
July 17, 2023 – EthiopianReporter.com

በአዲስ አበባ የሜትር ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ከሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ይሰበስብ የነበረውን አሥር በመቶ የተርን ኦቨር ታክስ (ቲኦቲ) አነሳ፡፡
ቢሮው ከገንዘብ ሚኒስቴር አገኘሁት ባለው ማብራሪያ መሠረት፣ በኮድ 03 የሜትር ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡትን ተሽከርካሪዎች ነው የተጨማሪ እሴት ታክስና ተርን ኦቨር ታክስ ተግባራዊ እንዳይሆንባቸው የወሰነው፡፡
ተሽከርካሪዎቹ በንግድ ሥራ ፈቃዳቸው ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ቢልም፣ ሊብሬያቸው የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ እንደሆኑ በመጥቀሱ አሥር በመቶው የአገልግሎት ሰጪዎች ተርን ኦቨር ታክስ ተግባራዊ ይደረግባቸው ነበር፡፡
ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በታክስ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ታዬ ማስረሻ ተፈርሞ ለአሥራ አንዱም ክፍላተ ከተሞችና ለአምስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የተላከው ደብዳቤ፣ አገልግሎቱን የሚሰጡ የሜትር ታክሲ ተሽከርካሪዎች ከሁለቱ ታክሶች ነፃ እንዲሆኑ አስታውቋል፡፡
‹‹የሚሰጡት አገልግሎት የትራንስፖርት በመሆኑ የንግድ ሥራ ገቢ ግብርን በተመለከተ ግብር ከፋዮች የሚያቀርቡት የሒሳብ መዝገብ፣ የሒሳብ መዝገብ ካልያዙ ደግሞ በመረጃ እንዲስተናገዱ፤›› ይላል ደብዳቤው፡፡
በገቢዎች ቢሮ የግብር አወሳሰንና አሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ወንድማገኘሁ ካሳዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሜትር ታክሲዎች የብቃት ማረጋገጫቸው የመኪና ኪራይ የሚልና ኮድ 3 ሰሌዳ የሚወስዱ ቢሆንም፣ በኮድ 1 ተሽከርካሪዎችም ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
‹‹ይህ ደግሞ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡትን የተለያየ የታክስ አከፋፈል ስለሚተገበርባቸው ቅሬታ ሲያስነሳ ነበር፤›› ብለዋል፡፡
የኅብረተሰቡን የትራንስፖርት ጫና በማየትና ተሽከርካሪዎችን እንደ ኮድ 1 በመቁጠር፣ ቢሮው ታክሱን እንዳነሳው ነው አቶ ወንድማገኘሁ የገለጹት፡፡
በኮድ 3 የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን ከታክሱ ነፃ መሆን ዕድል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ፣ ቢሮው እነሱን ለመለየት በሲስተሙ ላይ እየሠራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
‹‹የሜትር ታክሲ አገልግሎት ከሚያቀላጥፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም መረጃ እየሰበሰብን ነው፤›› ሲሉ አቶ ወንድማገኘሁ አስረድተዋል፡፡