አቡነ ማትያስ ሹመት በሰጡበት ጊዜ
የምስሉ መግለጫ,አቡነ ማትያስ ሹመት በሰጡበት ጊዜ

ከ 6 ሰአት በፊት

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈላት ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ደም አፋሳሹ የእርስ በርስ ጦርነት መጠናቀቁን ተከትሎ በአገሪቱ ጉልህ ቀውስ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የገጠማት ተጠቃሽ ነው።

በጦርነቱ ወቅት ግንኙነታቸው ተቋርጦ የቆዩ የትግራይ የሃይማኖቱ መሪዎች እና ምዕመናን ቤተክርስቲያኗ ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ የቆየ ሲሆን፣ በድንገት የተሰጠው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመትም ሌላኛው ቀውስ ነበር።

ጦርነቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ሲያስከትል፣ በትግራይ የሚገኙ አባቶች ቤተክርስቲያኗ ጦርነቱን በማውገዝ እና በክልሉ ለሚገኙ ቀሳውስት እና ምዕመናን የሚጠበቅባትን አላደረገችም ሲሉ ወቅሰዋል።

ይህ ሁኔታ ግን በቅሬታ እና በተቃውሞ ሳያበቃ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ማብቂያ ላይ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በመነጠል የራሳቸውን ቤተክህነት ለመመሥረት መወሰናቸው ይታወሳል።

በጦርነቱ በትግራይ ውስጥ ያሉ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን እንዲሁም የእምነት ስፍራዎች ጭምር ጉዳት እንዳጋጠማቸው የተለያዩ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል።

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በትግራይ ያሉት የሃይማኖት አባቶች በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በትግራዩ ጦርነት ለፌደራል መንግሥቱ ወግናለች ሲሉ ከሰዋል።

ቢሆንም ግን የቤተክርስቲያኗ ፓትሪያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ጦርነቱ ያስከተለውን ጉዳት በማንሳት ሰላም እንዲወርድ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር። እሳቸውም በሚገባቸው መጠን ስለጦርነቱ መናገር በሚችሉበት ሁኔታ እንዳልነበሩ በአንድ አጋጣሚ ተናግረዋል።

የአካታችነት ጥያቄ

በአገሪቱ ከፍተኛ ተከታይ ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በዚህ ዓመት ከገጠሟት ፈተናዎች መካከል ሌላኛው ደግሞ ጥር 14/2015 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ውስጥ የተፈጸመው የ26 ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ነበር።

ከቤተክርስቲያኗ ሕግ እና እውቅና ውጪ የተፈጸመውን ይህንን ሹመት የመሩት አቡነ ሳዊሮስ፣ ቤተክርስቲያኗ ምዕመናን በቋንቋቸው የእምነታቸውን ሥነ ሥርዓት እንዲፈጽሙ አላስቻለችም በማለት የአካታችነት ጥያቄ አንስተው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ድርጊቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት፣ የቀኖና እና የአስተዳደራዊ ጥሰቶች የሚፈጽም ነው በማለት፣ ሹመቱን የሰጡ እና የተቀበሉ አባቶች ይቅርታ ጠይቀው እስኪመለሱ ድረስ ተወግዘው እንዲለዩ ወስኖ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ፍጥጫዎች እና የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ያልተመጣጠነ ኃይል በጥይት እና በድብደባ ግድያዎች መፈጸማቸውን፣ እንዲሁም ለእስር የተዳረጉ በርካታ ሰዎች እንደነበሩ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጹ ይታወሳል።

ይህ ቤተክርስቲያኗን ያጋጠማት ቀውስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራ ሽምግልና መፍትሔ አግኝቶ የተወገዙት አባቶች በይቅርታ እንዲመለሱ ተደርጎ፣ የቀረበው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ጥያቄ በቅዱስ ሲኖዶስ አማካይነት በቤተክርስቲያኗ ሥርዓት እና ደንብ መሠረት ምላሽ እንደሚያገኝ ከስምመነት ተደርሶ ተቆጭቷል።

አቡነ ማትያስ
የምስሉ መግለጫ,አቡነ ማትያስ

የቤተ ክርስቲያኗ ይቅርታ

ቀጣይ የቤተክርስቲያኗ ትኩረት የነበረው ከትግራይ አባቶች ጋር ተቋርጦ የቆየውን ግንኙነት ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ነበር። ለዚህ የመጀመሪያ እርምጃ የነበረው ይፋዊ ይቅርታ በትግራይ ላሉ የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን እና አባቶች ማቅረብ ነበር።

ቅዱስ ሲኖዶሱ በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ወቅት ቤተ ክርስቲያኗ “ጦርነቱ እንዲቆም በወቅቱ መግለጫ ባለመስጠቷ፣ በጦርነቱ መካከልም በሚቻልበት ወቅት የክልሉን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንት እና ሕዝቡን ባለመጠየቋ እንዲሁም ባለማጽናናቷ ለተፈጠረው ቅሬታ እና አለመግባባት” በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።

የቤተክርስቲያኗን የይቅርታ ጥያቄን ተከትሎ በፓትሪያርኩ የሚመራ ቡድን ከክልሉ አባቶች እና አመራሮች ጋር ለመገናኘት ቢያመራም ያሰቡት ሳይሳካ ቀርቷል። የትግራይ ሃይማኖት አባቶቹ በየትኛውም ሥነ ሥርዓት ላይ ካለመገናኘታቸው በተጨማሪ ቡድኑ በመቀለ ወደሚገኝ ቤተክርስቲያን ባመራበት ወቅት ዝግ በመሆኑ ፓትሪያርኩ ከውጪ መመለሳቸው ተዘግቧል።

ይህም ከቅዱስ ሲኖዶስ የቀረበው የይቅርታ ጥያቄ በትግራይ አባቶች ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት እንዳላገኘ አመላካች ነው ሊባል ይችላል። በትግራይ ያሉ አባቶች መሠረትነው ያሉት የመንበረ ሰላማ ቤተ ክህነት የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑ አንድ አባት “ጅምሩ ምልካም ቢሆንም የዘገየ እና በቂ አይደለም” ብለው ተናግረዋል።

በትግራይ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ በተካሄደበት ወቅት
የምስሉ መግለጫ,በትግራይ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ በተካሄደበት ወቅት

የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት

ቀደም ሲል ከቤተክርስቲያኗ ሥርዓት እና ደንብ ውጪ ተሹመዋል ከተባሉት 26 ኤጴስ ቆጶሳት ጋር በተያያዘ ቅዱስ ሲኖዶሱ የተራዘመ ስብሰባ አድርጎ ነበር። በዚህም አስፈላጊ የተባሉ ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት በመምረጥ ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም. ለመሾም ቀጠሮ ይዞ እንደነበር ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ በአቡነ ማትያስ የተመራው ቡድን ወደ ትግራይ ደርሶ ከተመለሰ በኋላ፣ በክልሉ ያሉ አባቶች በበኩላቸው በተመሳሳይ ዕለት የራሳቸውን ኤጲስ ቆጶሳትን ለመምረጥ መወሰናቸውን ይፋ አደረጉ።

የተፈጠረውን ቅሬታ ለመፍታት ጥረት እያደረገ የነበረው የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ በክልሉ ያሉት አባቶች እና ሊቃውንት በዚህ ውሳኔያቸው “የሰላም እና የውይይት በርን ከመጠቀም ይልቅ መዋቅራዊ አደረጃጀትን ጥሰዋል” በማለት የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ድርጊቱን እንዲያስቆም ጠይቋል።

ሹመቱን “ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ያላከበረ እና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር ተገቢ ያልሆነ፣ የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊነት የሚጥስ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚጎዳ ነው” በመሆኑ ተገቢነት የለውም ብሎ አውግዞታል።

የተፈጠረው ቅሬታ እና ችግርም በውይይት እንዲፈታ ጥሪ ያቀረበው ቅዱስ ሲኖዶስ “የሰላም ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን እስካሁን ሰላም መፈለጓ ያልተቋረጠ ቢሆንም፣ አለመሳካቱ የሚያሳዝን በመሆኑ ለሰላም የሚደረገው ጥረት ዘላቂ መፍትሔ እስከሚገኝ ድረስ የማይቋረጥ ነው” ብሎ ነበር።

አዲስ አበባ እና አክሱም

ቀደም ሲል ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ ቅዱስ ሲኖዶሱ በወሰነው እና በተካሄደው ምርጫ አማካይነት የተመረጡት ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት እሁድ ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም. በፓትርያርክ አቡነ ማትያስ መሪነት አዲስ አበባ ውስጥ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተፈጽሟል።

አሁን የተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል ውስጥ ባሉ አህጉረ ስብከቶች ተመድበው የሚያገለግሉ ሲሆን፣ ለቀሪ አገረ ስብከቶች የሚያስፈልጉ ኤጲስ ቆጶሳትም በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ እንደሚወሰን ተነግሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም እራሳቸውን የመንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብለው የሚጠሩት አባቶች፣ በበኩላቸው በታሪካዊቷ የአክሱም ፅዮን ቤተክርስቲያን የራሳቸውን ኤጲስ ቆጶሳት የሚሆኑ ዕጩዎችን እሁድ ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም. በተመሳሳይ ቀን ማካሄዳቸው ታውቋል።

በዚህም አምስት ለክልሉ፣ አምስት ደግሞ በውጭ አገራት የሚያገለግሉ በአጠቃላይ አስር ኤጲስ ቆጶሳት መመረጣቸው እና በቀጣይም በሚካሄድ ሥነ ሥርዓት ሹመቱ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ይህ ሁኔታም በቅዱስ ሲኖዶሱ በኩል የቀረበው ይቅርታ፣ ለመቀራረብ እና ለመነጋገር የተደረገው ጥረት ፍሬ አለማፍራቱን የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም በማዕከላዊው ሲኖዶስ እና በትግራይ አባቶች መካከል ያለው አለመግባባት እየሰፋ መሄዱን አመላካች ነው።

ነገር ግን አሁንም ቤተክርስቲያኗ በትግራይ አባቶች ኤጲስ ቆጶስ ለመሾም የሚደረገውን ጥረት እንደማትቀበለው፣ እሁድ ዕለት በተካሄደው የሹመት ሥነ ሥርዓት ላይ ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ ባደረጉት ንግግር ተናግረዋል።

ፓትሪያርኩ በቤተ ክርስቲያኒንቱ ውስጥ ባልተጠበቀ እና ባልተለመደ ሁኔታ እየታዩ ነው ያሏቸው “ራስን በራስ የመሾም አባዜ መገታት አለበት” በማለት፣ የሚከሰቱ ችግሮች በውይይት እና በምክክር፣ የተበደለንም በመካስ መፈታት ይገባል “ከዚህ ውጭ በጥፋት ላይ ጥፋት እየተከሠተ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተን ድርጊት ማቆም አለብን” ሲሉ አሳስበዋል።