
July 17, 2023 – EthiopianReporter.com

የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ወቅታዊ ገጽታ
ዜና የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ላልተጠቀመበት ቢሮ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ መክፈሉ…
የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ላልተጠቀመበት ቢሮ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ መክፈሉ በኦዲት ተረጋገጠ
ቀን: July 16, 2023
ከተቋቋመ 11 ዓመታት ያስቆጠረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ ላልተጠቀመበት ቢሮ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙ በኦዲት ሪፖርት ይፋ ተደረገ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት እንደሚያሳየው የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት የቆየና በአጠቃላይ 2.7 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ከአምስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት የቆየ 43.9 ሚሊዮን ብር፣ በአጠቃላይ 46.7 ሚሊዮን ብር ለምን ተከፋይ ሒሳብ እንደሆነ፣ ምዝገባው በተከናወነበት ሰነድም ሆነ ሒሳቡ ለማን እንደሚከፈል የሚገልጽ የመነሻ ሰነድና ማስረጃ ተጠይቆ ማቅረብ አልቻለም፡፡ እንዲሁም ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለተከራየው ያልተገለገለበት ቢሮም 7.8 ሚሊዮን ብር መክፈሉን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ከሕዝቡ በስጦታ የመጡና በሁለት መጋዘኖች የተቀመጡ አዳዲስ ቋሚ ንብረቶች በተለይም ብዛት ያላቸው የውኃ ማጣሪያዎች፣ ፍሪጆች፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ ቴሌቪዥኖች፣ የሞባይል ቀፎዎች፣ ባጃጅና ሞተር ብስክሌት በቆጠራ የተገኙ መሆናቸውን የጠቀሰው የኦዲት ሪፖርቱ፣ እስካሁን ምንም ዓይነት ዕርምጃ አለመወሰዱን በኦዲት ግኝቱ አሳውቋል፡፡
የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብርሃም ለሪፖርተር እንደነገሩት፣ ጽሕፈት ቤቱ ከመቋቋሙ በፊት በቀድሞው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ከሕዝብ ሀብት ማሰባሰቢያ አካውንት ተከፍቶ ነበር፡፡ ይሁንና ገንዘቡ ባንክ ቢቀመጥም ባለቤት ሳይኖረው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ሕዝብ ማስተባበር ሥራው በመሆኑ ሕዝብ ለስብሰባ በሚጠራበት ወቅት ገንዝብ ወጪ በማድረግ የምሳ ግብዣ እንዲደረግ፣ ነገር ግን ምሳ መጋበዝ የሚል አሠራር የለም ተብሎ በክፍተት እንደሚያዝ ተናግረዋል፡፡
ሕዝቡ ገንዘብ ለግድቡ ግንባት እንዲያዋጣ ለቅስቀሳ የሚሆን ዶክመንተሪ ቪዲዮ ለማሠራት ጽሕፈት ቤት በሚያስብበት ወቅት፣ የሚመደብለት በጀት ትንሽ በመሆኑ አወዳድሮ ማሠራት ስለማይችል በትብብር ከሚሠሩ የሚዲያ ተቋማት ጋር በመሆን በቀነሰ ዋጋ ሲያሠራ፣ አወዳድራችሁ የከፈላቸሁበትን አምጡ ተብለው ሲጠየቁ ማቅረብ ስለማይችሉ በኦዲት ክፍተት ተብሎ እንደሚያዝ አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ በኦዲት ሪፖርቱ እንደ ክፍተት የተወሰዱት ንብረቶች ከሕዝብ በስጦታ የተሰጡ በመሆናቸውና ጽሕፈት ቤቱም መጠቀም ስለማይችል፣ ተሸጠው ወደ ህዳሴው ግድብ አካውንት እንዲገቡ ጨረታ ወጥቶባቸዋል ብለዋል፡፡
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው የፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ አሁን የሚጠቀምበት ቢሮ በመጥበቡ ምክንያት፣ ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ስታዲየም አካባቢ የሚገኘውንና የኤርትራ ኤምባሲ ይጠቀምበት የነበረውን ግቢ አሳድሶ እንዲጠቀም መዋዋሉን አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡ የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ በዚህ ግቢ ይገለገል የነበረው የኤርትራ ኤምባሲ ለቆ አምቼ አካባቢ መግባቱ ይታወሳል፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባቀረበው የኦዲት ሪፖርት የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ቢሮውን ከግንቦት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን የተከራየ ቢሆንም፣ ቢሮው ውስጥ ሳይገባ ላልተገለገለበት ኪራይ በአጠቃላይ 7.8 ሚሊዮን ብር መከፈሉን በተመለተ፣ አዲሱን ጽሕፈት ቤት ቢረከቡትም ሙሉ ግቢውን አሳድሶ ለመግባት የሚጠይቀው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ እስካሁን መዘግየታቸውን አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ሕዝባዊ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተወያይቶበት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሙሉ ዕድሳት ከፍተኛ መጠን ያለው ወጪ አድርጎበት ወደ አዲሱ ቢሮ ለመዘዋወር ዕቅድ እንዳለ አቶ ኃይሉ አስረድተዋል፡፡