብ ፍሰት ወደላይ ከፍ ማድረግ አለብን ከዚያ በኋላ ነው ሁሉን እንደልባችን የምናደርገው” ብሏል።

የድርጅቱን ግማሽ ሠራተኞች ካባረረ፤ ቀጥሎ ደግሞ ለመረጃ ቋት ለሚጠቀመው ‘ክላውድ’ የሚከፈለውን ከቀነሰ በኋላ ባለሃብቱ ኢላን መስክ በ2023 “3 ቢሊዮን ዶላር እናስገባለን” ብሎ ነበር።

በ2021 ትዊተር 5.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቶ ነበር።

ትዊተር አንዳንድ ሕጎቹን ከቀየረ በኋላ ጥለው የወጡ ምርትና አገልግሎት የሚያስተዋውቁ ድርጅቶች አለመመለሳቸው አንዱ ምክንያት ሆኖ ተቆጥሯል።

መስክ ወጭ ለመቀነስ ያደረጋቸው እርምጃዎችም በቂ አለመሆናቸውን የትዊተር ገቢ ማሽቆልቆል ይጠቁማል።

የትዊተር ባለቤት ባለፈው ሚያዚያ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ በርካታ ድርጅቶች ተመልሰዋል ብሎ ነበር።

በያዝነው የፈረንጆቹ ወር መባቻ መስክ ተጠቃሚዎች ምንያክል ትዊት ማየች ይችላሉ ለሚለው ገደብ አስቀምጦ መነጋጋሪያ ሆኖ ነበር።

ቬሪፋይድ አሊያም ሰማያዊ እርማት ያላቸው ተጠቃሚዎች 10 ሺህ ትዊት፤ የሌላቸው ደግሞ 1 ሺህ ብሎ ነበር።

ይህ እርምጃቸው በርካታ ማስታወቂያ ለሚለቁ ድርጅቶች ግራ አጋቢ ሆኖ ቆይቷል።

መስክ ይህን ያደረገው ተጠቃሚዎች በገንዘባቸው ሰማያዊ እርማት ገዝተው ቬሪፋይድ እንዲሆኑ በማሰብ እንደሆነ ተጠቁሟል።

የቀድሞ የኤንቢሲ ዩኒቨርሳል የማስታወቂ ክፍል ኃላፊ የነበረችው ሊንዳ ያካሪኖ ባለፈው ሰኔ የትዊተር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆና ተሹማለች።

ይህ ትዊተር አሁንም ከማስታወቂያ ገቢ ለማግኘት ብዙ እየጣረ መሆኑን ጠቋሚ ነው።

ሥራ አስኪያጇ፤ ትዊተር ከዚህ በኋላ ቪድዮ ይዘት ራሳቸው የሚፈጥሩ [ኮንቴን ክሬተርስ] እና የንግድ ግንኙነት ላይ ያተኩራል ብላለች።

ትዊተር የፖለቲካና የመዝናኛ ሰዎች ወደ ትዊተር መጥተው ገቢ የሚያገኙበት መንገድ ለማመቻቸት እየሞከረ መሆኑም ተሰምቷል።